
ለሁለተኛ ተከታታይ አለም ዋንጫ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ከምድብ ማለፍ አቅቶት በጊዜ ተሰናብቷል፡፡ ከ2018 በፊት ለመጨረሻ ጊዜ ከምድብ ሳያልፍ የቀሩት 1938 አ.ም ነበር፡፡
ለረጅም ጊዜያት የውድድሮች የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የመድረስ ልምድ ያላት ጀርመን አሁን የምትገኝበት የውጤት ቀውስ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የፈረንጆቹ ሚሊኒየም ከገባ በኃላ ያሉትን ውጤቶች ስንመለከት ጀርመን በ2002 የፍጻሜ ተፋላሚ የነበረች ሲሆን በ2006 እና 2010 ውድድሮች ደግሞ ሶስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡ በ2014 ደግሞ በታሪኳ ለ4ኛ ጊዜ አለም ዋንጫውን ከፍ አድርጋ አንስታለች፡፡ ታድያ ይህ በሆነበት ማግስት እንዴት የውጤት ቀውስ ሊያጋጥም ቻለ?
ከ2014 በኃላ ጀርመንን በግልጽ ክፍተት ፈጥሮባት የነበረው ጉዳይ ወሳኙ አጥቂያቸውን ሚሮስላቭ ክሎዘን የመተካት ጉዳይ ነበር፡፡ በ2016 አውሮፓ ዋንጫ ማርዮ ጎሜዝ የክሎዘ ቀጥተኛ ተተኪ ሆኖ ቀርቦ ነበር ሆኖም ግን የረጅም ጊዜ መፍትሄ እንደማይሆን ግልጽ ነበር፡፡
በአውሮፓ እግር ኳስ ውስጥ እያጋጠመ የመጣው እውነተኛ 9 ቁጥር ተጫዋቾችን የማፍራት ችግር ጀርመን ቤት ውስጥም ነበር፡፡ በትልቅ ደረጃ ሲጠበቅ የነበረው እና የአጥቂነቱን ሚና በጥሩ ሁኔታ ይወጣል ተብሎ የተጠበቀው ቲሞ ቨርነር በአር ቢ ላይብዚሽ ቤት ውስጥ ያሳየውን ብቃት በ2018ቱ አለም ዋንጫ ማሳየት አልቻለም ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ኳስን ተቆጣጥሮ እና ከኃላ መስርቶ ለሚጫወት ቡድን የቨርነር ሚና እንደማይስማማ አስተውለናል፡፡ እርሱ ስኬታማ የሆነው በcounter-pressing አጨዋወት ስልት ለሚተገብር ቡድን ነው፡፡
በ2022ቱ አለም ዋንጫ ጀርመኖች የአጥቂ ስፍራ ችግራቸውን ለመፍታት እንደአማራጭ ይዘው የሄዱት ከአመት በፊት በሁለተኛ ዲቪዝዮን ሲጫወት የነበረውን የ29 አመቱን የቨርደር ብሬመን አጥቂ ኒክላስ ፉልክሩግን ነው፡፡ ምንም እንኳን ሁለት ግቦችን ቢያስቆጥርም ቡድኑን ከመውደቅ ሳይታደግ ቀርቷል፡፡
ለጀርመን በአጥቂ ስፍራ የወደፊቱ ተስፋ በቅርቡ የ18 አመት ልደቱን ያከበረው ዩሱፋ ሙኮኮ ነው፡፡ አሁን ባለበት አቋሙ እንዲቀጥል እና የዚህ ወሳኝ ቦታ መፍትሄ እንዲሆን የጀርመን ደጋፊዎች ጸሎት ነው፡፡
ሌላኛው የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ክፍተት የሚስተዋለው በተከላካይ መስመር ላይ ነው፡፡ በ2014 አሸናፊ በነበሩበት ወቅት እንደ ፊሊፕ ላህም፤ ጄሮም ቦአቴንግ፤ ማትስ ሃምልስ፤ ፔር ሜተሳከር የመሳሰሉ ጥራታቸው ከፍ ያለ እና በአመራር ብቃታቸውም የተመሰከረላቸው ተከላካዮች ነበሩ፡፡
በአሁኑ ወቅት ያለው የተከላካይ መስመር ብዙ ጥያቄዎች የሚነሱበት ነው፡፡ የቀድሞው የብሄራዊ ቡድኑ ተጫዋች ባስቲያን ሽዋንሽታይገር ከአንቶኒዮ ሩዲገር ዉጪ ሌሎቹ ተከላካዮች ለብሄራዊ ቡድኑ አይመጥኑም ማለቱ ብዙም አከራካሪ አይመስልም፡፡
የትኩረት ማጣት ችግሮች በጃፓኑ ሽንፈትም ሆነ በኮስታሪካ በተመሩበት ወቅት የተስተዋሉ ነበሩ፡፡
አሰልጣኝ ሃንሲ ፍሊክ የአጥቂ እና የመስመር ተከላካይ ችግር እንዳለባቸው ያመኑ ሲሆን ራሳቸውን በትኩረት በመመልከት መስተካከል ያለባቸውን ጉዳዮች ማቃናት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡
ጀርመን ከ2004ቱ የአውሮፓ ዋንጫ በኃላ ነገሮችን ሀ ብላ በመጀመር እንዳስተካከለችው ሁሉ አሁንም ብዙ ማስተካከል ያለባት ነገር እንዳለ መረዳት ይቻላል፡፡