በረከት ፀጋዬ
ምድብ ሁለት
ሴኔጋል፣ ጊኒ፣ ዚምባቡዌ፣ ማላዊ
ሴኔጋል
- ተሳትፎ፡ 16ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት፡ የፍፃሜ ተፋላሚ (2002፣ 2019)
- አሰልጣኝ፡ አሊዩ ሲሴ
- ኮከብ ተጨዋች፡ ሳይዶ ማኔ

- ምን ይጠብቃሉ፡ የቴራንጋ አንበሶቹ አሁንም የውድድሩ ከፍተኛ ተገማች ሆነው ካሜሩን ደርሰዋል። ለዚህም በቂ ምክንያት ያለ ይመስላል- ምንም ጨዋታ ሳይሸነፉ ማጣሪያውን ማለፋቸው እና ያሏቸው ተጨዋቾች ጥራት ይጠቀሳል። 2019 በፍፃሜው በአልጄሪያ ቢረቱም ዘንድሮ ይህን መቀየር በእጅጉ ይፈልጋሉ።
የቡድኑ ኮከብ ሳይዶ ማኔ ከቅርብ ወራት ወዲህ ግብ ማስቆጠር አለመቻሉ ቢያስተቸውም ወደ አፍሪካ ዋንጫው ከመምጣቱ በፊት ቼልሲ ላይ ግብ በማግባት ተቺዎቹን ዝም አሰኝቷል። እንደ ኤድዋርዶ ሜንዲ፣ ኢድሪሳ ጉዬ እና ካሊዱ ኩሊባሊ የመሳሰሉ ሌሎች ኮከቦች በቡድኑ ውስጥ መኖራቸው የአፍሪካን ብቻ ሳይሆን ከዛም በጥራታቸው ላቅ ያሉ ቡድኖችን መገዳደር የሚያስችል ቁመና እንዳላቸው ያሳያል።
አንዳንዶች ቡድኑ ያለውን የስኳድ ጥልቀት አናሳነት በመጥቀስ ምናልባትም ፈተና ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ። በቀድሞ ተጫዋቻቸው አሊዩ ሲሴ መሪነት ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ያገኙት ሴኔጋሎች ከዋንጫው ውጪ የሚያስመዘግቡት ምንም አይነት ውጤት እንደ ውድቀት ሊታይ ይችላል።
በቅርቡም የአሰልጣኛቸውን ኮንትራት እስከ 2022 ክታር አለም ዋንጫ ማራዘማቸው በእርሱ ላይ ያላቸው እምነት ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል። የወቅቱ የፊፋ ሃገራት ደረጃ የአህጉሪቱ ቁንጮ ሴኔጋል ሻምፒዮን ለመሆን በማለም ውድድራቸውን ከዚምባቡዌ ጋር በማድረግ ይጀምራሉ።
ጊኒ
- ተሳትፎ፡ 13ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት፡ የፍፃሜ ተፋላሚ (1976)
- አሰልጣኝ፡ ካባ ዲያዋራ
- ኮከብ ተጨዋች፡ ናቢ ኬይታ

ምን ይጠብቃሉ፡ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ሽንፈት ተከትሎ የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ ካባ ዲያዋራን ሾመዋል። ምክትል አሰልጣኝ ሆነው የቆዩት ዲያዋራ ከዋና አሰልጣኝነት ዕድገታቸው መልስ ያን ያህል ለውጥ አላመጡም ተብለው ከትችት አላመለጡም።
ከመጋቢት ወር አንስቶ ምንም ጨዋታ ያላሸነፉ ሲሆን እንደ ጥንካሬ የሚነሳላቸው ብቸኛ ነገርም የመሃል ክፍሉ በጥራታቸው ላቅ ባሉ ተጫዋቾች መዋቀሩ ብቻ ነው። አማዱ ዲያዋራ (ሮማ)፣ ሜዲ ካማራ (ኦሎምፒያኮስ) እና ናቢ ኬይታ (ሊቨርፑል) የጊኒ መሃል ክፍል ሞተሮች ናቸው። የምዕራብ አፍሪካዋ ሃገር የእግር ኳስ አመራሮች መሃል የሰላም አየር አለመንፈሱ እና የፊፋ ጣልቃ ገብነትን ማስከተሉ ምናልባት በቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ያሰጋል።
የዲያዋራ ሌላው ፈተና የሚሆነው ቡድኑ የግብ ዕድሎችን እንዲፈጥር ማስቻል ይሆናል። ያለፈውን አፍሪካ ዋንጫ ጥሎ ማለፍ ተቀላቅለው የነበረ ቢሆንም በአልጄሪያ ተረተው ተሰናብተዋል። ከምድቡ ተፎካካሪዎቻቸው በአንፃራዊነት የተሻለ ነገር ማሳየት ይችላሉ በሚል ግምት ሴኔጋልን ተከትለው የማለፍ ዕድል ብዙዎች ይሰጧቸዋል።
ዚምባቡዌ
- ተሳትፎ፡ 5ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት፡ ምድብ ማጣሪያ (2004፣ 06፣ 17፣19)
- አሰልጣኝ፡ ኖርማን ማፔዛ
- ኮከብ ተጨዋች፡ ኖውሌጅ ሙሶና

ምን ይጠብቃሉ፡ የኢንተርናሽናል እግድ ስጋትን ከፊት ለፊታቸው አስቀምጠው አፍሪካ ዋንጫውን ይከፍታሉ። የሃገሪቱ እግር ኳስ አስተዳደር ያለበት ቀውስ (በቅርቡ ከአለም አቀፉ እግር ኳስ አስተዳዳሪ ፊፋ እገዳ ተጥሎበታል) እና የቅርብ ጊዜ የአሰልጣኝ ሹመታቸው እውቅና አለማግኘቱ በራሱ ቡድኑን እንደሚጎዳው ይገመታል።
ማርቭለስ ናካምባ (አስቶንቪላ)፣ ብሬንዳን ጋሎዌይ (ፕሌይማውዝ)፣ ማርሻል ሙኔትሲ (ሬሚስ) በጉዳት ከቡድኑ ውጪ የሆኑ ቁልፍ ተጫዋቾች ናቸው። ሌላው ኮከብ ካማ ቢላት በህዳር ወር ራሱን ከኢንተርናሽናል ውድድሮች ማግለሉን ተከትሎ አምበሉ ኖውሌጅ ሙሶና እና ጓደኞቹ ትከሻ ላይ ብዙ ሃላፊነት ይወድቃል።
ካለፉት 18 ጨዋታዎች አንድ ብቻ ያሸነፉ ሲሆን እርሱም ከሜዳቸው ውጪ ቦትስዋናን የረቱበትና የአፍሪካ ዋንጫውን ትኬት መቁረጥ የቻሉበት ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ያሸነፉት ጋናን 2006 ዓ.ም 2-1 የረቱበት ሲሆን ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ውድድሮች አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ ከምድብ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል። ወቅታዊ አቋማቸውን ከግምት በማስገባት ‘ዘ ዋሪየርስ’ ሌላ ከባድ የአፍሪካ ዋንጫ ጊዜን እንደሚያሳልፉ ይገመታል።
ማላዊ
- ተሳትፎ፡ 3ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት፡ ምድብ ማጣሪያ (1984፣2010)
- አሰልጣኝ፡ ማሪዮ ማሪኒካ
- ኮከብ ተጨዋች: ጆን ባንዳ

ምን ይጠብቃሉ፡ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ አህጉሪቱ የእግር ኳስ ድግስ ብቅ ያሉት እሳቶቹ ከቀደሙት ሁለት ውድድሮች የምድብ ማጣሪያ ስንብት የተሻለ ነገርን ማሳየት ያልማሉ። በአለም ዋንጫ ማጣሪያ ከስድስት ጨዋታዎች አንድ ብቻ ማሸነፋቸው አሰልጣኛቸው የነበሩትን ሜክ ምዋሴን ወደ ምክትልነት እንዲወርዱና ሮማኒያዊው ማሪኒካ ወደ አሰልጣኝነት እንዲመጡ አስገድዷቸዋል።
እኚህ ሮማኒያዊ በቴክኒካል መሪነት ቡድኑን እንዲያሰለጥኑና በአፍሪካ ዋንጫው የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አደራ ተሰጥቷቸው ስራቸውን ጀምረዋል። እርሳቸው እንደ ዚምባቡዌና ጊኒን የመሳሰሉ ቡድኖችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያምናሉ። ” ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን ውጤቱ መጥፎ ሊሆን ይችላል፤ ስለዚህ ይህ እንዲከሰት አንፈልግም” በማለት ባለው አጭር ተሳትፎ ቡድኑን ለማሻሻል እንደሚጥሩ ይናገራሉ። አንድ ጨዋታ ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ ሳይጠበቁ ጥሩ ሶስተኛ ሆነው ማለፍ የሚያስችላቸውን ዕድል ሊፈጥርላቸው እንደሚችል ይገመታል።
የጨዋታ መርሃ ግብሮች
ሰኞ ጥር 2/2014
- ሴኔጋል vs ዚምባቡዌ (ቀን 10፡00 ሰዓት)
- ማላዊ vs ጊኒ (ምሽት 1:00 ሰዓት)
አርብ ጥር 6/2014
- ሴኔጋል vs ጊኒ (ቀን 10፡00 ሰዓት)
- ዚምባቡዌ vs ማላዊ (ምሽት 1:00 ሰዓት)
ማክሰኞ ጥር 10/2014
- ማላዊ vs ሴኔጋል (ምሽት 1:00 ሰዓት)
- ጊኒ vs ዚምባቡዌ (ምሽት 1:00 ሰዓት)
ምንጮች፡
- ጎል አፍሪካ ድህረ ገፅ www.goalafrica.com
- ዩሮስፖርት ድህረ ገፅ www.eurosport.com/AfricanCupOfNations
- BBC ስፖርት www.bbc.com