
2009/10 የቻምፕየንስ ሊግ አሽናፊ የጣልያኑ ኢንቴር ነበሩ:: በፍፃሜውም ባየርን ሚውኒክን በማሸነፍ ባለጆሮውን ዋንጫ ከፍ አድርገዋል:: ለጀርመናውያኑ ንቀት አይምሰልና የውድድሩ ወሳኝ ምዕራፍ ግን ግማሽ ፍፃሜው ነበር:: ኢንቴር ከ ባርሴሎና:: የቀድሞ ወዳጆችን ጠላት ያደረገ ፣ የሁለት ተቃራኒ እግርኳስ ሃሳቦችን ያላተም እና የጆዜን የወደፊት አሰልጣኝነት ስራ የወሰነ 180 ደቂቃ:: በዘንድሮው የ ግማሽ ፍፃሜ ደርሶ መልስ ጨዋታ እነዚህ ሁለት ክልቦች በድጋሚ መገናኘታቸው ሰበብ አድርገን በትዝታ 15 ዓመታትን ወደኅላ ተመልሰን እንጎብኝ::
ጆዜ እና ባርሳ
ሰር ቦቢ ሮብሰን በፖርቹጋል ሊግ አሰልጣኝነት ስራቸው አስተርጏሚ ሆኖ ያገላገላቸው ወጣቱ ጆዜ ማሪዮ ዴ ሳንቶስ ሞውሪንዮ ፌሊዝ ነበር:: ገና በ 20ዎቹ እድሜው ነው መጫወት ዕጣ ፈንታው እንዳልሆነ የተረዳው:: ከእግር ኳስ ግን አልራቀም:: ወደማሰልጠኑ ዓለም ለመቀላቀል መንገዱን መፈለግ ጀመረ:: የእንግሊዝኛ ቋንቋ አቀላጥፎ ይናገር ስለነበር በስፖርቲንግ ክሉብ አሰልጣኝነት የተሾሙት ሰር ቦቢ ጋር የመስራቱን ወርቃማ ዕድል ተፈጠረ:: የሁለቱ ግንኙነትም ከስፖርቲንግ አንስቶ ፖርቶ እንዲሁም ባርሴሎና ድረስ ዘልቋል::
ባለብዙ ቋንቋ ተናጋሪው ጆዜ በእንግሊዛዊው አሰልጣኝ እና ተጨዋቾቻቸው መካከል ወሳኝ ድልድይ ነበር:: ከቦቢ ሮብሰን ስንብትም በኅላ ከቀጣዩ አሰልጣኝ ቫን ሃል ጋርም መስራት ችሏል::ለቀጣይ አሰልጣኝነት ህይወቱ በባህሪም ሆነ የጨዋታ ፍልስፍና መሰረት የተጣለባቸው ስድስት ዓመታት ነበሩ::
ጆዜ እንደ አሰልጣኝ እራሱን የሚፈልግበት ጊዜ ደረሰ:: በ 2002 የፖርቶ አሰልጣኝ ሆነ:: በሁለት ዓመታት ውስጥ ፖርቶን ከሊግ እስከ አውሮፓ ድረስ ባለድል አደረገ:: 2004 ወደ እንግሊዝ በማቅናት ተአምራዊ ተፅዕኖ መፍጠር ቻለ:: በእነዚህ 5 ባልሞሉ ዓመታት ተከታታ የሊግ ዋንጫዎች ፣ የ UEFA ካፕ እና ቻምፕየንስ ሊግ እንዲሁም በርካታ የጥሎ ማለፍ ዋንጫዎችን ያሳካ የወቅቱ ቁጥር 1 አሰልጣኝ ተባለ::
ጆዜ አእምሮ ውስጥ ግን ሁሌም አንድ ህልም ነበር:: እርሱም ባርሴሎናን በአሰልጣኝነት መምራት ነው:: የካታላኑ ክለብም ቀጣይ አሰልጣኙን እየፈለገ በነበረበት ወቅት የቀድሞ አሰልጣኝ ቡድን አባላቸው ስም ዝርዝር ውስጥ ነበር:: ፖርቱጋላዊውን ለአሰልጣኝነት ማጨታቸው ምክንያታዊ ነበር:: በባርሴሎና ክለብ ውስጥ ለዓመታት የሰራ ፣ልዩ የሆነውን ባህል የሚረዳ እንዲሁም በተለያዩ ሊጎች ሰርቶ አሸናፊነቱን ያስመሰከረ አሰልጣኝ ነበር:: የፍራንክ ራይካርድ ተተኪ ይሆናል ብለው የገመቱም ጥቂት አልነበሩም:: ለ አሰልጣኝነቱ ስራም ቃለመጠይቅ አደረገ::
በመጨረሻ የክለቡ ውሳኔ ግን ሌላ ነበር:: የባርሴሎና እግርኳሳዊ ውሳኔዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘውዋሪ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠር የሚችለው ዮሃን ክሩይፍ የክለቡ ሃላፊዎች ፔፕ ግዋርድዮላን ቀጣዩ አሰልጣኝ እንዲሆን አማከረ:: ህዋን ላፖርታ እና ቦርዳቸውም ትእዛዛዊ ምክሩን ተቀበሉ:: ፔፕ በወቅቱ የባርሴሎናን ሁለተኛ ቡድን ያሰለጥን ነበር:: የጆዜ እና ባርሳ ቁርሾ እዚህ ጋር ይጀምራል::
ቲኪ ቤግሪስቴን ጆዜ ሞውሪንዮን ለባርሴሎና አሰልጣኝነት ቅጥር ቃለ-መጠይቅ የመራው የክለቡ ስፖርቲንግ ዳይሬክተር ነበር:: የፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ በ ፓወር ፖይንት የታገዘ ዝርዝር ማብራርያ ቲኪን አስደምሟል:: በቂ ግን አልነበረም:: ካታላኑ ከእራሳቸው ለአንዱ፣ የክራይፍን ይሁንታ ላገኘው እና ምንም እንኳን ዋንጫ በአሰልጣኝነት አንስቶ ባያውቅም ከቀድሞ አስተርጏሚያቸው አስበልጠው የሚያይዩት ፔፕ ግዋርድዮላ ሃላፊነቱን ተረከበ::
ከዚህ ክስተት በኅላ ሞውሪንዮ ባርሴሎናን አሰልጥኖ እራሱን ለማስመስከር የነበረው ህልም በ ባርሴሎና ተቃራኒ ቆሞ እራሱን ወደማስመስከር ተቀየረ:: ባርሴሎና የሚያምንበትን የእግርኳስ ፍልስፍና በሙሉ ተቃራኒውን መተግበር አላማ ሆነ:: ባርሴሎና ውብ እግኳስ ይጫወታል? ሞውሪኖ ለጨዋታው ውበት ደንታ የለውም:: የኳስ ቁጥጥር የሁሉም ነገር መነሻ ነው? ሞውሪንዮ ከፈለክ ኳሱን ይዘህ ቤት እንድትወስደው ይፈቅድልኅል:: ፀረ ባርሴሎና ፍልስፍና::
የ ፖርቱጋላዊው ቀጣይ ቅጥር የተጠና ነበር:: ጊዜው በቀጥታ ወደ ሬያል ማድሪድ ለመሄድ ምቹ አልነበረም:: ነጮቹ በወቅቱ የፕሬዝዳንትነት ሽኩቻ እንዲሁም የ ድህረ ጋላክቲኮ ዘመን ሃንጎቨር ላይ ናቸው:: ስለዚህ ሞውሪንዮ ስልታዊ ውሳኔ መወሰን ነበረበት:: በቅርብ ዓመታት ፈጣን ስኬት ማስመዝገብ የሚችልበትን ክለብ መፈለግ ነበረበት :: ይህም ክለብ ኢንቴር ነበር::
በወቅቱ የጣልያን እግርኳስ ጥሩ ሁኔታ ላይ አልነበረም:: ዋና ዋና ክለቦቹ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ቅሌት ቀውስ ውስጥ ነበሩ:: ይህ ለ ሴሪ-ኣ ተአማኒነት እና ተቀባይነት የቀነሰበት ነበር:: ጊዜው ለጣልያን የክለቦች እግርኳስ ከባድ ቢሆንም በአንፃራዊነት ኔራአትዙሪ የተፎካካሪዎችን መዳከም ተጠቅመው ስኬታማ መሆን ችለዋል:: በማንቺኒ እየተመሩ በአንፃራዊነት የለም ሊባል በሚችል ፉክክር የሊግ ክብሮችን አሳክተዋል:: ሞውሪንዮም በዚህ ቡድን የአጭር ጊዜ ስኬት እንደሚመጣ ተረድቷል:: ውሳኔውም ስህተት አልነበረም::
ኢንቴር በፖርቱጋላዊው እሰልጣኝነት በመራራት ሁለት ተከታታይ ስኩዴቲ ፣ አንድ የ ኮፓ ኢታልያ ፣ አንድ የ ሊግ ሱፐርኮፓ እና እስከዛሬም በኩርቫ ኖርድ የሚዘመርለትአድ የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫን አንስተዋል:: ሞውሪንዮ በሁለት ዓመታት ኢንቴርን ለዘመናት ካሰለጠኑ አንጋፋ አሰልጣኞች ጎን በታሪክ ይጠቀሳል::
2009/10 የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ የኢንቴር ጉዞ ግማሽ ፍፃሜ ላይ ይገታል ብሎ ያልገመተ አልነበረም:: ለዚህ ምክንያቱ የወቅቱ ሃያል ቡድን ባርሴሎና ከፊቱ የሚገጥሙትን በሙሉ እያርበደበደ በአሳማኝ ሁኔታ የሚረታ ፣ ብዙዎች በአንድ ድምፅ የዘመኑ ምርጥ ቡድን ብለው የሰየሙት እና የወቅቱን የ ባሎንዶር አሸናፊ እንዲሁም እግርኳስ ካፈራቻቸው ጥበበኞች አንዱ የሆነውን ሊዮኔል ሜሲ የያዘ ቡድን መሆኑ ነበር::
ለሞውሪንዮ ይህ የደርሶ መልስ ጨዋታ ወደ ፍፃሜ የማለፍ ጉዳይ ብቻ አልነበረም:: የተዳፈነ ቁርሾ መልሶ የሚጎበኝበት ፣ ሂሳብ የሚወራረድበት እና ለፍሎረንቲኖ ፒሬዝ ጠንከር ያለ መልዕክት የሚተላለፍበት አጋጣሚ ነበር:: ይቀጥላል