በረከት ፀጋዬ
ምድብ አራት
ግብፅ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ጊኒ ቢሳው
- ተሳትፎ፡ 25ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት: ሻምፒዮን (1957፣59፣86፣98፣2006፣08፣10)
- አሰልጣኝ፡ ካርሎስ ኬሮዥ
- ኮከብ ተጫዋች፡ ሞሃመድ ሳላህ

ምን ይጠብቃሉ፡ ግብፅ የአፍሪካ ዋንጫ የምንጊዜውም ውጤታማ ቡድን ከመሆኗ በላይ የማይሞከረው የሶስት ተከታታይ ጊዜ አሸናፊነት ሪከርድም ባለቤት ናት። በዚህ ሁሉ ክብር ያጌጡት ግብፃውያን ዘንድሮ ተፎካካሪ የመሆናቸው ጉዳይ ያጠራጥራል። ከሁለት አመት በፊት ለስምንተኛ ጊዜ ሻምፒዮን የመሆን ዕድላቸውን በገዛ ሃገራቸው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
በደቡብ አፍሪካ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ተሸንፈው ተሰናብተዋል። በወቅቱ የብ/ቡድኑ አቋም በእጅጉ የወረደ ነበር በማለት ከደጋፊዎች የሰላ ትችትም አስተናግደው ነበር። የወቅቱ አሰልጣኛቸው ካርሎስ ኬሮዥ የቡድኑን ማንነት መልሰውታል ሲሉ የሚያደንቋቸው አልጠፉም።
ይህም በቅርብ በካታር በተካሄደው የአረብ ሃገራት ዋንጫ ላይ አለወሳኝ ተጨዋቾቻቸው እስከ ግማሽ ፍፃሜ ድረስ መጓዛቸው ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል። ፖርቹጋላዊው የባለ ብዙ ልምድ አሰልጣኝ እንደ ሞ ሳላህ፣ መሃመድ ኤልኔኒ እና ሞስጠፋ መሃመድን የመሳሰሉ ቁልፍ ተጫዋቾቻቸውን ሲያገኙ ቡድኑን የበለጠ ጠንካራ እንደሚያደርጉት ታምኖበታል።
በወረቀት ላይ ፈርኦኖቹ ከአፍሪካ ሻምፒዮኗ አልጄሪያ፣ ከአፍሪካ ቁጥር አንዷ ሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒዝያ እና አስተናጋጇ ካሜሩን በልጠው ጥር 29 ዋንጫውን ለማንሳት የበረታ ፉክክር ይጠብቃቸዋል። ሆኖም ዋንጫውን ከማሸነፍ ውጪ የሚመዘገብ ማንኛውም ውጤት ለግብፅ እንደ ውድቀት ቢታይ አይገርምም። ለዚህም የኮከባቸውን መሃመድ ሳላህ በምርጥ ብቃት ላይ መገኘትን አጥብቀው ይሻሉ። በከባድ ሚዛኑ ፍልሚያ ግብፅ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ናይጄሪያን ‘በስታድ ኦምኒ ስፖርት ሮምዴ አጄ’ ጋሩዋ ከተማ ላይ በመግጠም የአፍሪካ ዋንጫውን ትጀምራለች።
ናይጄሪያ
- ተሳትፎ፡ 19ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት: ሻምፒዮን (1980፣94፣2013)
- አሰልጣኝ፡ ኦግስቲን ኢጉዌቬን (ጊዜያዊ አ)
- ኮከብ ተጫዋች፡ ኬሌቺ ኢሄናቾ
ምን ይጠብቃሉ፡ በብዙ ምስቅልቅል ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያደርጉትን ጉዞ የጀመሩት ሱፐር ኢግልስ የዚ ምስቅልቅል ዲዛይነር ራሳቸው ተደርገውም ተቆጥረዋል። ውድድሩ ሊጀምር የሳምንታት ዕድሜ ሲቀረው ጀርመናዊው አሰልጣኝ ገርኖት ሮር ተሰናብተው የቀድሞ አምበላቸው ኢጉዌቬን በጊዜያዊነት ተሹመዋል። ይህ ሹመት ለአሰልጣኙ ሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ከደጋፊው የከፋ ትችት ያስተናገደ ሹመት ነበር። የደጋፊውን ማጉረምረም ወደ ጎን ትተው የቡድን ስብስባቸውን ይፋ ያደረጉት ኦግስቲን ኢጉዌቬን ወደ ካሜሩን የሚያቀኑት ዋንጫውን ለማሸነፍ እንደሆነ ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደሙ የሚፋጀው ወንበር ስራቸው በአንዱ ማለትም በ2006 አፍሪካ ዋንጫ ቡድኑን ሶስተኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ የረዱት እኚሁ አሰልጣኝ ነበሩ። ቡድኑን ከአፍሪካ ዋንጫ በኃላ ለመረከብ የተሾሙት አዲሱ አሰልጣኝ ጆዜ ፔስዬሮ ተመልካች ሆነው ከቡድኑ ጋር እንደሚጓዙ ተዘግቧል። ውስጣዊ ችግሮቻቸውን በመብለጥ ወደ ጥሎማለፍ መቀላቀል የሱፐር ኢግልስ ተቀዳሚ እቅድ ይሆናል።
በጥሩ ብቃት ላይ ይገኙ የነበሩት አጥቂዎቻቸው ቪክቶር ኦሽሜን (ናፖሊ) እና ኢማኑኤል ዴኒስ (ዋትፎርድ) በጉዳት ከቡድን ስብስብ ወጪ መሆናቸው የፊት መስመራቸውን በእጅጉ ያሳሳዋል። ይሁን እንጂ እንደ ኬሌቺ ኢሄናቾ፣ ሳሙኤል ቹኩዌዜ እና ከኢንተርናሽናል ውድድር ራስን ማግለል መልስ እንደገና የቡድን ጥሪ የደረሰው አንጋፋው ኦዲን ኤጋሎ በፊት መስመር መኖራቸው ክፍተቱን ሊሸፍን እንደሚችል ይታመናል። ኤጋሎ የ2019ኙ የግብፁ አፍሪካ ዋንጫ በ5 ጎሎች ኮከብ ግብ አግቢ እንደነበር አይዘነጋም።
ከአጥቂዎች በተጨማሪ ዊልፍሬድ ኢንዲዲ በአማካይ ስፍራ የሚገኝ ሌላው ተጠባቂ ተጨዋች ነው። የግብ ጠባቂ እና የተከላካይ ክፍሉ መሳሳት ከአማካዮቹ ቀላልነት ጋር ተጨምሮ የፊት መስመሩን የሚመሩት ኢሄናቾ መቀዝቀዝ እንዲሁም በስፔን ለቪላሪያል የሚጫወተው ቹኩዌዜ ከረጅም ጉዳት መመለስ ጋር ተደምሮ የናይጄሪያን ጉዞ እንዳያሳጥረው ያሰጋል።
ሱዳን
- ተሳትፎ፡ 9ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት: ሻምፒዮን (1970)
- አሰልጣኝ፡ ቡርሃን ቲያ (ጊዜያዊ አ)
- ኮከብ ተጫዋች፡ ሞሃመድ አብዱልራህማን
ምን ይጠብቃሉ፡ ከአስር አመት በኃላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለተመለሱት ሱዳኖች ይህን ምድብ ማለፍ የማይቻል ሊመስል ይችላል። በማጣሪያው ደቡብ አፍሪካ በምትገኝበት ምድብ ጋናን ተከትለው ያለፉ ሲሆን በዚህ ሂደት ደ/አፍሪካን 2-0 የረቱበት ውጤት ቁልፍና ዋነኛው ነበር።
በአረብ ሃገራት ዋንጫ በግብፅ የደረሰባቸውን የሰፊ ጎል ሽንፈት ጨምሮ ሁሉንም የምድብ ጨዋታ በመሸነፋቸው አሰልጣኛቸው የነበሩት ሁበርት ቬሉድን አሰናብተዋል። በጊዜያዊነት የተሾሙት ቡርሃን ቲያ አንጋፋ ተጫዋቾችን በመሸኘት ቡድኑን እንደ አዲስ ለማዋቀር ጥረዋል።
ሌላው በዚሁ ምድብ አብራቸው የተደለደለችው ጊኒ ቢሳው ከዓመት በፊት በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ካርቱም ላይ 4-2 በሆነ ውጤት ያሸነፈችበት አጋጣሚ ለሱዳን እግር ኳስ በመጥፎነት ይጠቀሳል። ሱዳን የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መስራችና 1957 የመጀመሪያው አፍሪካ ዋንጫ አስተናጋጅ ሃገር ናት። የውድድሩ የአንድ ጊዜ ሻምፒዮን እና የሁለት ጊዜ ፍፃሜ ተፋላሚ የነበረች የኃላ ታሪኳ ደማቅ የነበረ ሃገር ናት። ታላላቆቹ ክለቦቿ አል ሂላል እና ሜሪክ በአህጉሩ የክለቦች ውድድር ላይ የተሻለ ጉዞን በማድረግ ይታወቃሉ።

ያልተጠበቁ ነገሮችን የሚያሳየው የሃገሪቱ የእግር ኳስ ጉዞ አሁን ላይ ካለፈው ክብር እና ከወቅቱ ስጋት ጋር በትግል ላይ ያለ ይመስላል። ‘ሚስጥራዊ ወፎቹ’ በሚጠበቁት ልክ ሆነው መገኘት ከብዶዋቸው ታይተዋል። በዚህ ውድድር የሱዳንን የትኛውን ፊት እንመለከተዋለን? ደማቁን ወይስ የደበዘዘውን? ካሜሩን ላይ የሚካሄደው ውድድር መልሱን ይነግረናል!
ጊኒ ቢሳው
- ተሳትፎ፡ 3ኛ ጊዜ
- ምርጥ ውጤት: የምድብ ማጣሪያ (2017፣19)
- አሰልጣኝ፡ ባሲሮ ካንዴ
- ኮከብ ተጫዋች፡ ሞሬቶ ካሳማ
ምን ይጠብቃሉ፡ ለሶስተኛ ተከታታይ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫው የቀረቡት ጊኒ ቢሳው አሁንስ ከምድብ ማጣሪያው ማለፍ ይችሉ ይሆን ሚለው ጥያቄ ይነሳል። በ2019 በጋናና ካሜሩን 2-0 ተሸንፈው ከቤኒን ጋር ያለ ምንም ግብ ተለያይተው ከምድብ ማጣሪያ ተሰናብተው ነበር። ያለፋትን አራት ተከታታይ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ግብ አለማስቆጠራቸው ቡድኑ በማጥቃት ረገድ ደካማ መሆኑን ያሳያል።

አሰልጣኙ በመከላከል ጊዜውን የሚያባክንና ግልፅ የጨዋታ እቅድ የሌለው ተብሎ ትችት ይሰነዘርባቸዋል። የቡድኑ ተጫዋቾች በአብዛኛው ፓርቹጋልና ፈረንሳይ ውስጥ በሁለተኛ ዲቪዝዮን የሚጫወቱ ናቸው። ሆኖም እንደ አማካዩ ሞሬቶ ካሳማ (ሬሚስ)፣ አልፋ ሴሜዶ (ቪክቶሪያ ጊዩማሬሽ)፣ እና አጥቂው ፒኩዌቲ ( አል ሾውላ, ሳዑዲ አረቢያ) የመሳሰሉ በትልቅ ደረጃ የሚጫወቱ ኮከቦችም አሏቸው።
በተለይ አጥቂው ፒኩዌቲ የጋቦን 2017 አፍሪካ ዋንጫ ካሜሩን ላይ ያስቆጠራት አስደናቂ ግብ ትታወሳለች። ከሴኔጋል ቀጥሎ ጊኒ ቢሳው በአፍሪካ ዋንጫው በቡድን ስብስቧ ውስጥ አንድም በአህጉሪቱ የሚጫወት ተጫዋች ያላካተተች ሃገር ናት። ከምድብ ማለፍ መቻል ‘ለጫካ ውሾቹ’ ትልቅ ውጤት ነው።
የጨዋታ መርሃ ግብሮች
ማክሰኞ ጥር 3/2014
- ናይጄሪያ vs ግብፅ (ምሽት 1፡00 ሰዓት)
- ሱዳን vs ጊኒ ቢሳው ( ምሽት 4፡00 ሰዓት)
ቅዳሜ ጥር 7/2014
- ናይጄሪያ vs ሱዳን (ምሽት 1፡00 ሰዓት)
- ግብፅ vs ጊኒ ቢሳው (ምሽት 4፡00 ሰዓት)
ረቡዕ ጥር 11/2014
- ጊኒ ቢሳው vs ናይጄሪያ (ምሽት 4፡00 ሰዓት)