
written by Leoul Tadesse
የዘንድሮ ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ለእኩል የቀረበ እድል ያላቸውን ቡድኖችን አገናኝቷል። አራቱም ቡድኖች የተለያየ የአጨዋወት ማንነት ያላቸው ቡድኖች መሆናቸውም ጨዋታዎቹን አጓጊ ያደርጋቸዋል። ተፋላሚዎቹን የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ግን አለ – የአሰልጣኖቹ አሻራ በጉልህ የሚታይባቸው የ’አሰልጣኝ ቡድን’ መሆናቸው። አሰልጣኞቹ ቡድኖቹን ያሰለጠኑባቸው ጊዜ ርዝመት ቢለያይም፣ ሁሉም ከቀደምቶቻቸው ፍፁም የተለዩ ቡድኖችን ገንብተዋል። ሚኬል አርቴታ ለዓመታት ችግር ውስጥ የነበረ፣ መነሳት እና መፎካካር ያቃተውን ቡድን አፍርሶ ቀስ በቀስ በጡብ ላይ ጡብ እየጨመረ ራሱን የመሰለ ጠንካራ፣ ኮምጫጫ፣ ተቀያያሪ እና በሁሉም ዘርፎች የላቀ ቡድን ገንብቷል። ሲሞኒ ኢንዛጊ የአንቶኒዮ ኮንቴን 3-5-2 ቢያስቀጥልም፣ በተለይ ኳስ ይዞ በመጫወት፣ በፈጠራ፣ በማጥቃት እና በተለዋዋጭነት ፍፁም የተለየ እና የተሻለ ኢንተርን እያሳየን ይገኛል። ሉዊስ ኤንሪኬ የ’ቀበጦቹን ከዋክብት’ ፒኤዤ፣ ወደሮጠው ያልጠገቡ፣ ታታሪ፣ ለቡድን የሚለፉ ወጣቶች አስደናቂ ቡድንነት ቀይሮታል። ሀንሲ ፍሊክ በበኩላቸው ባለፈው የውድድር ዘመን ደካማ የነበረው ባርሴሎናን በሁሉ ረገድ ድንቅ የሆነ፣ በርካታ ጨዋታ-ቀያሪ ተጨዋቾችን የያዘ እና ‘ትሬብል’ ለማሸነፍ የሚጫወት ቡድን አድርገውታል፤ የቡድኑን ግርማ-ሞገስም መልሰውታል። ግማሽ ፍፃሜውም ከተጨዋቾች ጥራት ይልቅ ታክቲክ እና ስነ-ልቦና የሚወስነው የሚመስለው በአሰልጣኞቹ የእስካሁን ስኬት የተነሳ ነው።
ቻምፒየንስ ሊጉ የዘንድሮ ባሎን ዶ’ር ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ከዋክብትን እያንጠባጠበ እዚህ ደርሷል። ሳላህ፣ ቫንዳይክ፣ እምባፔ እና ሁሊያን አልቫሬዝ በግላቸው (ሳላህ እና ቫን ዳይክ በሊጉ ከቡድናቸውም ጋር) ድንቅ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ቢገኙም፣ የሀገራት ውድድር በሌለበት ዓመት ትኩረት የሚደረገው ቻምፒየንስ ሊግ ላይ በመሆኑ እድሉ ያመለጣቸው ይመስላል። ጥሩ ያልሆኑት ቪኒሲዩስ፣ ቤሊንግሀም እና ሀላንድም እንደዚያው። በእኔ እምነት አሁን አምስት/ስድስት የተሻለ እድል ያላቸው ተጨዋቾች አሉ። ሶስት ከባርሴሎና (ራፊንሀ፣ ያማል እና ፔድሪ)፣ ሁለት ከፒኤዤ (ዴምቤሌ እና ቪቲኒሀ) እና ላውታሮ ማርቲኔዝ። አርሰናል ሻምፒዮን ከሆነ ምናልባት ራይስ ወይም ሳካ የ2006ቱ የፋቢዮ ካናቫሮን ያልተጠበቀ በጥቂት ጨዋታዎች ግዙፍ ተፅዕኖ የተገኘን አሸናፊነት ይደግሙት ይሆናል።
የሩብ ፍፃሜው ምርጥ ተጨዋቾች (ብዙ የተባለላቸውን አይጨምርም):- ፒኤዤ ከዶናሩማ እስከ አጥቂው ዴምቤሌ በሁሉ ረገድ የተሟላ ቡድን ነው። በተለይ ስለአማካይ ክፍሉ ብዙ ተብሏል። አሁን ግን ፉልባኮቹ አችራፍ ሀኪሚ እና ኑኖ ሜንዴሽን ግን በተለየ ማንሳት አለብኝ። ማጥቃት የሚወዱት እና በኤንሪኬ ነፃነታቸውን ያገኙት ጥንድ የተጋጣሚያቸውን አጥቂዎች ከማቆም አልፈው አስቶን ቪላ ላይ ሶስት ወሳኝ ጎሎች አስቆጥረዋል። ሀኪሚ በቀኝ እና ሜንዴሽ በግራ ሲያሻቸው በውጪ በኩል እየደረቡ፣ ሲፈልጉ ወደውስጥ እያጠበቡ የቪላን ተከላካዮች ሲያሸብሩ ነበር።
ለመድፈኞቹ ድል የራይስ እና ሳካ ተፅዕኖ ቢጎላም ልዊስ-ስኬሊ እና ሜሪኖም የሚገባቸውን ክብር ቢያገኙም ሌሎች ሊነሱ የሚገባቸውም አሉ – ቲምበር እና ኪቪዮር። ስለሁለገቡ ሆላንዳዊ ምን ማለት ይቻላል? ተጨዋች ከACL ጉዳት ተመልሶ እንዴት እንዲህ አይነት ድንቅ የውድድር ዘመን ያሳልፋል? ሲከላከል ጠንካራ፣ ሲያጠቃ ደፋር፣ ከስህተት የፀዳ፣ ግርግር የሌለበት የስራ ሰው። ፖሊሹ የመሀል ተከላካይ በበኩሉ የብዙዎችን ስጋት እና ጥርጣሬ ያስረሱ 180 ደቂቃዎች አሳልፏል። ከመጀመሪያው ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በኋላ ኪቪዮር ድንቅ ነበር። ለሶስት ወራት አንዴም ሳይጫወት ወንበር ሲያሞቅ ቆይቶ በድንገት ይህ ኃላፊነት ወድቆበት በስኬት መወጣት የሚያስደምም ነው።
የምርጥ ዓመታቱ ብቃቱን እና አስፈሪነቱን ያሳየን ራሽፈርድ፣ በመጀመሪያው ጨዋታ እድሎቹን ባይጠቀምም በመልሱ ጨዋታ ሀት-ትሪክ ሰርቶ ካታላኖቹን ያስደነገጠው ጊራሲ፣ አምስት ጎሎች ቢቆጠሩበትም ፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ በርካታ ሙከራዎችን ያዳነው ኩርቷ ከተሸናፊ ወገን ቢሆኑም በግላቸው የሚኮሩበትን ብቃት አሳይተዋል።