የቀድሞ ክለቡን ሊቨርፑል በማክሰኞ ምሽት የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ የሚገጥመው ትሬንት አሌክሳንደር አርኖልድ በልጅነቱ ወቅት ስቴቨን ጄራርድ እና ዣቢ አሎንሶን ያደንቅ እንደነበር ተናግሯል፡፡ አርኖልድ ይህንን የተናገረው ከአማዞን ፕራይም ጋር በነበረው ቆይታ ሲሆን ኳስን ማቀበል አርት እንደሆነ ከጄራርድ እና አሎንሶ መማሩን ጠቅሷል፡፡ “ በጣም አሪፍ የሆነን ኳስ ሲመታ በሚያወጣው ድምጽ መለየት ይቻላል ፤ ለመግለጽ ቢያስቸግርም ጥሩ የሆነ እና በትክክል የተመታ ኳስ በድምጹ ያስታውቃል፤ አሎንሶ የተለያዩ አይነት የማቀበል ቴክኒኮችን እንድሞክር ምክንያቴ ሆኗል፤ አሁን አሰልጣኝ ሆኖ እንኳን ያን ብቃት አብሮት አለ” በማለት ትሬንት ተናግሯል፡፡

ትሬንት በነጻ ዝውውር ሊቨርፑል በመልቀቅ ሪያል ማድሪድን ከተቀላቀለ በኋላ ድንቅ አቋሙን ለማግኘት ጊዜ የፈጀበት ሲሆን በጉዳት ምክንያትም ተደጋጋሚ የቋሚነት እድልን ማግኘት አልቻለም፡፡ ከሊቨርፑል ጋር በሚደረገው ጨዋታ ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ይገባል ወይ የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል፡፡




