
ዋልያዎቹ በ4 ነጥብ ከምድባቸው መጨረሻ በማጠናቀቅ አይቮሪ ኮስት ለምታዘጋጀው አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ጨዋታን ለማድረግ ያልታደለው ብሄራዊ ቡድን በሜዳም ከሜዳ ውጭም በርካታ ፈተናዎች እየገጠሙት ይገኛሉ፡፡

Picture- Ethiopian Football Federation
የአዲስ አበባ ስቴዲየም እድሳት በተያዘለት ቀነ ገደብ አለማለቅ፤ የተተከለው ሳር ድጋሚ ተነስቶ በሌላ እንዲተካ መወሰን፤ የአደይ አበባ ስቴዲየም ግንባታ በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት መጓተት እና የሜዳ ጨዋታዎችን ከሀገር ውጭ ለማከናወን እየወጣ ያለው ከፍተኛ ገንዘብ ብሄራዊ ቡድኑ ከሜዳ ውጭ ከተጋረጡበት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱት ናቸው፡፡
ፌደሬሽኑ ምንም እንኳን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ስምምነቶችን በመፈጸም ራሱን በፋይናንሱ ረገድ ለማጠናከር የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም እስከመቼ ድረስ ጨዋታዎችን ከሜዳ ውጭ እያሰናዳ ይዘልቃል የሚለው ነገር ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡
ሜዳ ላይም ቢሆን ብሄራዊ ቡድኑ ውጤት ከራቀው ሰንበትበት ብሏል፡፡ ሰኔ 2014 ላይ ግብጽ ላይ የተመዘገበው ድል ብዙዎችን ያስፈነደቀ ቢሆንም እናም ከጥቂት ወራት በኋላም ለአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የዋልያዎቹ ቆይታ እንደአንድ ምክንያት ቢጠቀስም ከዛ በኋላ የተደረጉት የማጣሪያ ጨዋታዎች ደካማ የነበሩ እና ከውጤት ማጣቱም ጋር ተያይዞ ለአሰልጣኙ በፈቃድ ስራ የመልቀቅ እንደ አንድ ምክንያት ሆነዋል፡፡
በአሰልጣኝ ውበቱ ስር ኳስን ከኋላ መስርቶ እና ተቆጣጥሮ ለመጫወት የሚጥርን ቡድን የመስራቱ ሂደት ለቻን እና ለአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮች ማሳለፍ ቢችልም በውድድር ግጥሚያዎች ላይ የታየው እንቅስቃሴ ግን እጅጉን ደካማ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ብዙ ኳሶችን አደጋኛ ባልሆነ የሜዳ ክፍል የሚቀባበል እና በርካታ የሚባሉ ጥራት ያላቸው እድሎችን ለመፍጠር የሚቸገር ቡድንን አስተውለናል፡፡ ይህ ደግሞ ውጤታማነቱን እጅጉን ጎድቶታል፡፡ ቀላል በሚባሉ የተከላካይ መስመር ስህተቶችም ግብ እየተቆጠረበት ለሚያስቆጩ ሽንፈቶች ተጋላጭ ሲሆን አይተናል፡፡
ከውበቱ መልቀቅ በኋላም ቡድኑ ከማላዊ ጋር 0-0 ሲለያይ ባለፈው አርብ ደግሞ በግብፅ 1-0 ተረቷል፡፡ አሁን ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው በሚዲያዉም ሆነ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው እና ቡድኑን አንድ ደረጃ ወደፊት ፈቀቅ ሊያደርግ የሚችል አሰልጣኝ ማነው የሚለው ነው፡፡
ውበቱ በተደጋጋሚ ከሚዲያ ይደርስበት የነበረው ጫና ከመጠን ያለፈ እንደነበር በመግለጫዎቹም ሆነ በተጋበዘባቸው ፕሮግራሞች ላይ ሲናገር ተስተውሏል፡፡ ይህ ሞቃቱ የብሄራዊ ቡድን ወንበር የሚመች ሊሆን እንደማይችል ይጠበቃል፡፡ አሁን በሊጉ ውስጥ ካሉ አሰልጣኞችም የትኛው ለብሄራዊ ቡድን ይሆናል የሚለው ጉዳይ ብዙዎችን እንደሚያከራክር ይጠበቃል፡፡ ምናልባትም አይንን ወደ ውጭ ሀገር አሰልጣኝ ማዞር የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም፡፡ እዚህ ላይም ቢሆን ግን የቅርብ አመታት ተሞክሮን ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ምርጫ የማይስማማቸው ብዙዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታሰባል፡፡
ከህዳር ወር ጀምሮ ለ2026ቱ አለም ዋንጫ የማጣሪ ጨዋታዎችን ማድረግ የሚጀምረው ቡድን በቀጣዮች ጥቂት ወራት ሁሉንም እንኳን ባይባል አንገብጋቢዎቹን ጉዳዮች መፍትሄ በማበጀት የተሻለ እንቅስቃሴን ማሳየት ይኖርበታል፡፡

Picture- Ethiopian Football Federation
ብሄራዊ ቡድኑ ፈረንጆቹ እንደሚሉት መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ በቀጣይ ከአሰልጣኝ፤ ከሜዳ እናም በአጠቃላይ ከአስተዳደር አንጻር የሚወሰኑ ውሳኔዎች ትልቅ አንድምታ እንደሚኖራቸው እሙን ነው፡፡ በብዙ ችግር ላይ ያለው ብሄራዊ ቡድን ህመሙን የሚያስታግስለት መድሃኒት በአስቸኳይ ይፈልጋል፡፡