
ሰሞኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድኖቻችንን አጨዋወት ለመወሰን ከአሰልጣኞቻችን ጋር ሊመክር ነበር። ጥሩ ጅምር ይመስለኛል። ሆኖም ከዶሮዋና ከእንቁላሏ አይነት ክርክር ውስጥ መግባት ባልፈልግም ፌዴሬሽኑ ጊዜውን በቅድሚያ የሚሰጠው የተጫዋቾች ልማት ላይ ቢሆን እመርጣለሁ።
ጥያቄዎቹም
ተጫዋቾች ከየት እናገኛለን?…እንዴት እናሳድጋቸዋለን?…የት እናሳድጋቸዋለን?…እንዴት እናሰለጥናቸዋለን?
እንዴት ፕሮፌሽናል ተጫዋቾች እናደርጋቸዋለን? መሆን አለባቸው።
እነዚህን ጥያቄዎች በትክክል ከመለስን በኋላ የትኛውንም አይነት የጨዋታ መንገድ ይኑረን ለስኬት ቅርብ እንሆናለን ብዬ አምናለሁ።
ለምሳሌ ፈረንሳይ አንድ የብሔራዊ ቡድን አጨዋወት መንገድ ያላት አይመስለኝም። ሆኖም ግልፅ የሆነ የተጫዋቾች ልማት ሞዴል አላት። በዚህም ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት አራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ደርሳለች። ሁለት ዋንጫ አንስታለች። ሁለቱን ፍፃሜዎች የተሽነፈችውም በመለያ ምት ብቻ ነበር።
በብሔራዊ ቡድኖቿ አጨዋወት የምትታወቀው ስፔንም በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ጭምር የተመሰከረለት ከgrassroot የሚጀምር የወጣቶች ልማት ሞዴል አላት።
የጀርመን እግር ኳስ ለውጥ መነሻም ፌዴሬሽኑን፣ የአውራጃ ፌዴሬሽኖችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና ክለቦችን ያሳተፈ የወጣቶች ተሰጥኦ ልማት ነው። ምናልባት እነዚህ የአውሮፓ ሀገራት የቀደመ የእግር ኳስ ታሪክ ያላቸው ናቸው ካልን እስኪ የኳስ የስኬት ታሪክ የሌላትን ኡዝቤኪስታንን እንመልከት።
ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫ የምትሳተፈው ኡዝቤኪስታን አሁን ማንቸስተር ሲቲ የሚጫወተውን ኩዛኖቭን አይነት ተጫዋቾች ማፍራት የቻለችው ከሰባት ዓመት በፊት “ሰበብ ይብቃኝ” ብላ በጀመረችው የተጫዋቾች ልማት ነው። በወቅቱ በፕሬዚደንታዊ አዋጅ የአምስት ዓመት የተጫዋቾች ልማት ዕቅድ አወጣች። በ14ቱም ክልሎቿ የህፃናት እና ወጣቶች አካዳሚዎችን ገነባች። የስልጠና እና የውድድር ጥራትን በእጅጉ አሻሻለች። ከዚህ በኃላ በተከታታይ የእግር ኳስ ልማትን የሚመለከቱ ህጎችን አውጥታለች። በዚህም ከሁለት ዓመት በፊት የኤዥያ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫን አሸነፈች። ከ23 ዓመት በታች ቡድኗ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ተሳተፈ። ከ17 ዓመት በታች ቡድኗ ለመጀመሪያ ጊዜ የአህጉሩ ሻምፒዮን ሆነ። ዋናው ብሔራዊ ቡድኗም ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ አለፈ። በመህል ኩዛኖቭ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የተጫወተ የመጀመሪያው የሀገሪቱ ዜጋ ሆነ። ግልፅ የእግር ኳስ እና የተጫዋቾች ልማት ስኬት ይህ ነው።
የብሔራዊ ቡድን አጨዋወት መኖር ጥሩ ነው። አጨዋወቱ ያለ ተጨዋቾች ግን ምንም ነው። ዋናው ትኩረትም በርካታ ጥራት ያላቸው ተጫዋቾችን ማፍራት ላይ መሆን አለበት።