የአለም ዋንጫ ቤተኞች እነማን ናቸው?

by Bereket Tsegaye


አለም በጉጉት የሚጠብቀውና የፕላኔታችን ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር እንደሆነ የሚታመነው የአለም ዋንጫ በሚጢጢዋና የባህረ ሰላጤዋ እንቁ በሆነችው ካታር ሊጀመር በእጅጉ ተቃርቧል። በነዳጅ ሃብት የፈረጠመችው ሃገር እስከዛሬ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ እንግዶቿን በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች። 220 ቢሊዮን ዶላር ለስታዲዮም ግንባታ፣ መሰረተ ልማት እና መሰል ወጪዎች ያወጣችው ካታር ያለፈውን አለም ዋንጫ ካስተናገደችው ሩስያ በብዙ እጥፍ የላቀ ወጪ ማውጣቷ ብዙዎችን አነጋግሯል። ከዋንጫው የራቁት ላቲኖች ብራዚል እና አርጀንቲና የማሸነፍ ቅድመ ግምቱን በአቋማሪዎች ያገኙበትና በስምንት እጅግ ዘመናዊ ስታዲየሞች (በመካከላቸው የ35 ኪ.ሜ ራዲየስ ብቻ መኖሩም አስገርሟል) የሚደረገው የስፖርት ድግስ ከህዳር 11 እስከ ታህሳስ 9 2015 ዓ.ም ድረስ የስፖርት አፍቃሪያንን ቀልብ ይወስዳል።

Brazil last won the World Cup in 2002- gettyimages



ቀጣዩ አጭር ጥንቅርም በአለም ዋንጫው በብዛት የተሳተፉ አስር ሃገራትን ያስቃኘናል። መልካም ንባብ!

10. ኡራጋይ- 14 ተሳትፎ

አርጀንቲናን 4-2 ረተው ዋንጫውን ወደ ላይ ከፍ ያደረጉበትን የመጀመሪያ አለም ዋንጫን ጨምሮ የሁለት ጊዜ ሻሞፒዮን ናቸው። ሁለተኛው ድላቸውም ሌላዋን የላቲን አሜሪካ ጎረቤታቸው ብራዚልን ያሸነፉበት የ1950 አለም ዋንጫ ነበር። ‘ላ ሴሌስቴ’ በሚል መጠሪያ የሚጠሩት ኡራጋውያን በላቲን ከሚገኙ እጅግ ስኬታማ የኳስ ሃገራት ተርታ ይመደባሉ። 15 ጊዜ የኮፓ አሜሪካን ያሸነፉ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ የትልቅ ውድድርን ስኬት ያጣጣሙትም 2011 ላይ ያሸነፉት ኮፓ አሜሪካ ነበረ።

9. ቤልጅየም- 14 ተሳትፎ

አንድም አህጉራዊ ውድድር ያላሸነፈች ሆኖም ግን በተደጋጋሚ የሃገራትን የፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ ከላይ ሆና የመራች ሃገር ተብላ ትጠራለች። በመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ተሳትፎዋ ከመጀመሪያ ዙር ማለፍ አልቻለችም። የመጀመሪያ የውድድሩ ድላቸው ሆኖ የተመዘገበውም እ.ኤ.አ 1970 አለም ዋንጫ ኤል ሳልቫዶርን 3-0 የረቱበት አጋጣሚ ነበር። ከ1982 እስከ 2002 በነበሩ ውድድሮች ለስድስት ጊዜ ያህል የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህም በአምስቱ ከምድብ ማለፍ የቻሉበትን ውጤት አስመዝግበዋል። በብዙ የተጠበቁበትና ወርቃማ ትውልዳቸው ይነግስበታል በተባለው የ2018 የሩስያ አለም ዋንጫ በግማሽ ፍፃሜ በፈረንሳይ 1-0 ተረተው ውድድሩን በሶስተኛነት ጨርሰዋል።

8. እንግሊዝ- 16 ተሳትፎ

አለም ዋንጫን ካሸነፉ 8 ሃገራት አንዷ ነች። 1966 ራሷ ያስተናገደችውን ውድድር ዋንጫውን እዛው ማስቀረት ችላለች። 1990፣ 2018 ውድድሮች አራተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል። ከስኮትላንድ ብ/ቡድን ጋር በጋራም የአለማችን አንጋፋ ቡድን ተብለው በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍረዋል። እ.ኤ.አ 1974፣78፣ 1994 አለም ዋንጫዎች ሶስቱ አናብስት ያልተሳተፉባቸው ውድድሮች ነበሩ።

7. ፈረንሳይ- 16 ተሳትፎ

የወቅቱ የአለም ሻምፒዮን ‘ለ ብለ’ አለም ዋንጫን ደጋግመው ማለፍ ከቻሉ ሃገራት ተርታ ይጠቀሳሉ። ክሮሽያን በፍፃሜው ድል አድርገው ካሸነፉበት ውድድር ማግስትም ዳግም ተጠባቂ ሃገር ሆነው ክታር ይደርሳሉ። የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ድላቸው የተመዘገበውም ራሳቸው ባሰናዱት የ1998 አለም ዋንጫ በፍፃሜው ብራዚልን 3-0 ረተው ዋንጫውን ከፍ ያደረጉበት ውድድር ነበር። በመጀመሪያው የአለም ዋንጫ አውሮፓን ከወከሉት አራት ሃገራት አንዷ ሆነው በታሪክ ይታወሳሉ።

6. ስፔን- 16 ተሳትፎ

እ.ኤ.አ 1930- 77 በነበሩ አለም ዋንጫዎች አራት ጊዜ ብቻ ማለፍ የቻሉት ‘ላ ሮሃዎች’ ከዝያ በኃሏ በነበሩ 11 ተከታታይ ውድድሮች ማለፍ ችለዋል። ወርቃማ ትውልዳቸው የብቃቱ ጫፍ ላይ በነበረበት 2010 የአፍሪካ አለም ዋንጫን ጨምሮ ተከታታይ የአውሮፓ ዋንጫን በ2008 እና 2012 መሃል ማሸነፍ ችለዋል። በቲኪ ታካ የአጨዋወት መንገዳቸው የሚታወቁት ስፔኖች ለ35 ተከታታይ ጨዋታዎች ባለመሸነፍ ከብራዚል እኩል ሪከርድ ይዘው የካታር ውድድራቸውን ይጀምራሉ።

5. ሜክሲኮ- 17 ተሳትፎ

ለ17ኛ ጊዜ በትልቁ ውድድር ላይ በመገኘት ከኮንካ ካፍ (ሰሜንና መካከለኛው አሜሪካ) ሃገራት በቀዳሚነት ‘ለ ትሪዮ’ ይቀመጣሉ። የመጀመሪያ የአለም ዋንጫ ጨዋታቸውን በ1930 ከዩራጋይ ጋር ማድረግ ችለዋል። እ.ኤ.አ 1994 አንስቶ በተደረጉት ሁሉም ውድድሮች ላይ መሳተፍ ከቻሉ ስድስት ሃገራት ተርታም ይሰለፋሉ። በትልቁ ውድድር ድግስ ላይ ሳይሳተፉ የቀሩበት 1934፣38፣74፣82፣90 የአለም ዋንጫዎች ይታወሳሉ። ጥሩ ውጤታቸውም እ.ኤ.አ 1970 ራሳቸው ያስተናገዱትና 1986 ሩብ ፍፃሜ የገቡባቸው ውድድሮች ነበሩ። ባለፉት ሰባት አለም ዋንጫዎች ከብራዚል ጋር ከምድባቸው ያለፉበትን ውጤት ማስመዘገብ ችለዋል።

4. ጣልያን- 18 ተሳትፎ

በአለም ዋንጫና የእግር ኳስ ውድድሮች እጅግ ስኬታማ ከሚባሉ ሃገራት ተርታ ይሰለፋሉ። የአራት ጊዜ (1934፣38፣82 እና 2006) የአለም ሻምፒዮኖቹ በትንሿ ሰሜን መቄዶንያ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ተሸነፈው ከካታሩ ድግስ ቀርተዋል። ይህ ሽንፈትም የአውሮፓ ሻምፒዮን በሆኑ ማግስትም መሆኑ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኖ አልፏል።

3. አርጀንቲና- 18 ተሳትፎ

የሁለት ጊዜ የአለም ሻሞፒዮኖቹ እ.ኤ.አ 1974 አንስቶ በዚህ ውድድር ሲገኙ ለተከታታይ 12ኛ ጊዜ ይሆናል። አልቢሴሌስቴስ በመጀመሪያው አለም ዋንጫ እ.ኤ.አ 1930 ለፍፃሜ ቢደርሱም በዩራጋይ ተሸንፈው ዋንጫውን አጥተዋል። በተመሳሳይ የ2014 ብራዚል አለም ዋንጫ ፍፃሜ በጀርመን 1-0 ተሸንፈው ዋንጫውን ያጡበት ለስኬት ተቃርበው የነበረበት የቅርብ ውድድር ሆኖ አልፏል። አርጀንቲና ያልቀረበችበት የአለም ዋንጫ 1938፣50፣54፣78 አለም ዋንጫዎች ነበሩ።

2. ጀርመን- 20 ተሳትፎ

የ2014 አለም ሻምፒዮኖቹ ‘ዳይ ማንሻፍት’ በብዙ ተሳትፎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ እናገኛቸዋለን። የመጀመሪያ ተሳትፎን እ.ኤ.አ 1934 ላይ ያሳኩት ጀርመናውያን ዋንጫውን ወደላይ ከፍ ለማድረግ 20 አመታትን መጠበቅ አስፈልጓቸዋል፡- 1954 ከአራቱ የሻምፒዮና ክብሮች የመጀመሪያውን አጣጥመዋል። በውድድሩ ታሪክ በጣም ወጥ ከሆኑ ቡድኖች ተርታ የሚመደቡት ጀርመኖች 2014 ብራዚል ላይ ሻምፒዮን ከሆኑበት ውድድር በፊት 2010 ላይ ሶስተኛ ሆነው ማጠናቀቅ ችለዋል። በውድድሩ ታሪክ ለበርካታ ጊዜያት (13 ጊዜ) ግማሽ ፍፃሜውን በመቀላቀል ባለ ሪከርድ ናቸው።

1. ብራዚል- 22 ተሳትፎ

በአለም ዋንጫው የብራዚልን ያህል እጅግ ስኬታማ ብሄራዊ ቡድን ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። የአምስት ጊዜ የአለም ሻምፒዮኖቹ ‘ሴሌሳኦ’ በሁሉም ውድድሮች በመቅረብ ብቸኛ ባለታሪክ ናቸው። ምንም እንኳን ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን ካሸነፉ 20 አመታት ቢቆጠርም ብራዚላውያን ይህን ታሪክ በካታር መቀየር እንደሚችሉ በሰፊው ያምናሉ። እ.ኤ.አ 1958፣62፣70፣94 እና 2002 ብራዚላውያን በአለም ዋንጫው ድል ያሸበረቁባቸው አመታት ሲሆኑ ምናልባትም ይኸኛው መድረክ ስድስተኛውን ዋንጫ ወደ መደርደሪያው የሚመልሱበት እንደሚሆን ይታመናል። በአራት የተለያዩ አህጉራት ውድድሩን በማሸነፍ ብራዚል ባለ ሪከርድም ጭምር ናቸው።

  • Brook Genene

    Brook is a football writer who focuses on sports injuries. He has previously written on local sports for Soccer Ethiopia and Ethiopian Business Review magazine. He also has over a decade of experience covering the Bundesliga and German football for several outlets.

    Related Posts

    St. George wins the City Cup 

    Ethiopia’s oldest and most successful club St. George have added another trophy to their cabinet by winning the 19th edition of the Addis Ababa City Cup. This is the club’s…

    ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

    © Getty Images ኢትዮጵያዊቷ ሐዊ ፈይሳ በባንክ ኦፍ አሜሪካ ቺካጎ ማራቶን ባለድል ሆናለች። መገርቱ አለሙ ደግሞ በሁለተኛነት አጠናቅቃለች። ሐዊ ውድድሩን ያሸነፈችበት ጊዜ 2:14:56 ሲሆን የግሏ ምርጥ ሰዓት ነው።  የዓለም ማራቶን ሜጀር…

    Leave a Reply

    You Missed

    St. George wins the City Cup 

    St. George wins the City Cup 

    ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

    ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

    Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

    Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

    Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

    Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

    የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ

    የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ