
በዘንድሮው የውድድር ዘመን በአምስቱ ታላላቅ የአውሮፓ ሊጎች ከዚህ በፊት በግብ አስቆጣሪነታቸው የሚታወቁት ተጫዋቾች አሁንም ግብ ማምረታቸውን ቀጥለውበታል፡፡ እንደሀሪ ኬን ፤ አርሊንግ ሀላንድ እና ኪሊያን ምባፔ ያሉ ተጫዋቾች በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
እንደስፖርቲንግ ፔዲያ ዘገባ ከሆነ ደግሞ የሞናኮው የፊት መስመር ተጫዋች አንሱ ፋቲ በወጥነት እንደዚሁም እድሎችን በመጠቀም አንጻር በአውሮፓ ያሉትን ታላላቅ አጥቂዎች እንደሚበልጣቸው ቁጥራዊ መረጃዎችን አስደግፎ አቅርቧል፡፡
አንሱ ፋቲ በተሰለፈባቸው ሁሉም የሞናኮ ጨዋታዎች ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡ በ3 የሊግ ጨዋታዎች 5 ግቦች አሉት፡፡ ይህም በየ32 ደቂቃው ግቦችን እንደሚያስቆጥር ማሳያ ነው፡፡ ፋቲ ምንም እንኳን ለረጅም ጊዜ በጉዳት ርቆ የቆየ ቢሆንም ወዲያውኑ ወደግብ ማግባቱ መመለስ ችሏል፡፡ እንደአንሱ ፋቲ በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ግብ ማስቆጠር የቻለው ሀሪ ኬን ሲሆን በየ45 ደቂቃው ግብ እንደሚያስቆጥር ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሀላንድ ግቦችን በየ66 ደቂቃ የሚያስቆጥር ሲሆን ምባፔ በበኩሉ በየ72 ደቂቃው ግቦችን ያስቆጥራል፡፡
የአይንትራክት ፍራንክፈርቱ ወጣት ተጫዋች ካን ኡዙን በተሰለፈባቸው 80% ጨዋታዎች ግቦችን ማስቆጠር ችሏል፡፡
ሀላንድን የሚጠጋ ሪከርድ በፕሪሚየር ሊጉ ያለው የቦርንማውዙ አጥቂ አንትዎን ሴሜንዮ ሲሆን በተሰለፈባቸው 57% ጨዋታዎች ግቦችን አስቆጥሯል፡፡
