
ሰሞኑን በፌዴሬሽኖች የፕሬዚደንት እና የስራ አስፈፃሚ ምርጫዎች አወዛጋቢ ጉዳዮች ሲነሱ ተመልክተናል። በእርግጥ አንደኛው ተወዳዳሪ ከሌላኛው በችሎታ የተሻለ ስለሚሆን ባለው የስፖርት አደረጃጀት ውስጥ እገሌ ከእገሌ የተሻለ ለውጥ ማምጣት ይችላል። ሆኖም ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ለተወዳዳሪዎቹ አስቸጋሪ እንደሚሆን አልጠራጠርም። ስለዚህ ትኩረታችን በሁለት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ቢሆን የተሻለ ይመስለኛል።
የስፖርት አስተዳደር በሁለት ምሶሶዎች የቆመ ነው። በራስ-ገዝነት እና ቅቡልነት ላይ!
- ለፌዴሬሽኖች ራስ ገዝ መሆን ከፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች በተቻለ መጠን ነፃ ሆኖ መንቀሳቀስ ማለት ነው። ይህ ራስ-ገዝነት በሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ህጎች ስር የስፖርት ፌዴሬሽኖች የራሳቸውን ደንቦች ከፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች ነፃ ሆነው ማውጣት፣ ማሻሻልና መለወጥን፤ ከመንግስታዊም ሆነ ከሌላ ሶስተኛ ወገን ነፃ ሆነው የራሳቸውን መሪዎች መምረጥን እና ገንዘባቸውን እና የሰው ኃይላቸውን ያለማንም ጣልቃገብነት ለዓላማዎቻቸው ማዋልን ይጨምራል።
አሁን ባለን የስፖርት አደረጃጀት በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ፌዴሬሽኖቻችን ራስ ገዝ ናቸው ወይም ራሳቸውን በራሳቸው ያስተዳድራሉ ለማለት አልደፍርም። ይህም የሚመነጨው የፌዴሬሽኖቹ የስልጣን ባለቤት ከሆነው ጠቅላላ ጉባዔ አወቃቀር ነው። አብዛኞቹ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል/ከተማ አስተዳደር ወይም በፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በመሆናቸው ድምፅ ሲሰጡም ሆነ ደንቦችን ሲያፀድቁ ከመንግስታዊ ጣልቃገብነት ነፃ የሚሆኑ አይመስልም። ስለዚህ የጠቅላላ ጉባዔ አባላት ማነንት እና አወቃቀር እስካልተቀየረ ድረስ ነፃ የሆነ የፌዴሬሽኖች ምርጫ ሊኖር አይችልም። - ሁለተኛው የስፖርት አስተዳደር ምሶሶ ቅቡልነት ነው። ይህ ከህጋዊ ቅቡልነት ባለፈ ማህበረሰባዊ ቅቡልነትን ይጨምራል። ለምሳሌ ፊፋ በሴፕ ብላተር ዘመን በሙስና እንደተዘፈቀ ሲታወቅ በእግር ኳስ ተከታታዩ ተቀባይነትን አጥቶ እንደነበር ይታወሳል። ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴም የተቀባይነት እጦት አጋጥሞት ያውቃል። ይህን ለማስተካከልም የስነ-ምግባር እና የመልካም አስተዳደር መርሆችን እና መመሪያዎችን አውጥተዋል። አሻሽለዋል። በሀገር ውስጥ ስንቶቹ ፌዴሬሽኖች በማህበረስቡ ዘንድ ቅቡል እንደሆኑ አንባቢ ይፍረድ። ቅቡልነት የሌላቸው ፌዴሬሽኖች ስፖንስር ማምጣት፣ ገበያ መፍጠር እና አዳዲስ ነፃ የሆኑ ደረጃቸው ላቅ ያለ ብዙ ሰዎችን ወደ ስፖርቶቹ መሳብ ሊቸገሩ ይችላሉ። ይህን መቀየር ሌላ ትልቅ የቤት ስራ ነው።
ራስ-ገዝ ባልሆኑ እና ማህበረሰባዊ ተቀባይነታቸው ጥያቄ ምልክት ውስጥ በገባ ፌዴሬሽኖች በሚደረግ ምርጫ ከግለሰቦች ውድድር ባለፈ የስፖርት ማህበራት አደረጃጀትን መቀየር ዋና አጀንዳ እንዲሆን መወትወት ያስፈልገናል።