ሮናልዶ – የኦሌ ‹‹የታክቲክ ፈተና ››

(ከአትሌቲክ የተወሰደ)

በአቤል ጀቤሳ


ማንቸስተር ዩናይትድ በሌስተር ሲቲ 4 ለ 2 መሸነፉ ላይ ላዩን ሲያዩት እንግዳ ውጤት ይመስላል ፡፡ በአብዛኛው የጨዋታው ክፍለ ጊዜ 1ለ1 እንደነበሩ አትዘንጉ ፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በጨዋታው ሊያስቆጥሩ እንደሚችሉ ከተገመተው የጎል መጠን በላይ አስቆጥረዋል ፡፡ በጨዋታው ከተመዘገቡት ስድስት ጎሎች አራቱ በግጥሚያው የመጨረሻ 12 ደቂቃዎች የተገኙ መሆኑንም ልብ በሉ ፡፡ ሶስቱን ያስቆጠረው ሌስተር ነበር ፡፡

የግጥሚያው የመጨረሻ ደቂቃዎች ስትራቴጂ እና ታክቲክ ቸል የተባሉበት የጨዋታው አስደሳች ክፍል ሆኖ አልፏል ፡፡ በምትኩ ትርምስ እና ዕድል ጎልተው ታይተዋል ፡፡
በመጨረሻ ሌስተር አሳማኝ አሸናፊ ሆኗል ፡፡ የብሬንዳን ሮጀርስ ቡድን ያለ ኳስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የበለጠ ቅንጅት አሳይቷል ፡፡ ከኳስ ጋር የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችም ከዩናይትድ በተሻለ ዓላማ ነበራቸው ፡፡

የሌስተር እንቅስቃሴ በጨዋታው ሁለቱም ፈርጆች ከማንቸስተር ዩናይትድ በተሻለ ትስስር እና ፍሰት ነበረው ፡፡ ዩናይትድ የበለጠ በተጫዋቾች የግል ብቃት ላይ አተኩሯል ፡፡ የያዛቸውን ተጫዋቾች ጥራት በሚገልጽ መልኩ ግን ጠንካራ አልነበረም ፡፡


ዩናይትድ አሁን ለገጠመው ችግር ጎልቶ የሚጠቀሰው ችግር ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው ፡፡ 36 ዓመት ሆኖታል ፡፡ የዋንጫ ተፎካካሪዎቻቸውን የፊት መስመር የሚመሩ አጥቂዎች ያለመታከት ‹‹ፕሬስ›› የሚያደርጉ መሆናቸውን አስታውሱ ፡፡ ሮናልዶ ያለማቋረጥ ‹‹ፕሬስ›› በሚያደርግበት አካላዊ ብቃት ላይ አይገኝም ፡፡ ‹‹ፕሬስ›› የማድረግ ፍላጎት ያለውም አይመስልም ፡፡ የተጫዋቾችን የ‹‹ፕሬሲንግ›› አቅም በሚለኩ ቁጥራዊ መለኪያዎች ፖርቱጋላዊው ከመጨረሻዎቹ ተርታ መቀመጡ ብዙዎችን ያላስገረመው ለዚህ ይመስላል ፡፡


በ2021-22 የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ ከ270 ደቂቃዎች በላይ ከተጫወቱ 29 አጥቂዎች ሁሉ ‹‹ፕሬስ›› በማድረግ ዝቅተኛ ቁጥር ያስመዘገበው ሮናልዶ ነው ፡፡ በዝርዝሩ ቀዳሚውን ቦታ የያዙት እያንዳንዳቸው 20 ጊዜ ‹‹ፕሬስ›› ያደረጉት ዊልፍሬድ ዛሃ እና ኒል ሙፔ ናቸው ፡፡ ሮናልዶ 2.7 ብቻ መሆኑ ታይቷል ፡፡ የችግሩን ግዝፈት የሚያሳየው ተጨማሪ ማሳያ ዝቅተኛ ተሳትፎ በማድረግ ከሮናልዶ በመቀጠል ደካማ ሆኖ ከታየው የኒውካስል ዩናይትዱ አለን ሰን -ማክሲ(5.2) እንኳን በግማሽ ያነሰ ቁጥር ማስመዝገቡ ነው ፡፡


ማንቸስተር ዩናይትድ ሮናልዶን ሲያስፈርም ምን እንደሚጠብቀው ያውቃል ፡፡ ኳስን መልሶ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ብዙም እንደማያግዘው አልጠፋውም ፡፡ በየጨዋታው በአማካይ አንድ ጎል ገደማ ሊያስቆጥርለት እንደሚችል ታሳቢ አድርጓል ፡፡ ሮናልዶ ከእርሱ የሚጠበቀውን ከሞላ ጎደል ፈጽሟል ፡፡ በአማካይ በ111 ደቂቃ አንድ ጎል አስቆጥሯል ፡፡ አንዳቸውም ከፍጹም ቅጣት ምት የተገኙ አይደሉም፡፡

አስቶንቪላን በገጠሙበት ጨዋታ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች የተገኘችውን የፍጹም ቅጣት ምት እርሱ መትቶ አስቆጥሮ ቢሆን በየጨዋታው በአማካይ አንድ ጎል እንዲያስቆጥር የተቀመጠለትን ግብ በሚገባ ያሟላ ነበር ፡፡

እርሱ የነበረበት የቀድሞው ማንቸስተር ዩናይትድ ፣ ሪያል ማድሪድ ፣ ጁቬንቱስ እና ፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድኖች በተለያየ መጠንም ቢሆን የተዋቀሩት የእርሱን ጉድለት መሸፈን በሚያስችል መንገድ እንደነበር አስታውሱ ፡፡

በግራ መስመር ተሰልፎ ከተጫወተ በተቃራኒ መስመር የተሰለፈው የመስመር ተጫዋች የበለጠ ወደ ወደ መሃል ይሳባል ፡፡ በፊት መስመር ከተጫወተ የመስመር ተጫዋቾቹ አሊያም 10 ቁጥር ተጫዋቹ ከተለመደው ጊዜ የበለጠ ወደ ኋላ በጥልቀት ተስበው ይጫወታሉ ፡፡ ሮናልዶ ሲለቅቅ ሌሎች (ዌይን ሩኒ ፣ ካሪም ቤንዜማ) የቡድኑ ቀዳሚዎቹ የጎል ምንጮች እንዲሆኑ ስለሚደረግ ደረጃቸው ከፍ ብሎ ታይቷል ፡፡


ማንቸስተር የእርሱን ጉድለት ስኬታማ በሆነ መንገድ መሸፈን አልቻለም ፡፡ ቡድኑ ያለ ኳስ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውሉ ጠፍቶት ታይቷል ፡፡ ወደ ኋላ በመመለስ ጥቅጥቅ ያለ ቅርጽ አይኖረውም አሊያም ፕሬስ አያደርግም ፡፡ ተጋጣሚዎቹ በቀላሉ ኳሶችን ማንሸራሸር እና ወደ ጎል መቅረብ እንዲችሉ አድርጓቸዋል ፡፡


ሌይስተርን በገጠመበት ጨዋታ ዩናይትድ በሚያፈገፍግባቸው አጋጣሚዎች ምን እንደተፈጠረ እንመልከት …..


በምስሉ ላይ በቀስት እንደተመላከተው ሌስተር በዘጠነኛው ደቂቃ በማንቸስተር ዩናይትድ አማካይ ክፍል ነጻ ሆኖ ለተገኘ ተጫዋች ያደረጋቸውን ፓሶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከተ (በዚህኛው አጋጣሚ ቡባካሪ ሱማሬ መሃል ለመሃል ለኬሌቺ ኢሄናቾ ያቀበለው ኳስ ) የጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማሳያ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል ፡፡ (ምስል 1 ይመልከቱ)

ምስል 1

በጨዋታው 38ኛ ደቂቃ ላይ ዩሪ ቲዬለማንስ ተመሳሳይ ኳስ ለጀምስ ማዲሰን ሲያቀብለው ግን ሁለቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ሆልዲንግ አማካዮች ኔማኒያ ማቲች እና ፖል ፖግባ በትክክለኛው ቦታ ላይ ስለመገኘታቸው መጠየቃችሁ አይቀርም ፡፡ (ምስል 2 ይመልከቱ)

ምስል 2

ሶስተኛው አጋጣሚ ማዲሰን ለቲዬልማንስ ያቀበለው ነው ፡፡ የመስመር ተጫዋቾቹን አቋቋም ልብ ብላችሁ ተመልከቱ ፡፡ ፕሬስ ሊያደርጉ በሚችሉበት ቦታ ላይ እንደሆኑ ሊታሰብ ይችላል ፡፡ ቡድኑ ግን ኳስ የያዘውን ተጫዋች ምንም ዓይነት ጫና ሳያሳርፍበት ነጻ ሆኖ ከኳስ ጋር የሚያሳልፈው በቂ ጊዜ ፈቅዶለታል ፡፡ ይህን ጊዜ ለማቲች እና ፖግባ ማዘን ትጀምራላችሁ ፡፡ ሰፊውን የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት ብቻቸውን እንዲሸፍኑ ተገድደዋል ፡፡ (ምስል 3 ይመልከቱ)

ምስል 3

ቲዬለማንስ ኳሷን ተቀብሎ ሲዞር በአማካይ እና ተከላካይ ክፍሉ መካከል ሰፊ ክፍተት መኖሩን ትገነዘባላችሁ ፡፡ ማቲች እና ፖግባ የሜዳውን የጎንዮሽ ስፋት ብቻ ሳይሆን ቁመት ጭምር እንዲያካልሉ ይጠበቅባቸዋል ፡፡ (ምስል 4 ይመልከቱ)

ምስል 4

ዩናይትድ ፕሬስ ሲያደርግ የሚሆነውን እንመልከት …


ሮናልዶ በዚህ አጋጣሚ ፕሬስ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ ግልጽ አይደለም ፡፡ ወደ ኋላው ዞሮ ሜሰን ግሪንዉድ ወደፊት ተጠግቶ ካግላር ሶዩንቹ ነጻ እንዳይሆን እንዲያደርግ ምልክት እየሰጠው ነው ፡፡ (ምስል 5 ይመልከቱ)

ምስል 5

ግሪንዉድ እንደተባለው አደረገ ፡፡ ፕሬስ ለማድረግ የሞከረበት መንገድ ግን ታክቲካዊ መሰረት አልነበረውም ፡፡ ሩጫው ሶዩንቹ ፓስ የሚያደርግበት አማራጭ እንዲያጣ አላደረገውም ፡፡ የበለጠ የተቀናጀ ቡድን ውስጥ ቢሆን ኖሮ የሌይስተሩ የግራ መስመር ዊንግ ባክ ቲሞቲ ካስታኛ ኳሷን መቀበል እንዳይችል ለመጋረድ ሩጫውን ቀጥተኛ ከማረግ ይልቅ በግማሽ ክብ ቅርጽ ባደረገው ነበር ፡፡ እርሱ ግን በቀጥታ ወደ ሶዩንቹ ሮጠ …(ምስል 6 ይመልከቱ)

ምስል 6

…ይህም ተከላካዩ በቀላሉ ዞሮ ለካስታኛ ቀላል ፓስ እንዲያደርግ ዕድሉን ፈጠረለት ፡፡ የመጀመሪያውን የፕሬሲንግ እንቅስቃሴ ለማገዝ የሞከረ ሌላ የዩናይትድ ተጫዋች አልነበረም … (ምስል 7 ይመልከቱ)

ምስል 7

…ካስታኝ ከፊት ለፊቱ ወዳገኘው ክፍት ቦታ ኳሷን አእየገፋ ሄደ ፡፡ ሮናልዶ ይህን ጊዜ ወደ ኋላ ተመልሶ ክፍተቱን መዝጋት እንዳለበት ተሰማው ፡፡ ካስታኝ በቀላሉ መሃል ሜዳ ላይ ነጻ ሆኖ ለተገኘው አማካይ ኳሷን ፓስ አደረገ ፡፡ ሌይስተር ከመሃል ሜዳ የማጥቃት እንቅስቃሴውን መመስረት ቻለ ፡፡ የዩናይትድ ‹‹ፕሬሲንግ›› ለመሰበር የዚህን ያህል የቀለለ ሆኖ ታየ ፡፡ (ምስል 8 ይመልከቱ)

ምስል 8

ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መንገድ የሌስተሩ አጥቂ የፕሬሲንግ እንቅስቃሴውን ሲያስጀምር አጠቃላይ ቡድኑ አገዘው ፡፡ ቲዬለማንስ ያስቆጠራት የሌስተር ድንቅ ጎል የተገኘችው ዴቪድ ዴሄያ ለመሃል ተከላካዮ ሃሪ ማጓዬር ያደረገውን ፓስ ኢሄናቾ ቆርጦ በማስቀረቱ ነው ፡፡ ምናልባት ይህኛው ጽንፍ የረገጠ ምሳሌ ሊሆን ይችላል፡፡ የሌስተርን አቀራረብ በሚገባ የሚገልጽ አጋጣሚ መሆኑ ግን እርግጥ ነው ፡፡
ይህኛውን አጋጣሚ ልብ በሉ ፡፡ ጄሚ ቫርዲ ወደ ቪክቶር ሊንደሎፍ ሲንቀሳቀስ አምስት ተጫዋቾችን ያሳተፈ የፕሬሲንግ እንቅስቃሴ አስጀመረ ፡፡ በሌስተር ቡድን የግራ አጋማሽ የነበሩ አምስቱም ተጫዋቾች ተንቀሳቀሱ … (ምስል 9 ይመልከቱ)

ምስል 9

…ብሩኖ ፈርናንዴዝ ያደረገውን አሳማኝ ያልሆነ ፓስ ቆርጦ ያስቀረው አምስተኛው ተጫዋች ሶዩንቹ ነው ፡፡ (ምስል 10 ይመልከቱ)

ምስል 10

ቡድኑ ከኳስ ውጪ የያዘው ቅርጽ ከአንድ የፕሪምየር ሊግ ቡድን አይጠበቅም ፡፡ የዩናይትድ 4-2-3-1 ቅርጽ ብዙውን ጊዜ የበለጠ 4-2-4 መስሎ ይታያል ፡፡ ቀጥሎ ባለው ምስል እንደሚታየው ጄደን ሳንቾ ፕሬስ ለማድረግ ሲሞክር አማካይ ክፍሉ ቅርጹን አጥቶ ይስተዋላል ፡፡ በመካከላቸው ኳስ መቀባበልም ቀላል ሆኗል ፡፡ በተጫዋቾች መካከል ብዙ ክፍተቶች ይታያሉ ፡፡ (ምስል 11 ይመልከቱ)

ምስል 11

ከሌስተር ሲቲ ቅርጽ ጋር ዩናይትድን ማነጻጸር ስሜት አይሰጥም ፡፡ የተጠቀመው 3-4-1-2 ፎርሜሽን ነው ፡፡ በእያንዳንዱ ዲፓርትመንት ቅንጅት አለ ፡፡ በዲፓርትመንቶቹ መካከል ደግሞ ስኬታማ ትስስር ታይቷል ፡፡ የተከላካይ እና የአማካይ ክፍሉ ምን ያህል ተጠጋግተው እንደሚጫወቱ ልብ በሉ ፡፡ (ምስል 12 ይመልከቱ

ምስል 12

ተጫዋቾችን በተናጥል ከተመለከትን ዩናይትድ በመጀመሪያ አሰላለፍ የተጠቀመባቸው አስራ አንድ ተጫዋቾች ድንቅ ናቸው ፡፡ የተዋጣለት ጥምረት መፍጠር እና ሚዛንን መጠበቅ ላይ ግን ደካማ ሆነው ታይተዋል ፡፡

ዩናይትድ ያለ ኳስ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ፈርናንዴዝ የሮናልዶን ድክመት ለማካካስ የበለጠ ሜዳ ያካልላል ፡፡ ፖርቱጋላዊው ይህንን የሚያደርገው ባለመታከት ስሜት ነው ፡፡ ሂደቱ ብዙ ጉልበት እንዲያወጣ አስገድዶታል ፡፡ እንቅስቃሴው ትኩረቱ እንዲቀንስ ስለሚያደርገው ኳስ እግሩ ስር ስትገባ ምን ማድረግ እንደሚኖርበት ለማወቅ ሲቸገርም ተስተውሏል ፡፡

ለዩናይትድ ከፈረመ ወዲህ ያሳየውን ድንቅ ብቃት ለተመለከተ ቡድኑ በእርሱ ዙሪያ ተገንብቶ ሊቀጥል እንደሚገባ አይጠፋውም ፡፡ የሮናልዶ መፈረም ሁኔታውን ለዋወጠው ፡፡ የዩናይትድ ምርጡ ተጫዋች ሚናም አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ ፡፡


ሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች የታክቲክ ዲሲፕሊን የሚያከብሩ ቢሆን አማካዩ ጠንካራ በሆነ እና ችግሮቹንም መቅረፍ በቻለ ነበር ፡፡ ሳንቾ ሲበዛ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚያተኩር የመስመር ተጫዋች ነው ፡፡ አጨዋወቱ ከአማካይነት ይልቅ ወደ አጥቂነት ያመዝናል ፡፡

በዶርትሙንድ ቡድኑ በህብረት ትስስር ባለው መልኩ ‹‹ፕሬስ›› የሚያደርገውን የዶርትሙንድ ቡድን ተለማምዷል ፡፡ አሁንም ድረስ የየዩናይትድን አማካዮች ከማገዝ ይልቅ የሚገኘው በእነዚያ ቦታዎች ላይ ነው ፡፡

በሌላኛው መስመር የሚጫወተው ሜሰን ግሪንዉድም በተመሳሳይ ማጥቃቱ ላይ የሚያተኩር ተጫዋች ነው ፡፡ ዩናይትድ በውድድር ዘመኑ ካደረጋቸው የመጀመሪያዎቹ ሶስት ጨዋታዎች በሁለቱ ጨዋታውን የጀመረው የፊት መስመር አጥቂ ሆኖ ነው ፡፡

በሁለቱም ጨዋታዎች ኳስ እና መረብ አገናኝቷል ፡፡ በውድድር ዘመኑ በዋነኝነት የሚጫወተው በዚያ ሚና እንደሚሆንም ታስቦ ነበር ፡፡ የሮናልዶ መምጣት ይህንንም ለውጦታል ፡፡ ከመስመር እየተነሳ ጎሎችን ሊያስቆጥር ቢችልም ከኳስ ውጪ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የፓርክ ጂ-ሱንግን ገድል እንዲደግም አይጠበቅም ፡፡


የቡድኑ የመሃል ሜዳ ችግር አዲስ ክስተት አይደለም ፡፡ ፖግማ በአማካይ ክፍል ከሌላ ተጫዋች ጋር ተጣምሮ ሲሰለፍ በመከላከሉ ረገድ ደካማ መሆኑ ይታወቃል ፡፡ ሶልሻዬር ይህንን በመገንዘብ እርሱን ከመስመር እየተነሳ እንዲጫወት ማድረግ ጀምሮ ታይቷል ፡፡ ፈረንሳዊው በዚያ ሚና የውድድር ዘመኑን በጥሩ መንገድ እንደጀመረ ታይቷል ፡፡

አሁን በአጥቂ ቦታ የሚሰለፈው ሮናልዶ ነው ፡፡ ግሪንዉድ ከመስመር እየተነሳ ለመጫወት ተገድዷል ፡፡ ይህም ፖግባ በድጋሜ ወደ መሃል ሜዳ እንዲመለስ አስገድዷል ፡፡ ስለሆነም የዩናይትድ የመሃል ሜዳ ችግር ምንጩ አሁንም የሮናልዶ መሰለፍ ይሆናል ፡፡


መፍትሄውን መጠቆም ቀላል አይደለም ፡፡ ሶልሻዬር በሪያል ማድሪድ የጋላክቲኮዎች ዘመን ከነበሩ አሰልጣኞች ጋር ተቀራራቢ ፈተና ገጥሞታል ፡፡ አንዳንድ ተጫዋቾችን በገናና ስማቸው ምክንያት ለማሰለፍ ተገድዷል ፡፡ ፈታኝ ታክቲካዊ ውሳኔዎችን ከማሳለፍ ተጫዋቾቹን አለማስቀየም መርጧል ፡፡

ሮናልዶ እና ፈርናንዴዝን ከአሰላለፍ ውጪ ማድረግ የማይቻል ይመስላል ፡፡ 73 ሚ.ፓ የወጣበትን ሳንቾ ሲያባክን መታየት አይፈልግም ፡፡ የግሪንዉድ ወቅታዊ ብቃት የመሰለፍ መብት ያሰጠዋል ፡፡ ፖግባ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ባማረ መልኩ ነው ፡፡ አምስቱ ግን አንድ ላይ መጫወት አይችሉም ፡፡

ኤቨርተንን በገጠሙበት ጨዋታ አንቶኒ ማርሲያል የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል ተሰጥቶት የዩናይትድን ብቸኛ ጎል አስቆጥሯል ፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ከተጠባባቂ ወንበር ተነስቶ ወደ ሜዳ የገባው ራሽፎርድ ያስቆጠራት ጎል ለአጭር ጊዜም ቢሆን ጨዋታውን 2ለ2 ማድረግ ችላለች ፡፡

ኦ …ኤዲንሰን ካቫኒን አስታወሳችሁት?


ሮናልዶ ኦልድ ትራፎርድ ከደረሰ በኋላ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ተገማች ነው ፡፡ ከኳስ ውጪ በሚደረግ እንቅስቃሴ የበለጠ ሊያበረክት ይገባል የሚለው ሃሳብ ያከራክራል ፡፡ የእርሱ መኖር ሶልሻዬር ላይፈታው የሚችል ታክቲካዊ እንቆቅልሽ መፍጠሩ ግን ግልጽ ነው ፡፡

(አቤል ጀቤሳ በኢትዮ ኤፍኤም የኢትዮ-ስፖርት አዘጋጅ እና አቅራቢ ነው)

Girmachew Kebede

Related Posts

አዲሱ የአሎንሶ አብዮት; የጨዋታ ቁጥጥር እና ከኳስ ውጪ የተጨዋቾች ሚና

ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች አውሮፓ ውስጥ ላሉ ታላላቅ ክለቦች እና አሰልጣኞቻቸው አዲስ ነገር አይደሉም:: በእግርኳስ ከፍ ባለው ልህቀት ደረጃ ላይ የደረሱ አሰልጣኞች ዋነኛ አላማቸው የጨዋታውን አካሄድ መቆጣጠር ነው:: ይህም ተጋጣሚን አጨዋወቱን…

በሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዙሪያ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ምን ይላል?

ከአራት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብን “የታገዱ ተጫዋቾችን በማሰለፍ” በሚል በኢትዮጵያ ዋንጫ ያገኘው ድል ተሰርዞ በፎርፌ እንዲሽነፍ እና የቀጣዩ የውድድር ዘመን የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ…

Leave a Reply

You Missed

St. George wins the City Cup 

St. George wins the City Cup 

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ

የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ