
ማንቸስተር ዩናይትድ በፕሪምየር ሊጉ ራሳቸውን ያረጋገጡ ተጫዋቾችን ቢያዘዋውርም ቡድኑ ግን በዘላቂነት የሚሻሻል አይመስልም። የእዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቡድኑን ኳስ ከኋላ እንዲመሰርት የሚያደርግበት መንገድ ነው።
መነሻ
(ይህ አጭር ፅሁፍ የዩናይትድን የመጀመሪያ ምዕራፍ ኳስ ምስረታ ብቻ የሚመለከት ነው።)
ስለ ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ 3-4-3/3-4-2-1 ብዙ ተብሏል።
አሞሪም በሶስት ከኳስ ጋር ምቾት የሚሰማቸው የመሀል ተከላካዮች መጫወትን ይመርጣል። ሁለቱ የክንፍ ተከላካዮች ከተከላካይነት ይልቅ የመስመር አማካይ ሚና ይኖራቸዋል። ከተከላካዮቹ ፊት በቴክኒኩ የላቁ ግን ደግሞ ለመፋለም ዝግጁ የሆኑ አማካዮችን ይፈልጋል። ከእነርሱ ፊት ሁለት 10 ቁጥሮች ሆኖም ለቡድኑ የተለያየ ሚና የሚወጡ ተጫዋቾች ይይዛል። የማቴየስ ኩንያ እና ብሪያን ምቡዌሞ ዝውውሮች የእነዚህን 10 ቁጥሮች ልዩነት የሚያጎላ ይመስላል። በአራት ተከላካይ የሚጫወቱ የኳስ ቁጥጥር ቡድኖች ኳስ ከበረኛ በሚጀምሩበት ወቅት ለግብ ጠባቂያቸው የተሻለ ኳስ የማቀበያ አማራⶐችን በሁለቱ የመሀል ተከላካዮች፣ በፉልባኮቻቸው እና በስድስት ቁጥሮቻቸው ይፈጥራሉ። ይህ በተለይ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት በቴክኒኩ የላቀ ለተጋጣሚ ጀርባውን ሰጥቶ ኳስ መቀበል የሚችል አማካይ ቡድኑ እንዲኖረው ያደርጋል። ይህ ከሁለቱ የመሀል ተከላካዮች ጋር ሲደመር ከኃላ የዳይመንድ ቅርፅ እንዲኖር በማስቻል ለተጋጣሚ ጫና የማይመች ኳስ አመሰራረት ይፈጥራል። ለምሳሌ ምስል ዜሮ ግብ ጠባቂው ያለውን ኳስ የማቀበያ አማራጭ ያሳያል። ምስሉ ከባርሳ አካዳሚ የተገኘ ነው።

ሩበን በሁለት የመሀል ተከላካይ የሚጫወቱ ቡድኖች ያላቸውን ኳስ የመመስረት አማራጭ በሶስት ተከላካይ ቡድኑ ላይ ለመፍጠር ያደረገው በመጀመሪያው ምዕራፍ ኳስ ምስረታ የመሀል ተከላካዩን ወደ አማካይነት መቀየር ነው።
ኳስ ከኋላ በትክክል መመስረት ከፊት መስመር ያሉት የቡድኑ ፈጣሪ ተጫዋቾች ከተጋጣሚ ተጫዋቾች ጋር በተሻለ ሁኔታ አንድ ለአንድ እንዲገናኙ ያደርጋል። የአሞሪም ቡድን ግን ይህን ለማድረግ ይቸገራል። የእነዚህ ምክንያቱ ደግሞ አሞሪም የመሀል ተከላካዩን አማካይ እያደረጉ ማስጀመሩ ነው።
የአሞሪም ኳስ ምስረታ በሊድስ ጨዋታ

በምስል አንድ እንደምንመለከተው ግብ ጠባቂው ኳስ ሲይዝ የቡድኑ የመሀል ተከላካይ የሆነው ማትያስ ደ ሊት አማካይ ሆኖ ኳስ ለመቀበል ተዘጋጅቷል። ሆላንዳዊው የላቀ አማካይ ቢሆን ኖሮ ይህ በራሱ ችግር አይኖረውም። ሆኖም ለተጋጣሚ ጀርባን ሰጥቶ ኳስ መቀበል አይችልም። ቢቀበልም እንደ አማካዮች ቶሎ መዞር አይችልም። ወደ መስመር ተከላካዮቹ በፍጥነት ኳስ ሰውሮ ማቀብልም የሚችል አይመስልም። በዚህ ምክንያትም ቡድኑ መሀል ለመህል ወደ ቀጣዩ ዞን ከኳስ ጋር ለመግባት ይቸገራል። አንድ ለአንድ ማለፍም አይችልም። በዚህ ምክንያት ቡድኖች የበላይ ከሚሆኑባቸው ነገሮች አንዱ የሆነውን የጥራት የበላይነት (qualitative superiority) ዩናይትድ አያገኝም። ሌላኛው የበላይነት ደግሞ በሁለት ተጫዋቾች መካከል ባለ መናበብ የሚመጣ የበላይነት ነው። ካሴሚሮ እና ደ ሊት አንድ ሁለት ተቀባብለው ከችግር ይወጣሉ ብሎ ማሰብ ይከብዳል።
በምስሉ እንደምንመለከተው የመሀል ተከላካዩ ወደ መህል በመግባቱ ምክንያት በሚፈጠረው ግትር የሳጥን ቅርፅ ምክንያት ቡድኑ በተጫዋቾች ቦታ አያያዝ ምክንያት በተጋጣሚ ላይ ሊኖረው የሚችለውን የቦታ የበላይነት (Positional Superiority) አጥቷል። በምስሉ ላይ የኩኝያን ቦታ አያያዝ ተመልከቱት። የሊድስ የቀኝ መስመር ተከላካይ ብራዚላዊውን ከመከተል እና ከምስል ውጭ የሆነውን ዲዬጎ ሊዮንን በመያዝ መካከል ግራ ሲጋባ ታያላችሁ። የሊድስ የመሀል ተከላካይም በጥልቀት አዲሱን ፈራሚ ለመከተል ያመነታል። ይህ ኩኝያ በቦታ አያያዙ ምክንያት የፈጠረው የበላይነት ነው። የዩናይትድ አማካይ ክፍል በአብዛኛው ተለዋዋጭ ስላልሆነ እና ለተጋጣሚ ለመዘጋጀት ቀላል ስለሆነ ይህን አይነት የበላይነት አጥቷል።

በምስል ሁለት እንደምንመለከተውም የሊድስ 4-2-4 የመከላከል ቅርፅ እንዴት በቀላሉ የዩናይትድን አማካይ ክፍል ከጨዋታ ውጭ እንዳደረገው እንረዳለን። ይህ አሞሪም ሁሌም በሚከተለው ተመሳሳይ ከኃላ የመመስረት አጨዋወት ምክንያት የመጣ ነው።

ምናልባት የተጫዋቾች ለውጥ ችግሩን ይፈታዋል እንዳይባል በምስል ሶስት ሁሉም ተጫዋቾች ከተቀየሩም በኃላ ችግሩ ተመሳሳይ እንደሆነ ይታያል። በሁሉም ምስሎች እንደሚታየውም ዩናይትድ ሁለቱን 10 ቁጥሮች ( በምስል አንድ እና ሁለት ብሩኖ እና ኮልየር፣ በምስል 3 ሜይኑ እና ማንታቶን) በኳስ ለማግኘት ይቸገራል። ምክንያቱም ኳስ የማቀበያ መንገዱ (passing lane) በስድስት ቁጥሮቹ (በምስል አንድ እና ሁለት በደ ሊት እና ካሴሚሮ፣ በምስል ሶስት በማጓየር እና ኡጋርቴ) ተዘግቷል። ይህ የአሞሪም የኳስ ምስረታ መንገድ የፈጠረው ሌላኛው ችግር ነው። በዚህም ዩናይትድ ኳስ በሚመሰርትበት ወቅት አንድ አገልግሎት የማይሰጥ ተጫዋች ይኖረዋል ማለት ነው። ይህን ችግር ለመፍታት እና ኳስ ለማግኘት ብሩኖ በጥልቀት ወደ ኋላ ሲመለስ ወይም ወደ መስመር ሲወጣ ይታያል (ምስል አራት እና አምስት) ።


በዚህ አጨዋወት የቡድኑ ኳስ ምስረታ ብቸኛ መንገድ በመስመር መጫወት እና ኳስ በረጅሙ መምታት ብቻ ይሆናል።
መፍትሄው ምንድነው?
ከካሲሜሮ እና ኡጋርቴ የተሻለ አማካይ በተወሰነ መልኩኳስ አመሰራረቱን ሊያሻሽለው ይችላል።ሆኖም የተሻለው መፍትሄ የቡድኑን ኳስ የመመስረት ቅርፅ ማሻሻል ነው።በሶስት የመሀል ተከላካይ ከሚጫወቱ ቡድኖች መካከል የሲሞኔ ኢንዛጊው ኢንተር ሚላን የተሻለ መፍትሄ አግኝቶ ነበር። ቀጣዮቹ ምስሎች የተወሰዱት ከቻምፕየንስ ሊጉ የባየርን ሙኒክ የመልስ ጨዋታ ነው።

ኢንተር የወረቀት አሰላለፉ እንደሚያሳየው በ3-5-2 ይጫወታል። ሆኖም ኳስ ከበረኛ በሚመሰርትበት ጊዜ የአጨዋወት ቅርፁ የተለየ ነው። በምስል ሰባት የቀኝ የመሀል ተከላካዩ ፓቫር እና የመሀል ተከላካዩ አቼርቢ በሶመር ግራ እና ቀኝ ኳስ ለመመስረት ይዘጋጃሉ። የግራ የመሀል ተከላካዩ ባስቶኒ የግራ መስመር ተከላካይ ይሆናል። የቀኝ ክንፍ ተከላካዩ ዳርሚያን የቀኝ መስመር ተከላካይ ይሆንና ኳስ ለመመስርት ይዘጋጃሉ። የግራ ክንፍ ተከላካዩ ዲማርኮ ደግሞ ወደፊት ተገፍቶ የአጥቂ መስመሩን ይቀላቀላል።

በዚህ አመሰራረት አማካዮቹ ከግብ ጠባቂው እና ከመሀል ተከላካዮቹ ኳስ መቀበል ይችላሉ። በገዛ የቡድን አጋራቸው የሚዘጋ ኳስ የማቀበያ/መቀበያ መንገድም የለም። አሞሪም ተከታታይ ውጤት አምጥቶ በኦልድ ትራፎርድ ለመቆየት አንዱ መፍትሄ ይህ ይመስለኛል። አልያም ኳስ መመስረቱን እርግፍ አድርጎ ትቶ በረጅም ኳስ እየተጫወቱ ለሁለተኛ ኳስ መፋለም ግዴታ ይሆናል። ይህ ደግሞ በደጋፊው ብዙም ላይወደድ ይችላል።