
“My greatest challenge is not what’s happening at the moment, my greatest challenge was knocking Liverpool right off their f*g perch. And you can print that” ይህን ያሉት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በሴፕቴምበር 2002 ነበር። የማንቸስተር ዩናይትዱ አሰልጣኝ በወቅቱ ክለባቸውን በሊግ ድሎች ብዛት ከሊቨርፑል በላይ ባያደርጉትም ለ10 ዓመታት ገደማ ከበላይነቱ አፈናቅለውት ነበር። በኩራት ጠንካራ ቃላት ተጠቅመው የተናገሩትም ይህን ነበር። ስኮትላንዳዊው በ2011፣ ለዩናይትድ 19ኛ ድል አምጥተው፣ የሰሜን ጎረቤታቸውን ከበላይነታቸው ብቻ ሳይሆን ከምንጊዜም ንግስናቸው ፈንቅለዋቸዋል። ፈርጊ በ2013 በሌላ ድል ልዩነቱን አስፍተው ወደጡረታ አምርተዋል። ቀዮቹ ላለፉት 14 ዓመታት በባላንጣቸው ጥላ ስር ከቆዩ በኋላ ዛሬ ምሽት ወደእንግሊዝ እግር ኳስ ንግስናቸው ተመልሰዋል።
በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ የሊቨርፑልን ድል የገመተ ብዙ አልነበረም። ኦፕታ ሱፐርኮምፒዩተር ለቀዮቹ 5.1ፐርሰንት ብቻ ሊጉን የማሸነፍ ግምት ሰጥቷቸው ነበር። አርሰናል በ12.2ፐርሰንት እና ባለክብሮቹ ማንቸስተር ሲቲ በ82.2ፐርሰንት የተሻለ ተገምተዋል። እንዲያውም ጋሪ ኔቭል ከቀድሞ ክለቡ ማንቸስተር ዩናይትድም በታች አምስተኛ ሆነው እንሚያጠናቅቁ ግምቱን ገልጿል። ለሊቨርፑል አለመገመት በወቅቱ አሳማኝ ምክንያቶች ነበሩ። የክለቡ ህያው የርገን ክሎፕ መልቀቅ፣ የአዲሱ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት እምብዛም አለመታወቅ፣ ዝውውሮች አለመደረጋቸው እንዲሁም እድሜያቸው የገፋ ከዋክብት እና በኮንትራታቸው መጨረሻ ላይ የሚገኙ ቁልፍ ተጨዋቾች መኖራቸው ዋናዎቹ ነበሩ።
ቀዮቹ በመጀመሪያ ጨዋታቸው የመጀመሪያ አጋማሽ በኢፕስዊች ታውን ሜዳ ሲቸገሩ ፈታኝ የውድድር ዘመን እንደሚኖራቸው ተገመተ። ስሎት ለሁለተኛው አጋማሽ ሲመለሱ ኩዋንሳን አስወጥተው ኮናቴን በማስገባት ጨዋታውን ቀየሩት። ዲዮጎ ጆታም በ60ኛው ደቂቃ የመክፈቻውን ጎል አስቆጠረ። ከዚያ ቅፅበት በኋላ የሆነው ሁሉ ታሪክ ነው። በአራተኛው ሳምንት በኖቲንግሀም ጢኒጢዬ ኩርኩም ቢቀምሱም ወደኋላ አልተመለከቱም። ከሳምንት ሳምንት፣ በሜዳቸውም ሆነ ከሜዳቸው ውጪ እያሸነፉ ገና አራት ጨዋታ እየቀረ ሻምፒዮን ሆነዋል። ከጥቂት ጥርጣሬዎች ውጪም ላለፉት ሶስት/አራት ወራት ሊጉን ማሸነፋቸው ይታወቅ ነበር። የስሎት ቡድን በሁሉም ረገድ የበላይ ነበሩ:- በሙሉ የውድድር ዘመኑ በስድስት ሳምንታት ብቻ መሪ አልነበሩም (በመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ሳምንታት ውስጥ ነበሩ)፤ ከፍተኛ አስቆጣሪ ናቸው (ከቀጣዩ በ14 ጎሎች ይልቃሉ)፤ ሁለተኛ ምርጥ ተከላካይ ናቸው፤ ብዙ ያሸነፈ (ከተከታዩ በስድስት ይበልጣሉ) እና ትንሽ የተሸነፉም ናቸው።
የመርሲሳይዱ ቡድን ለአስደናቂ የሊግ ክብር የበቃባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይህ ራሱን የቻለ ብዙ የሚያወያይ ርዕስ ስለሆነ ጨረፍ አድርጌ ልለፈው። የክሎፕን መልቀቅ እንዳወቁ የቀድሞውን እጅግ ስኬታማ የስፖርት ዳይሬክተር ማይክል ኤድዋርድስን በዋና ስራ አስፈፃሚነት የሾሙት እና ተደጋግመው የተጠሩ ስሞችን ትተው በአስደናቂ ምልመላ ኔዘርላንዳዊውን አሰልጣኝ የቀጠሩት የክለቡ ባለቤቶች እና ኃላፊዎች ሊመሰገኑ ይገባል። ለዓመታት ቡድኑን በተጨዋቾች እና በማሸነፍ ስነ-ልቦና የገነቡት እና ለተተኪያቸው የተሟላ ስብስብ ትተው የሄዱት ክሎፕ የድሉ ተቋዳሽ ናቸው። ሁሉም ተጨዋቾች ለድሉ ተጠቃሽ ቢሆኑም በቅርቡ ኮንትራታቸውን ያራዘሙት የፕሪምየር ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሳላህ እና የቡድኑ መሪ ቫን ዳይክ የተለዩ ነበሩ። በአዲስ የ6 ቁጥር ሚና ያስደመመው ግራቬንቤርኽ የቡድኑ የልብ ምት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። ማካሊስተር እና ሶቦዝላይም ድንቅ ነበሩ። ዲያዝ እና ሀክፖ በተፈለጉባቸው ጊዜያት ተገኝተዋል። ወጣቶቹ ጆንስ፣ ብራድሊ፣ ኬልኸር እና ኤሊየት ያገኟቸውን እድሎች ተጠቅመዋል።
የ20ኛው የሊግ ክብር ቀዳሚው ተጠቃሽ ግን ስሎት ናቸው። የቀድሞው የፌይኖርድ አሰልጣኝ በአንፊልድ ከፈፀሟቸው ተግባራት ዋናዎቹ እነዚህ ይመስሉኛል:- የተረከቡትን ዓምና የተፎካከረ ቡድን ብዙ አለመንካታቸው (በተጨዋቾች ረገድ የተነኩት የኮናቴ ወደቋሚነት መመለስ እና የግራቬንቤርኽ በኤንዶ ምትክ መጫወት ብቻ ይመስሉኛል)፣ በአጨዋወት በኩልም ከክሎፕ ብዙ ሳይቀየር እርጋታ እና ጨዋታ ቁጥጥርን የጨመረ ቡድን መሆኑ፣ ሳላህ እና ቫን ዳይክን ወደምርጥ አቋማቸው እንዲመለሱ ማገዛቸው (በተለይ ግብፃዊው የመጫወት ደስታን መልሶ ያገኘ መስሏል)፣ ተዓምራዊው የግራቬንቤርኽ ለውጥ፣ የሶቦዝላይ መሻሻል እና የጆንስ ጉልህ እድገት ሁሉ ሊጠቀሱ የሚገባቸው የስሎት ስኬቶች ናቸው።
ቀዮቹ ከሶስቱ ከዋክብት የሁለቱን ኮንትራት ማራዘም መቻላቸው ለቀጣይ ዓመታትም በጥንካሬ የሚዘልቁበት መሰረት ይሆናቸዋል። በክረምቱ ሶስት ወይም አራት ተጨዋቾች (9 ቁጥር አጥቂ፣ 6 ቁጥር አማካይ እና የመሀል ተከላካይ…) ካስፈረሙ 21ኛ ክብራቸውን የማሸነፍ ተስፋቸውን ያጠናክርላቸዋል።
ባለፈው ዓመት ፌብሩዋሪ ሰር ጂም ራድክሊፍ የማንቸስተር ዩናይትድን ድርሻ መግዛታቸው እንደታወጀ ፈርጉሰንን የሚያስታውስ ሀሳብ ተናግረው ነበር:- “There is nothing I would like better than to knock both of them (Liverpool and Man City) off their perch.” በራድክሊፍ ጅማሮ የሆነው ግን የሊቨርፑል መልሶ መንበሩን መረከብ ነው። አሁን ጥያቄው ራድክሊፍ በሶስት ዓመታት ውስጥ ሊቨርፑል እና ሲቲን ከበላይነታቸው እንደሚያወርዱ የሰጡት ቃል እውን ይሆናል? መቼ? የሚለው ነው።