
መቶ ሃያ ደቂቃዎችን ከፈጀ እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ መልስ የአፍሪካ ተወካይ የሆነችው ሞሮኮ ስፔንን በመለያ ምት 3-0 በመርታት የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚ መሆን ችላለች፡፡ ይህም ከካሜሩን፤ሴኔጋል እና ጋና በመቀጠል የአለም ዋንጫ ሩብ ፍጻሜን የተቀላቀለች አራተኛዋ አፍሪካዊት ሀገር አድርጓታል፡፡
ሁሉም ተጫዋች ድንቅ እንቅስቃሴን አሳይቷል በማለት ከጫወታው በኋላ አስተያየቱን የሰጠው ግብ ጠባቂው ያሲን ቦኖ ከተመቱበት ሶስት የፍጹም ቅጣት ምቶች ሁለቱን በማዳን የጫወታው ኮከብ መሆን ችሏል ( ሌላኛዋ ፍጹም ቅጣት ምት በግቡ ቋሚ ተመልሳለች)፡፡
በጫወታው ስፔኖች እንደተለመደው እና እንደተጠበቀው የኳስ ቁጥጥር ብልጫን መያዝ ቢችሉም ከአንድ ኢላማውን ከጠበቀ ሙከራ ውጪ ቦኖን መረበሽ አልቻሉም፡፡ የጫወታው ምርጥ ዕድል የተገኘው 120 ደቂቃ ሊጠናቀቅ ሲል በሳራቢያ በኩል ነበር፡፡ እንዳመከነው ፍጽም ቅጣት ምት ሁሉ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡
ድሉ ሙሉ አፍሪካውያንን ያስፈነደቀ እና ሞሮኮአዊያንን ደግሞ ያኮራ ሆኗል፡፡ ከጫወታው በኋላ በውጤቱ የተደሰተው አንድ የሞሮኮ ጋዜጠኛ “ ጥያቄ የለኝም፡፡ ነገር ግን ቦኖ እና አሰልጣኝ ዋሊድን አመሰግናለሁ፡፡ የ40 ሚሊየን የሞሮኮ ህዝቦችን እምነት ቦኖ አግኝተሃል“ በማለት እንባ ተናንቆት ተናግሯል፡፡
ሶፊያን አምራባት ከጉዳት ጋር እየተገለ የመሃል ሜዳውን ፍልሚያ በተወጣበት ፤ ዋሊድ ቸዲራ ከአንድም ሁለት ወርቃማ ዕድሎችን ባልተጠቀመበት፤ ሮማን ሳይስ ከእነጉዳቱ ጨዋታዉን በጨረሰበት እና ሶፊያን ቡፋል ለሎሬንቴ ጭንቀት ሆኖ ባመሸበት ጨዋታ የፒኤስጂው የቀኝ መስመር ተከላካይ አሽራፍ ሃኪሚ ተወልዶ ያደገባትን ሀገር በቄንጠኛ ፍጹም ቅጣት ምት ከውድድሩ አሰናብቷታል፡፡
ሰርጂዮ ቡሽኬትስ እድለቢስ እንደሆኑ እና ሁልጊዜም በፍጹም ቅጣት ምት የሚያልቅ ጨዋታ ውጤቱ እንደማይታወቅ ገልጻል፡፡ የቡድኑ አሰልጣኝ ሉዊስ ሄነሪኬ በበኩላቸው ቡድናቸው 11 ሙከራዎችን ሞክሮ አንድ ብቻ ኢላማውን የጠበቀ እንደነበር ሲያስታውሱ በቡድናቸው እንደኮሩ እና የፍጹም ቅጣት መቺዎቹን የመረጡት እራሳቸው ስለሆኑ ኃላፊነትን እንደሚወስዱ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ሞሮኮ ከፖርቹጋል ጋር በሩብ ፍጻሜው የምትገናኝ ሲሆን ስዊዘርላንድን 6-1 ከቀጣችው ቡድን ቀላል ፈተና እንደማይጠብቃት መገመት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን ወደ ግማሽ ፍጻሜ በማለፍ ደማቅ ታሪክን የመጻፍ ትልቅ ዕድል አላት፡፡