ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ሲዳማ ቡና የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት /ካስ/ የፅሁፍ ምልልስ የተረዳሁት ነገር ፌዴሬሽኑ የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን 20 ለማድረግ ያቀረበው ምክንያት ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት የሌለው መሆኑን ነው::
እንደምታስታውሱት ፌዴሬሽኑ ሊጉን ወደ 20 ክለቦች ለማሳደግ ያቀረበው ምክንያት በፕሪምየር ሊጉ የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴ ከተመረመሩት እና በኋላም ከተቀጡት አራት ክለቦች ውጭ ያሉት ክለቦች አለመመርመራቸውን እና በክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ መሰረት ከጥፋት ነፃ መሆናቸው አለመረጋገጡ ነው::

ምስል 1- የፌደሬሽን ምክንያት
ሲዳማ ቡና ለ”ካስ” ባስገባው መከራከሪያ ሌሎቹ ክለቦች አለመመርመራቸውን በምክንያት በማቅረብ ምርመራው በዘፈቀደ የተደረገ መሆኑን ይገልፃል:: በዚህም አራቱ ክለቦች ተለይተው መቀጣታቸው አድሏዊ እና ኢፍትሀዊ [የውድድር] ከባቢ በመፍጠር ሲዳማ ቡና እና ሌሎቹ ሶስት ክለቦች ተገቢ ያልሆነ ኢላማ እንዲሆኑ ተደርገዋል ይላል:: (ምርመራውን ያደረገው ፌዴሬሽኑ እንዳልሆነ ልብ ይሏል)


ፌዴሬሽኑ በምላሹ በክለቦች የክፍያ ስርዓት አስተዳደር መመሪያ መሰረት የፋይናንስ አሰራር ተቆጣጣሪ ኮሚቴው ክለቦችን በዘፈቀደ መርጦ የመመርመር መብት እንዳለው ገልፇል:: ስለዚህ ሲዳማ ቡና እና ሌሎች ሶስት ክለቦች ተለይተው መመርመራቸው እና መቀጣታቸው የህግ ጥሰት እንደሌለበት በፅሁፍ ተከራክሯል::

የእኔ ጥያቄ እዚህ ላይ ነው:: በፌዴሬሽኑ የህግ ምላሽ መሰረት የ14ቱ ክለቦች አለመመርመር ምንም አይነት የህግ ጥሰት ከሌለበት “ገና ለገና አጥፍተው ይሆናል: ነፃ አይሆኑም” በሚል የሊጉን ተሳታፊዎች ቁጥር ማሳደግ የህግ መሰረቱ ምንድን ነው? ክለቦቹ በእግር ኳሱ የፍትህ አካላት ጥፋተኛ እስኪባሉ ድረስ ነፃ መሆናቸውንስ አይቃረንም? ፌዴሬሽኑ ለ”ካስ” የህግ ጥሰት የለም እያለ በሀገር ውስጥ ውሳኔዎቹ ግን ስህተት እንዳለ የሚያሳይ ውሳኔ መወሰኑ አይቃረንም?







