
በልኡል ታደሰ
ሌላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጨዋታ። ሌላ አሳቃቂ ሽንፈት። የእግር ኳሳችንን ያልተደበቀ ገመና ዳግም ይፋ ያደረገ ሽንፈት። ተመሳሳይ ድክመት። የማይቀየር ማንነት። የተቀየረ ነገር ካለም ቡድኑ እና ሽንፈቶቹ ያገኙት ለመረሳት የቀረበ አነስተኛ ትኩረት ብቻ ነው።
እንደወርቃማ ጊዜ ልናነሳ ከምንችለው 1950ዎቹ እና 60ዎቹ ውጪ የኢትዮጵያ እግር ኳስ እና ብሄራዊ ቡድኑ ለግማሽ ክፍለዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ደካማ ነበር። በመካከል የነበሩ ስኬቶች ከብልጭ-ድርግም ያለፉ አልነበሩም። እንደጉድ የሚወራላቸው የ70ዎቹ፣ 80ዎቹ እና 90ዎቹ ከዋክብት ከሴካፋ ድሎች ያለፈ አልነበራቸውም። የማጣሪያ ውርደትም ልማዳቸው ነበር።
የሰሞኑ ሽንፈቶችም ካለፉት የተለየ አይደለም። ብሄራዊ ቡድኑ ካለፉት ዘጠኝ የፉክክር ጨዋታዎቹ አንዱን ብቻ አሸንፏል። የምድቡ የመጨረሻ ሆኖ ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር መውጣቱን አረጋግጧል። በዓለም ዋንጫ ማጣሪያም በምድቡ ጂቡቲን ብቻ በልጦ አምስተኛ ላይ ይገኛል።
ለእግር ኳሱ እና ብሄራዊ ቡድኑ መቀንጨር የሚነሱ ምክንያቶችም አልተቀየሩም – ቢያንስ የግል የስፖርት ጋዜጦች መታተም ከጀመሩበት 80ዎቹ አጋማሽ/መጨረሻ አንስቶ። አስተዳደር (ፌዴሬሽን፣ ሊግ፣ ክለቦች…)፣ የተሰጥኦ እድገት፣ ስልጠና፣ የተጨዋቾች ባህሪይ…
የሚያስገርመው በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ የሜዳ ድክመቶቻችን እና ከስንት-ጊዜ-አንዴ ብልጭ የሚለው ጥንካሬያችን ተመሳሳይ መሆኑም ነው። የመከላከል መደራጀት፣ የመከላከል ሽግግር፣ የቆሙ ኳሶችን መከላከል፣ በወሳኝ ጊዜያት ትኩረት ማጣት፣ የኳስ ቁጥጥርን ወደጎል እድሎች እና ወደአደጋዎች መለወጥ አለመቻል የማይታረሙ ችግሮቻችን ናቸው። ከኳስ ጋር ያለ ምቾት እና ማራኪ ቅብብል ብቻ በአንፃራዊነት የቡድኑ ጥንካሬ ናቸው።
ሆኖም የዚህ ዘመን ደካማነት ከቀደሙት (70ዎቹ፣ 80ዎቹ፣ 90ዎቹ እና 2000ዎቹ) የከፋ እንደሆነ ይሰማኛል። ለዚህ አንዱ ምክንያት የአፍሪካ እግር ኳስ ላለፉት 15 ዓመታት እየተቀራረበ መሆኑ፣ ቀድሞ እጅግ ደካማ የነበሩ ሀገራት ፍፁም ተሻሽለው ትልልቆቹን መፈተን መጀመራቸው፣ የእኛ ብሄራዊ ቡድን ግን ለዚህ አለመብቃቱ ነው።
ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኮሞሮስ፣ አንጎላ፣ ጋምቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ኬፕ ቬርዴ፣ ዩጋንዳ፣ ሞሪቴኒያ በተደጋጋሚ ኃያላኑን እየተገዳደሩ፣ በአፍሪካ ዋንጫ በተደጋጋሚ እየተሳተፉ ይገኛሉ። እንደሱዳን፣ ቤኒን፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዜኒያ፣ ቦትስዋና እና ዚምባቡዌ አይነቶቹም ዋሊያዎቹ በማይሳተፉበት ቀጣዩ አፍሪካ ዋንጫ ይወዳደራሉ። ቡድኑ ከ24 የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊዎች መካከል አለመገኘቱ እጅግ አሳዛኝ ነው። ከአፍሪካ ሁለተኛውን የህዝብ ብዛት የያዘች ለዚያውም ‘የወጣት ሀገር’ እና እግር ኳስ በተወዳጅነት ቀዳሚ የሆነባት ሀገር እዚህ ደረጃ ላይ መገኘቷ አስገራሚ ነው።
ለዚህ ውድቀት አንድ ወይም ጥቂት ወገኖችን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ ፍትሀዊ አይሆንም። ሜዳ ተገኝተው የሚጫወቱት ተጨዋቾች እና አሰልጣኞች ቀዳሚ ተወቃሽ ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ክለቦች፣ ሊጉ፣ ፌዴሬሽኑ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ወይም መንግስትም ከቀጥታ ተጠያቂነት አያመልጡም።
ከስፖርት ፖሊሲው ጀምሮ፣ የመሰረተ-ልማት፣ የዋናው ፌደሬሽን እና የክልል ፌዴሬሽኖች አመራርና አሰራር፣ የክለቦች አስተዳደር፣ የወጣቶች እድገት፣ የአሰልጣኞች ስልጠና እና እድገት፣ የአሰልጣኞች ለሙያው መሰጠት፣ ራስን ማብቃት እና ስነ-ምግባር እንዲሁም የተጨዋቾች ዲሲፕሊን እና ፕሮፌሽናሊዝም…እና ሌሎች ያልተጠቀሱ ጉዳዮች ሁሉ የውድቀታችን ምክንያት ናቸው።
አሳዛኙ እና ለተስፋ መቁረጥ የሚያቃርበን በተዘረዘሩት ሁሉ እጅግ ደካሞች መሆናችን ነው። ታዲያ እንዴት መሻሻል እና ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መገ’ንባትን ልንጠብቅ እንችላለን?!
ምናልባት እንደ 2004/05ቱ ቡድን አንድ ጥሩ ትውልድ ለጥቂት ዓመታት ሊያፎካክረን፣ የተሻሻልን ሊያስመስለን ይችላል። ግን በተጠና እና በተንሰላሰለ ስራ የመጣ ስላልሆነ ዘላቂ ሊሆን አይችልም። በእነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ላለፉት ዓመታት በጣም ብዙ ስለተባለ ከዚህ በላይ ማብራራት ረብ የለውም።