የፓርቴይ ‹‹መነጠል›› የሚያስከትለው ጣጣ

(Getty Images)

(በአቤል ጀቤሳ-ከአትሌቲክ የተወሰደ)

መድፈኞቹ ክሪስታል ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ ጎልቶ የታየው የቶማስ ፓርቴይ ክህሎት የተጋጣሚ ተጫዋቾችን በቀላሉ የሚያልፍበት መንገድ ነበር ፡፡
የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ሊያደርጉ የሚችሉትን እንቅስቃሴ አስቀድሞ በመገመት በቀላሉ ዞሮ በመሄድ በአማካይ ክፍሉ ተወዳዳሪ ያልነበረው እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡

አልፎ አልፎ ግን ወጥመድ ውስጥ ሲገባ ታይቷል፡፡ ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ በተወሰኑ አጋጣሚዎች ተጋልጦ ታይቷል ፡፡ 50ኛው ደቂቃ ላይ አራት ተጫዋቾችን ለማለፍ የሞከረበት አጋጣሚ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በሂደቱ ኳስ ተነጠቀ ፤ ፓላስ የአቻነቷን ጎል አገኘ…አርሰናል ተቀጣ!

የግል ስህተት ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ የሚኬል አርቴታ ሲስተም ግን ከተጠያቂነት አያመልጥም ፡፡ በአማካይ ክፍሉ እምብርት ፓርቴይ ብቸኛው ደካማ ጎን ተደርጎ እንዲታይ አድርጎታል ፡፡


ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ ጋናዊው ከማርቲን ኦዴጋርድ እና ኤሚል ስሚዝ ሮው ጋር ሶስት ተጫዋቾችን የያዘው የአማካይ ክፍል አካል ነበር ፡፡ የቴሌቪዥን ምስሎች ፓርቴይ ሆልዲንግ አማካይ ሚናን እንደያዘ እና ኦዴጋርድ እና ስሚዝ ሮው ወደፊት እየሄዱ የማጥቃት እንቅስቃሴውን የሚቀላቀሉ ሁለቱ 8 ቁጥሮች እንደነበሩ ያሳያሉ ፡፡

ባለፈው የውድድር ዘመን በዩሮፓ ሊግ ግማሽ ፍጻሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ከቪያሪያል ጋር ተገናኝተው 0ለ0 ሲለያዩም የመረጡት ተመሳሳይ ሲስተም ነበር ፡፡
ያን ምሽት ዕቅዱ አላዋጣም ፡፡ አርሰናል በአማካይ ክፍል ቀጣይነት ያለው አጨዋወት ለመተግበር ተቸግሮ ታይቷል፡፡

ፓርቴይ በተደጋጋሚ ኳስ ተነጥቋል ፡፡ በዚያ ጨዋታ የተነጠቀው በ15 አጋጣሚ ነበር ፡፡ ከባለፈው የውድድር ዘመን መጀመሪያ ወዲህ ባለው ጊዜ በአንድ ጨዋታ ከፍተኛ ኳስ የተነጠቀበት ሁለተኛ ጨዋታ ነበር ፡፡ ለፓርቴይ ከአስቸጋሪ ቀኖቹ አንደኛው ተደርጎ ይታሰባል ፡፡

እጅግ አሳሳቢው ነገር በተደጋጋሚ ኳስ መነጠቁ አይደለም ፤ የሚነጠቀብት ቦታ እንጂ… ፡፡ ከላይ እንደምትመለከቱት በሚታወቅበት እንቅስቃሴው እርሱን ለመቆጣጠር የከበቡትን ተጫዋቾች አልፎ ለመሄድ ሲሞክር ተነጥቆ ቪያሪያል አደገኛ የማጥቃት ሽግግር አስጀምሯል፡፡

ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ ብቸኛ የተከላካይ አማካይ ሆኖ ተጫውቷ ብሎ መደምደም ስህተት ላይ ይጥላል ፡፡ ከጨዋታው በፊት አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ከስካይ ስፖርት ጋር ባደረገው ቆይታ ‹‹ የተጫዋቾቹ ብቃት በተወሰነ መልኩ የፎርሜሽኑን አተገባበር ሊለውጠው ይችላል ፡፡ እንዲያም ሆኖ ብዙ ለውጥ አይኖረውም ›› ብሏል ፡፡
ስፔናዊው ይህንን የተናገረው በዘፈቀደ አልነበረም ፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ኖርዌያዊው ማርቲን ኦዴጋርድ ብዙ ጊዜውን ከፓርቴይ ጎን ሲያሳልፍ ወደፊት እየሄደ የማጥቃት እቅስቃሴውን እንደልብ ሲቀላቀል የነበረው ስሚዝ ሮው ነው ፡፡ ይህም አጨዋወቱ አንድ ብቸኛ ‹‹ፒቮት›› እና ሁለት 8 ቁጥሮች የተሳተፉበት ሳይሆን ሁለት የተከላካይ አማካይ እና አንድ ወደፊት ተጠግቶ የሚጫወት አማካይ የያዘ ቡድን ቅርጽ እንዲኖረው አድርጓል ፡፡


በመጀመሪያው አጋማሽ ኦዴጋርድ ብዙ ጊዜውን ያጠፋው ግራኒት ዣካ ይጫወትበት በነበረው ቦታ ላይ ነው ፡፡ በተደጋጋሚ ወደ ግራ ተከላካይ ቦታ በጥልቀት አፈግፍጎ ይገኝ ነበር ፡፡ አርሰናል ከኋላ መስርቶ ለመጫወት የሚያደርገውን ጥረት ማገዝ እና ኪዬረን ቲይረኒ ወደ ሜዳው የላይኛው ክፍል በነጻነት እንዲጓዝ ዕድሎችን ሲፈጥር ታይቷል ፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ የነካባቸውን ቦታዎች ከተመለከትን ይህንኑ ይመሰክራሉ።

በሁለተኛው አጋማሽ አልበርት ሳምቢ ሎኮንጋ ተቀይሮ ወደ ሜዳ በመግባት ከፓርቴይ ጎን ያለውን ቦታ ያዘ ፡፡ ኦዴጋርድ ስሚዝ ሮው ሲወጣው የነበረው ሚና ተሰጠው ፡፡ የ10 ቁጥር ሚና ኖሮት እንደ አስፈላጊነቱ ወደ ቀኝ መስመር እየወጣ ከኒኮላ ፔፔ ጋር የአንድ ሁለት ቅብብሎችን እያደረገ ዕድሎችን እንዲፈጥር መመሪያ ተሰጥቶታል ፡፡

አሰልጣኙ ይህን ለማድረግ የወሰነው የአርሰናል የቀኝ መስመር ተከላካይ ታኬሂሮ ቶሚያሱ በተደጋጋሚ ወደፊት ተጉዞ የማጥቃት እንቅስቃሴውን አለመቀላቀሉ የሚፈጥረውን ክፍተት እንዲያካክስ ነበር ፡፡ በታሰበው ልክ ውጤታማ ሆኗል ማለት ግን አይቻልም ፡፡


ቀጣዩ ምሳሌ ጨዋታው አስር ደቂቃዎችን ብቻ እንደተጓዘ የተከሰተ አጋጣሚን ይመለከታል ፡፡ ሁለት ነገሮችን በግልጽ ያሳያል፡፡ ኦዴጋርድ እንዲሸፍነው የታሰበውን የግራ ተከላካይ ቦታ እና ፓላስ ከጨዋታው መጀመሪያው አንስቶ ፓርቴይ ከኳስ ጋር የሚያሳልፈው በቂ ጊዜ እንዳይኖረው እንዴት በፍጥነት ተጫዋቾች እንዲከብቡት ያደርግ እንደነበር ያሳያል ፡፡


በዚህኛው አጋጣሚ ፓርቴይ ብዙም አደጋ የማይጋብዘውን ምርጫ አሳለፈ ፡፡ኳሷን በቀላሉ ለመሃል ተከላካዩ ጋብሪኤል ፓስ አደረገ ፡፡ ፓርቴይ ክሪስታል ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ ካደረጋቸው 49 ፓሶች ዘጠኑ ለጋብሪኤል ያደረጋቸው ናቸው ፡፡

ይህም ተጋጣሚው እርሱን ፕሬስ ያደረገበት መንገድ ምን ያህል ውጤታማ እንደነበር ያሳያል ፡፡ በተደጋጋሚ በነጻነት ፓስ እንዲያደርግ የሚፈቀድለት ለጋብሪኤል ነበር ፡፡ በሜዳው መሃል ለመሃል ለቡድኑ አስር ቁጥር ተጫዋች ስሚዝ ሮው ፓስ ማድረግ የቻለው በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር ፡፡


ኦዴጋርድ የግራ ተከላካይ ቦታን እንዲደፍን መደረጉ መሃል ሜዳ ላይ ፓርቴይ ተነጥሎ እንዲገኝ አስገደደው ፡፡ በአርቴታ ሲስተም ትርፍ እና ጉዳቱ ተሰልቶ የተወሰደ ‹‹ሪስክ›› ነው ፡፡ ፓርቴይ ከቡድኑ ተጫዋቾች የተጋጣሚን ‹‹ፕሬስ›› በመቋቋም ቀዳሚው ተጫዋች ነው ፡፡ እርሱ በፈጣን ድሪብል አሊያም ቅጽበታዊ ፓስ የተጋጣሚን ‹‹ፕሬስ›› ማለፍ ከቻለ የአርሰናል ሌሎቹ ተጫዋቾች የሚጫወቱበት በቂ ክፍተት ያገኛሉ ፡፡


ፓርቴይ ወደ ለንደን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ አርቴታ የ28 ዓመቱን ተጫዋች የሚጠቀምበት መንገድ ወጥነት ታይቶበታል ፡፡ አርሰናል ኳስ ከራሱ አጋማሽ መስርቶ ለመውጣት ሲሞክር ፓርቴይ ብቻውን የሜዳውን መሃል እንዲቆጣጠር ይጠየቃል ፡፡


የውሳኔው ትክክለኝነት ያከራክራል ፡፡ ሌላ አማካይ ፓርቴይ አጠገብ እንዲገኝ ማድረግ ለአርሰናል አማራጮች ያስገኙለታል ፡፡ መስከረም ላይ በፕሪምየር ሊጉ በርንሌይን ሲገጥሙ ኦዴጋርድ ከፓርቴይ ጎን በጥልቅ ሚና ተጫውቷል ፡፡

ከላይ በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት ፓርቴይ ራሱን በሶስት የበርንሌይ ተጫዋቾች ፕሬስ እየተደረገ ነው ፡፡ ኦዴጋርድ ቀረብ ብሎ መጫወቱ ግን አማራጭ ፈጠረለት ፡፡ አሮን ራምስዴልም ተጨማሪ አማራጭ አገኘ ፡፡

ኦዴጋርድ ቀጥሎ ኳሱን ለፓርቴይ ማቀበል ቻለ ፡፡ ጋናዊው የበርንሌይን ፕሬስ ለማለፍ ኳሷን በተጫዋቹ አናት አሻግሮ ለቲይረኒ አቀበለው ፡፡

ኦዴጋርድ ወደ ፓርቴይ ቀረብ ብሎ መጫወቱ ጋናዊው በቀላሉ የቁጥር የበላይነት እንዳይወሰድበት አደረገ ፡፡ ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ ግን ኦዴጋርድ እና ፓርቴይ ግንኙነታቸው ተቋርጦ ታይቷል ፡፡


እውነት ለመናገር ፓርቴይ አማካይ ክፍሉን ለብቻው እንዲቆጣጠር ሲደረግ ሃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ‹‹ሪስክ›. ለመውሰድ የማይፈራ ሆኖ ይታያል፡፡ ይህንን ከተጠራጠራችሁ ከርቀት የሚያደርጋቸውን ሙከራዎች መመልከት ትችላላችሁ፡፡


ቁማሩ ሲሰምርለት እጅግ ውጤታማ ሆኖ ይታያል ፡፡ በርንሌይን ከገጠሙበት ጨዋታ ሌላ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን ፡፡ ራሶን ከሶስት የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ለማስመለጥ በእግሩ ውጫዊ ክፍል ኳሷን ቆርጦ በመምታት ለቡድን ጓደኛው አድርሷል ፡፡

ዞሮ የሚሄድበት መንገድ ወደ ክፍት ቦታ ሰብሮ እንዲገባ ረድቶታል፡፡ ኳሷን እየገፋ በመሄድ በመስመሮች መካከል ለሚገኘው ቡካዮ ሳካ ፓስ አደረገ።

አልፎ አልፎ እንዲህ ያለው ጀብደኙነቱ ዋጋ ሲያስከፍለው ይታያል፡፡ ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ 44ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ምልክቶች ታይተዋል ፡፡ የፓላስ ‹‹ ፕሬስ›› ከበርንሌይ የተሻለ ነበር፡፡ ከታች በምስሉ ላይ እንደምንመለከተው ፓርቴይ መሃል ሜዳ ላይ በተጫዋቾች ተከብቦ ኳስ ሲቀበል ይታያል፡፡

ኳሷን በቀላሉ ለሳካ አሊያም ቲይረኒ ማቀበል የሚችልበት ዕድል ነበር፡፡ ፓርቴይ ግን መገለጫው የሆነውን እንቅስቃሴ ማድረግን መረጠ፡፡ በውጪኛው የእግሩ ክፍል ኳሷን ከተከላካዮች ጀርባ ወዳለው ቦታ ለመጣል ሞከረ፡፡

ሙከራው ሳይሳካ ቀረ ፡፡ ኮኖር ጋላገር ኳሷን ቆርጦ በማስቀረት የፓላስን መልሶ ማጥቃት አስጀመረ ፡፡ አራት የፓላስ ተጫዋቾች ወደ አርሰናል ሁለት የመሃል ተከላካዮች ሮጡ፡፡ እንቅስቃሴው ለፓላስ ከማዕዘን ምት ውጪ ያስገኘው ነገር ባለመኖሩ መድፈኞቹ ዕድለኞች ናቸው ፡፡

በሁለተኛው አጋማሽም ፓርቴይ በድጋሚ ተመሳሳይ ፈተና ገጠመው ፡፡ ኳስ ከቶሚያሱ እንደተቀበለ አራት የፓላስ ተጫዋቾች ከበቡት ፡፡ ጆርዳን አየው ሳይቀር ከቀኝ መስመር ቦታውን ለቅቆ መጥቶ የቡድኑን የፕሬሲንግ እንቅስቃሴ ሲያግዝ ታይቷል ፡፡

ፓርቴይ በቀላሉ ኳሷን ለሎኮንጋ ማቀበል ይችል ነበር ፡፡ ጫናውን ተቋቁሞ ትክክለኛውን እንቅስቃሴ ማድረግ ከቻለ አርሰናል በቀላሉ ወደ ፊት እንዲገሰግስ ማድረግ እንደሚችል ያውቃል ፡፡ በክፍተቶች መካከል ሾልኮ ለመውጣት ሞከረ ፡፡ አልተሳካለትም ፡፡ ክሪስቲያን ኤሪክሰን የተጨራረፈችውን ኳስ አግኝቶ ጋብሪኤልን አልፎት በመሄድ የአቻነቷን ጎል አስቆጠረ ፡፡

አርቴታ ከጨዋታው በኋላ ፓርቴይ በተደጋጋሚ ከርቀት ሲያደርጋቸው ስለነበሩት ዒላማቸውን ያልጠበቁ ሙከራዎች ሲጠየቅ ‹‹ ከእርሱ ጋር በልምምድ ሜዳ ላይ ስሰራቸው ከነበሩ ነገሮች አንደኛው ጎሎችን ልናስቆጥር የምንችልባቸውን ቦታዎች ነው፡፡

ከዚያ ውጪ ያለው ነገር ሁሉ ከንቱ ድካም ይሆናል፡፡ ያን ማድረግ የሚያስችል አቅም አለው፡፡ በተጫዋችነት ዘመኑ በሙሉ ሲያደርገው ኖሯል ፡፡ እየሞከረ ነው ፣ ሙከራውን መቀጠልም ይኖርበታል ፡፡ ነገር ግን ሙከራዎቹን ማድረግ ያለበት በትክክለኞቹ ቦታዎች ላይ ነው ፡፡ ››


ተጫዋቾችን አልፎ ለመሄድ የሚያሳየው ፍላጎትም በተመሳሳይ መገደብ ይኖርበታል ፡፡ ድንቅ ክህሎት መሆኑ አይካድም ፡፡ ለአርሰናል የተጋጣሚን ‹‹ፕሬስ›› የሚሰብርበት ዕድል ይፈጥርለታል ፡፡ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ጊዜ እና ቦታ መምረጥ ያሻል ፡፡ ፓርቴይ ፓላስን በገጠሙበት ጨዋታ ትልቅ ‹‹ሪስክ›› ወሰደ እናም ተቀጡበት ፡፡


አርቴታ ቡድኑ በፓሱ ጨዋታ ጎል ያስተናገደበትን መንገድ የገለጸው ፍልስፍና በተጫነው መንገድ ነው ፡፡ ቡድኑ ኳስ ሲይዝ በተቻለ መጠን ተስፋፊ እንዲሆን ይፈልጋል ፤ እንዲህ ዓይነቱ አጨዋወት አደጋ ሊጋብዝ መቻሉንም ያምናል ፡፡ አጋጣሚው ግን የግለሰብ ተጫዋች ስህተት ብቻ አድርጎ መናገር ስህተት ላይ ይጥላል ፡፡


የአርቴታ እና የአሰልጣኝ ቡድኑ ሃላፊነት የፓርቴይን ድንቅ የ‹‹ድሪብሊንግ›› ክህሎት አደጋን በቀነሰ መልኩ ለመጠቀም የሚያስችል ሲስተም መገንባት ነው ፡፡ ጥሩ ጅማሬ የሚሆነው ሌላኛው የአርሰናል አማካይ ለፓርቴይ ቀረብ ብሎ እንዲጫወት ማድረግ ነው ፡፡

ቲይረኒ በቀድሞ ብቃቱ ላይ ስለማይገኝ እርሱ ጥሎት የሚሄደውን ቦታ ለመሸፈን አማካይ ክፍሉን ማራቆት ውሃ አያነሳም ፡፡ አርሰናል በግራ መስመር ተከላካይ ስፍራ ላይ ከሚያስፈልገው ከለላ በላይ ለፓርቴይ በአማካይ ክፍል አጣማሪ ማግኘት እጅግ አንገብጋቢው ጥያቄ ነው ፡፡

Girmachew Kebede

Related Posts

St. George wins the City Cup 

Ethiopia’s oldest and most successful club St. George have added another trophy to their cabinet by winning the 19th edition of the Addis Ababa City Cup. This is the club’s…

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

© Getty Images ኢትዮጵያዊቷ ሐዊ ፈይሳ በባንክ ኦፍ አሜሪካ ቺካጎ ማራቶን ባለድል ሆናለች። መገርቱ አለሙ ደግሞ በሁለተኛነት አጠናቅቃለች። ሐዊ ውድድሩን ያሸነፈችበት ጊዜ 2:14:56 ሲሆን የግሏ ምርጥ ሰዓት ነው።  የዓለም ማራቶን ሜጀር…

Leave a Reply

You Missed

St. George wins the City Cup 

St. George wins the City Cup 

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ

የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ