
በልኡል ታደሰ
በፎቶው እና በሞሀመድ ሳላህ ማሊያ ምክንያቶች አስቻለው ታመነ የሰሞኑ መነጋገሪያ ሆኗል። ይህንን ልለፈው እና አንድ የግል አስተያየቴን ልግለፅ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አምበሉ ድንቅ ተጨዋች ነው/ነበር።
አስቻለው በተለይ በደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቆይታዎቹ የነበረው ብቃት አስደማሚ ነበር – ፈጣን፣ ጉልበተኛ፣ 1.80ሜ እንኳ በማይሞላ ቁመቱ የአየር ላይ ፍልሚያዎችን የሚያሸንፍ፣ ጥሩ ኳስ አቀባይ፣ ጎበዝ ጨዋታ አንባቢ፣ ደፋር እና በአጭሩ dominant center-back።
የዲላው ተወላጅ በምርጥ ብቃቱ ዓመታት (ከ2007-2013 ገደማ) የሚስተካከለው የመሀል ተከላካይ አልነበረም። እንዲያውም ለእኔ እንደአስቻለው የተሟላ የመሀል ተከላካይ ተሰጥኦ አይቼ አላውቅም። ሁኔታዎች ቢመቻቹ (ከስር አነሳቸዋለሁ) በአውሮፓ መካከለኛ ሊጎች መጫወት ይችሉ ከነበሩ ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች አንዱ እንደሆነም ይሰማኛል።
ኢትዮጵያ ተወልዶ ላደገ ተጨዋች በአውሮፓ ትልልቆቹ እና መካከለኞቹ ሊጎች መጫወት እጅግ ከባድ ነው። ተጨዋቾቻችንን በ’ህልም-አልባነት’፣ በፕሮፌሽናሊዝም ባህሪያ እጥረት፣ ለሙያቸው አለመሰጠት እና ቁርጠኛ አለመሆን መተቸት ተለምዷል። በተሻሉ ሊጎች ላለመጫወታቸውም ምክንያት ስናደርገው ቆይተናል። በእርግጥ የተገለፁት አይነት ባህሪያት የብዙዎቹ መገለጫ መሆናቸው አያጠያይቅም። ግን ሁሉም ተጨዋቾች እንደዚያ ናቸው? በጭራሽ አይደሉም። በተሻሉ እና ራሳቸውን ከፍ ሊያደርጉበት፣ ብሔራዊ ቡድኑንም ሊጠቅሙበት በሚያግዟቸው ሊጎች መጫወት አለመቻላቸውስ የእራሳቸው ድክመት ብቻ ነው? በፍፁም አይደለም።
አንድ ኢትዮጵያዊ እግር ኳስ ተጨዋች የፈለገ ድንቅ ተሰጥኦ ቢታደል፣ ትልቅ ደረጃ የመድረስ ህልም ቢኖረው፣ ሙያውን አክባሪ እና የተሰጠ ፕሮፌሽናል ቢሆን ወይም በቀላሉ በትልቅ ደረጃ ለመጫወት የሚያስፈልጉ ሁሉንም ቅንጣቶችን ቢያሟላ እንኳ ህልሙን ማሳካት ‘የማይቻል’ ባይሆን እንኳ እጅግ አዳጋች ነው።
ለዚህ ዋነኛ ምክንያቶቹ exposure ማጣት እና networking አለመኖር ናቸው። ከአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት አንፃር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከአውሮፓ እግር ኳስ እና ሊጎች ጋር ያለው ትስስር እጅግ ደካማ ነው። የለውም ቢባልም ያስኬዳል። ከሌሎች ተነጥሎ የቆመ ‘ደሴት’ም ይመስላል። ለምን የሚለውን ለመመለስ ጥናት ቢያሻውም ከላይ የሚታዩ ጉልህ ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል።
ከነዚህ ዋነኛው ሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ከአውሮፓዊያኑ ጋር ያላቸው ፖሊቲካዊ እና ማህበራዊ ትስስሮች ለኢትዮጵያ አለመስራታቸው ነው። ለምሳሌ እንደእነኮት-ዲቩዋ፣ ሴኔጋል እና ማሊ ያሉ በፈረንሳይ ቅኝ የተገዙ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት ለአውሮፓ በተለይም ለፈረንሳይ ሊጎች በገፍ ተጨዋቾችን የሚያቀርቡ አካዳሚዎች አሏቸው። እነጋና እና ናይጄሪያ በፈረንሳይ ባይገዙም ተቀራራቢ ኔትዎርክ ፈጥረዋል።
አብዛኞቹ አካዳሚዎች በአውሮፓዊያኑ (በተለይም በፈረንሳዊያን) የሚደገፉ እና ከአውሮፓ ክለቦች ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸው ናቸው። ወደሰሜን አፍሪካ ስናማትር ደግሞ በአውሮፓ ሀገራት በተለይም ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድስ እና ስፔን የመሰረቷቸውን ትልልቅ ኮሚኒቲዎች እናገኛለን። አልጄሪያ በቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ግዙፍ ኮሚኒቲ አላት። በፈረንሳይ አድገው ለእድሜ ቡድኖች ተጫውተው ለዋናው ብሔራዊ ቡድን ያልተጠሩ ተጨዋቾች ለአልጄሪያ ይጫወታሉ (በ2014 ዓለም ዋንጫ ያስደመመው ቡድን 23 አባላት 19 ገደማ በፈረንሳይ ተወልደው ያደጉ ነበሩ)።
ሞሮኮ በበኩሏ በፈረንሳይ፣ ስፔን እና ኔዘርላንድስ ትልልቅ ኮሚኒቲዎች አሏት። እዚያ ያደጉትን ታጫውታለች። ከነዚያ ሀገራት ሊጎች ጋር ባላት ትስስርም ሀገር-በቀል ተጨዋቾች በቀላሉ ወደአውሮፓ ይሻገራሉ። የአንጎላ እና ኬፕ ቬርዴ ከቅኝ ገዢያቸው ፖርቱጋል ሊጎች ጋር ያላቸው የቀረበ ግንኙነትም ይታወቃል። የኢኳቶሪያል ጊኒ እና ስፔንም እንደዚያው። ለእንግሊዝኛ ተናጋሪዎቹ ደቡብ አፍሪካዊያን የብሪታኒያ ሊጎች ቅርብ ናቸው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በትልልቅ ውድድሮች ላይ አለመገኘት እንዲሁም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ደካማ መሆን እና የአፍሪካ ውድድር ተሳታፊ ክለቦች ረዥም ርቀት አለመጓዛቸውም ተጨዋቾች በዓለምአቀፍ የቴሌቪዥን ስርጭቶች የመታየትን እና የመልማዮችን ቀልብ የመሳብ እድላቸውን አሳጥተዋቸዋል። ለውጪ ሀገር ሰዎች ኢትዮጵያ የሩጫ እና ሯጮች እንጂ የእግር ኳስ ሀገር አይደለችም። እናም ለዚች ሀገር እግር ኳስ እና ተጨዋቾች ትኩረት መስጠትን አያስቡትም። ታዲያ በይት በኩል ተጨዋቾቻችን ይታዩ?
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን ማግኘቱ በትንሹም ቢሆን ለተጨዋቾች exposure (የመታየት እድል) ሰጥቷቸው ነበር። ወደተሻሉ የአፍሪካ ሊጎች በተለይም ወደደቡብ አፍሪካ ሄዶ ከዚያ ወደአውሮፓ መሻገር የተሻለው አማራጭ ይመስል ነበር። ግን እምብዛም አልሰራም።
ወደመነሻዬ ልመለስና በምርጥ አቋማቸው ወቅት የመታየት እድል ቢያገኙ እና ጥሩ ኔትዎርኪንግ ቢኖር በአምስቱ ትልልቅ ሊጎች አልያም ቀጥሎ በሚገኙት በሆላንድ፣ ፖርቱጋል፣ ቤልጂየም፣ ቱርኪዬ አልያም ለትልልቆቹ ሊጎች አቅራቢ በሆኑት የስካንዴኒቪያ እና የምስራቅ አውሮፓ ሀገራት ሊጎች መጫወት ይችሉ የነበሩ ተጨዋቾች እንደነበሩን/እንዳሉን አምናለሁ። ከሚሌኒየሙ ወዲህ ከተጫወቱት መካከል እነዚህን ላንሳ: (ማስታወሻ: የተጫዋቾቹን በአውሮፓ ሊያጫውቷቸው የሚችሉ ዋነኛ ኳሊቲዎችን ብቻ አነሳለሁ። የሜዳም ሆኑ የሜዳ ውጪ ድክመቶቻቸውን ሊያሻሽሉት ይችሉ እንደነበር ገምተን እንለፋቸው)
– ሰልሀዲን ሰዒድ: ለዘመናዊ እግር ኳስ የሚሆን ፍጥነት፣ ጊዜ አጠባበቅ እና አጨራረስ
– ጌታነህ ከበደ: የላቀ የ’9′ ቁጥር ደመ-ነፍስ፣ ቦታ አያያዝ እና አጨራረስ
– አዳነ ግርማ: ድንቅ ሁለገብነት፣ power እና የተለየ ራስ-መተማመን
– አቡበከር ናስር: ሁሉንም ቅንጣቶች (ድሪብሊንግ፣ የአንድ ለአንድ ልህቀት፣ ሙልጭልጭነት፣ ድንቅ የመጨረስ ብቃት…)አዋህዶ የያዘ ዘመናዊ አጥቂ
– ዳዊት እስጢፋኖስ: አቻ የሌለው እይታ እና ኳስ የማቀበል ብቃት
– አስቻለው ታመነ: ሁሉንም ያሟላ የመሀል ተከላካይ
– መስዑድ መሀመድ: Game intelligence (የታክቲክ መረዳት፣ ጨዋታ ማንበብ፣ ውሳኔ…)
– እና ‘የባከነው’ ሚኪያስ መኮንን: በተፈጥሮ የታደለ፣ ምንም ነገር ማድረግ ይችል የነበረ ፈጣሪ አማካይ/የክንፍ አጥቂ
* በሁለተኛ ደረጃ ሊነሱ የሚገባቸው: ሽመልስ በቀለ፣ ታፈሰ ሰሎሞን፣ አቤል ያለው፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ደጉ ደበበ…