
ዳግማዊው ዝላታን ይሉታል። በትውልድ ሃገሩ ስዊድን ትልቅ ተስፋ የተጣለበት ወጣት ተጨዋች ነው። በዓለም እግርኳስም የወደፊቱ ኮከቦች ተብለው ከተተነበያለቸውም ተርታ ይሰለፋል።
ከኤርትራውያን ወላጆች በ ቲንሿ ሶልና ከተማ የተወለደው አሌክሳንደር ኢሳክ ፣ በ16 ዓመቱ ስዊድን ሊግ/ኦልስቬስካን/ በዕድሜ ቲንሹ ግብ አስቆጣሪ፣ በብሄራዊ ቡድንም በ 17 ዓመት 92 ቀናት በዕድሜ ቲንሹ ስዊድናዊ ግብ አስቆጣሪ ነው።
‘AIK’ ፣ ዶርትመንድ ፣ ዊሌም(ከዶርትመንድ በውሰት) ከዛም ሬያል ሶስዬዳድ እያለ የዘለቀው የኢሳክ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ህይወት አሁን ወደ ሰሜን ታይንሱ ኒውካስል አድርሶታል። በ60 ሚልየን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ ኒውካስል ዩናይትድን ተቀላቅሏል። ለቀጣይ 6 ዓመታትም የማግፓይሶቹን ጥቁር እና ነጭ መለያ ሊለብስ ተስማምቷል።
አሌክሳንደር ኢሳክ ቁመተ ረዥም ተጨዋች ነው። አንድ ሚትር ከ 90 ገደማ ቁመናውን ለተመለከተ ስለአጨዋወቱ በፍጥነት ሊደመድም ይችላል። እንደ ሌሎች ረዣዥም ተጨዋቾች የዓየር ላይ ኳስን አጥቂ ፣ ከፍጥነት ይልቅ ጥንካሬውን የሚጠቀም እና በቴክኒኩ እምብዛም የሆነ። ኢሳክ ግን ከእነዚህ ሁሉ የተለየ ነው። የመጀመርያ(touch) ፣ dribble እና ኳስን ተቀብሎ የመዞር ከዛም የማምለጥ ችሎታው የላቁ ቁጥሮች ካሏቸው ጎራ ያሰልፈዋል።

Smarterscout የተባለው የ ዳታ ቀማሪ ተቋም ምናልባትም ምርጡን የ እግርኳስ ዓመቱ የሆነውን 2020/21 ቁጥሮችን እንደሚከተለው ያስቀምጣቸዋል። ቁጥሮቹ በ 2000 የጨዋታ ደቂቃዎች የተወሰዱ ናቸው።
shot volume (ወደ ግብ ምት) : ይህ መለክያ አንድ ተጨዋች ከሚነካቸው ኳሶች መካከል ስንት መቶኛ ወደ ግብ የተመቱ እንደሆኑ ይጠቁማል። የኢሳክ 93% shot volume ከፕሪምየር ሊጉ ምርጥ ተጨዋቾች መካከል ያካትተዋል። በዚህ መለክያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተጨዋች ኬቭን ደ ብሩይነ 99% ነው።
Carry and dribble(ኳስን ተቀብሎ ማምለጥ) : አዲሱ የ ኒውካስል አጥቂ በዚህ መለክያ አስደማሚ ቁጥር አለው። እጅግ ከሚደነቅበት የአጨዋወት ባህሪው አንዱ ነው። ኢሳክ 97% የተቀበላቸውን ኳሶች በሚገባ ተቆጣጥሮ ወደ አደጋ ቀጠና የመግባት ስኬት አለው ። ከአሁኑ የኒውካስል ዩናይትድ አጥቂ ካለም ዊልሰን(70%) ጋር ሲወዳደር እጅግ የላቀ ነው።
Reception in opposition box(በተጋጣሚ ሳጥን ኳስን መቀበል)
የመጫወቻ ክፍተት ከሚጠብባቸው ቦታዎች አንዱ የተጋጣሚ ፍ.ቅ.ም ሳጥን ነው። እዚህ አካባቢ ኳስን መቀበል የላቀ የቴክኒክ ብቃት እና የአእምሮ ፍጥነትን ይጠይቃል። ኢሳክ በዚህ መለክያ 84% ስኬት አለው። በአንፃሩ ካለም ዊልሰን 56%::
Areal duels( የዓየር ኳስ ፍልሚያ): እንደ ቁመቱ ብዙም የዓየር ላይ ኳስ አጠቃቀሙ ጥሩ ያልሆነው ስዊድናዊ በ ተቀናቃኙ ዊልሰን ይበለጣል። ዊልሰን 66% የዓየር ፍልሚያዎችን የማሸነፍ ስኬት ሲኖረው፣ ኢሳክ 17% አስመዝግቧል።
Defensive Intensity ( የመከላከል ጥበብ) : ይህ መለክያ ለኳሱ ቅርብ የሆነ ተጨዋች ኳስ የያዘውን ተጋጣሚ በ ምንያህል ርቀት መሸፈን ወይም መቼ የመንጠቅ ውሳኔ መወሰን እንዳለብት እና ከውሳኔው በኋላ ስኬታማነቱን ይለካል። በዚህም መሰረት ካለም ዊልሰን በከፍተኛ መጠን ቡድኑን አግዟል(71%)። የ ኢሳክ 29% በዚህ በኩል ብዙ ስራ እንደሚጠበቅበት ይጠቁማል።
ከላይ እንደተዘረዘረው አሌክሳንደር ኢሳክ በማጥቃት መለክያዎች የተዋጣለት ተጨዋች እንደሆነ መመልከት ይቻላል። በግል ተሰጥኦ ላይ የተመሰረቱት ባህርያቱ እጅግ አደገኛ አጥቂ ያደርጉታል። ከቦሩስያ ዶርትመንድ በውሰት ወደ ኔዘርላንድ አቅንቶ ለ ዊለም ሲጫወት በ መጀመርያዎቹ 12 ጨዋታዎች 12 ግቦችን በማስቆጠር የ ሮናልዶ ናዛርዮን ሬከርድ ማሻሻል ችሏል።
ነገር ግን በዘመናዊ እግርኳስ ስኬታማ ለመሆን የመከላከል ተሳትፎም ወሳኝ ሚና አለው። ኢሳክ ከኳስ ውጭ ያሉትን ቁጥሮቹን ማሻሻል ከቻለ ለኒውካስል ዩናይትድ ወሳኝ ሚናን መጫወት ይችላል።
ከግለኝነት ጋር ያለው ባህሪም ሌላ ስራ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። በሬያል ሶስዬዳድ ባሰለፋቸው ጊዜያት ስዊድናዊው አጥቂ 3 ግብ ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ማቀበል ችሏል። የ shot volume ቁጥሩ 93% ለሆነ ተጨዋች 3 ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ብቻ አመቻችቶ ማቀበል የጨዋታ ባህሪው ላይ ግለኝነትን ያመላክታል።
የወጣበት የዝውውር ሂሳብ ብዙ ተጨዋቾችን ጫና ውስጥ ሊከት የሚችል ይሆናል። ከ ዝላታን ኢብራሂሞቪች ጋር ከልጅነት እድሜው ጀምሮ እየተነፃፀረ ላደገው አሌክሳንደር ኢሳክ ግን ይሄ ፈተና ሊሆን አይችልም። በስዊድን ተወልዶ ፣ ጀርመን ተኮትኩቶ ፣ ስፔን ላቆጠቆጠው ደመ ኤርትራዊ ወጣት እንግሊዝ ለማበብ ቅዱስ ጄምስ ፓርክ ደርሷል።