የካሳሜሮ አስደናቂ የእግር ኳስ ጉዞ

Photo Credit- Getty Images

የሬያል ማድሪድ ሃላፊዎች ከ ብራዚል የመጣው ደቃቃ ጠይም ልጅ ፊት ተቀምጠዋል። የውሰት ውሉን ፊርማ ተፈራርሞ ለ ሪያል ማድሪድ ካስቲያ(ሁለተኛ ቡድን) ለመጫወት ተስማምቷል። ምን እንደሚሰማው ጠየቁት፤ “አምስት ጨዋታዎችን ለዋናው ቡድን እንድጫወት እድል ስጡኝ እና ብቃቴን ታዩታላቹ፣ መጫወት እችላለሁ ለዋናው ቡድን…”በአንድ ጊዜ ክፍሉ በሳቅ ተሞላ። በቦታው የነበረው የወቅቱ ዳይሬክተር ጀነራል ሆዜ አንጌል ሳንቼዝ ሲያስታውስ፣ “እነዝያን ቃላት ሲያወጣ ፊቱ ላይ አንድም የጥርጣሬ ስሜት አይነበብም። በራሱ ያለው መተማመን ጠንካራ የታዳጊነት ጊዜ እንደነበረው ያሳውቃል” ብሎ ነበር። 

   እንደብዙዎቹ የብራዚል ኮከቦች ሁሉ ካሳሚሮም ከሳዎ ፖሎ ነው የተገኘው። ሳዎፖሎ ከተቀሩት የብራዚል ክፍለሃገራት በድህነት ቢታወቅም ትንሹ ካሴ በከፋ ድህነት ውስጥ ነበር ያደገው። እናቱ ማግዳ ያለአባት ካሰሚሮን እና ሀለት ወንድሞቹን በብዙ ችግር አሳድጋለች። ከድህነታቸው የተነሳ ቀን አብረው ውለው ሌሊቱን ሌሎች ዘመዶች ቤት ተጥግተው የተለያየ ቦታ ነበር የሚያድሩት። ከስኬቱ እና ዝናው በኋላ በቅርቡ በአንድ ቃለ-መጠይቅ ላይ ጠያቂው አንድ ነገር ከኪሱ አውጥቶ ለካሳሚሮ አቀበለው። ካሳሚሮ ፊቱ ላይ ሳቅ፣ሃዘን፣እና መገረም እየተፈራረቁበት በእጁ የያዘውን አተኩሮ እያየ“በልጅነቴ ይሄ ጣፉጭ መጠጥ ሃያ ሳንቲም ነበር የሚሸጠው። ግን አንድም ቀን ቀምሼው አላውቅም ነበር። በህልሜም በእውኔም ጣዕሙ ምን ይሆን? እያልኩ አስብ ነበር” ብሎ ምላሹን ሰጥቶት ነበር።

ለካሳሚሮ እና ቤተሰቡ ከድህነት መውጫ መንገድ እንደ አብዛኞቹ የሃገሩ ልጆች ሁላ እግርኳስ ነበር። በ 11 ዓመቱ የሳዎ ፓውሎን የታዳጊዎች ቡድን ተቀላቀሎ እራሱን ለማስመስከር ብዙም ጊዜ አልፈጀበትም። የመሪነት ባህሪው ጎልቶ ይታይ ነበር። ከታዳጊው ቡድንም ይሁን በዋናው ሳዎ ፓውሎ ቡድን በትንሽ እድሜው የአምበልነት ሃላፊነት ተወጥቷል። በዚህ ስኬት ውስጥ ግን ሌላ ፈተና አብሮ ተከተለ፣ መዝናናት፣ ማምሸት እና እንስቶች። በሳዎ ፓውሎ ያሰለጥኑት ኤመርሰን ሌያኦ በ 2011 ሲናገሩ “ የካርላኦ ተሰጥኦ የሚካድ አይደለም። ከእድሜው በላይ የሆነ ተጨዋች ነው። አእምሮው ግን በሌሎች ነገሮች ተወስዷል፣ የመጫወቻ ጫማውን እረስቶታል” ብለው ነበር። (ካርላኦ በብራዚል ይጠራበት የነበረው ስሙ ነው። ክካርሎስ ሄንሪክ ከሚለው የመጀመርያ ስሙ)

የእግርኳስ ህይወቱ መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመ ቢመስልም፣ በ 2009 ናይጄሪያ ላይ በተደረገው የዓለም ከ 17 ዓመት በታች ቻምፕየንሺፕ ላይ የሬያል ማድሪድ መልማዮች እይታ ውስጥ ገብቶ ነበር። የመልማዮቹ ትኩረት ሌላኛው ኮከብ ኔይማር ላይ ቢሆንም፣ በውውድሩ ላይ በካሳሚሮ እንቅስቃሴም ተደምመው ተመልሰዋል። ከ አራት ዓመታት በኋላም ለሙከራ ወደ ሬያል ማድሪድ ካስቲያ በውሰት ውል አስፈረሙት። 

የካሳሚሮ ፕሮፌሽናል የእግርኳስ ህይወት ላይመለስ ለበጎ የተለወጠውም በሬያል ማድሪድ ካስቲያ በሚጫወትበት ጊዜ ነበር። የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ጆዜ ሞውሪንዮ ከቡድናቸው ጋር አብረው እንዲሰለጥኑ ለተወሰኑ ካስቲያ ተጨዋቾች ጥሪ ያቀርባሉ። ከነዚህ ተጨዋቾች መካከልም ካሳሚሮ አንዱ ነበር። ይሄን ትልቅ እድል እንዳገኘ እያሰበ በቫልዴቤባስ የመለማመጃ ሜዳ ለልምምዱ መጀመር እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት የሁለት ሰዎች ንግግር ወደጆሮው ይገባል። የ ጆዜ እና ምክትላቸው ካራንካ ንግግር ነበር።              “ ብራዚላዊው ልጅ ጥሩ ይመስላል፣ዛሬ በደንብ ጉልበት ሰጥቶ ከነጠቀ ለቤቲሱ ጨዋታ እናስገባው። ምን ታስባልህ?” የሚል ነበር። ይሄን የሰማው ካሳሚሮ ነገ የለም የተባለ ያህል በልምምዱ ክፍለጊዜ ያለውን ሁሉ አውጥቶ አሳየ። ምሽት ላይም ጆዜ ወደ ክፍሉ ሄደው ለቤቲሱ ጨዋታ እንደሚሰለፍ አበሰሩት። ከዓመታት በኋላ የልምምድ ሜዳውን ክስተት አስታውሶ ለጆዜ ከምክትላቸው ጋር የተነጋገሩትን እንደሰማ ሲነግራቸው፤ “እንደምትሰማ አውቄ ነበር፣ ሆን ብለን ነው እንድትነሳሳ ያደረግነው” እንዳሉት ያስታውሳል።

ወደዋናው ቡድን የተቀላቀለው ካሳሚሮ ከጆዜ ብዙ ምክርን እንዳገኘ ይመሰክራል። በፕሮፌሽናልነት እራሴን እንድመለከት አድርገውኛል ይላል። የሁለቱ ወዳጅነት ግን ብዙም አብሮ መዝለቅ አልቻለም። ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በአንቸሎቲ ተተክተው ነጩን ቤት በብዙ ውዝግብ ለቀቁ። አንቸሎቲ ለመጫወት ባሰቡት የጨዋታ እቅድ ካሰሚሮ ይሆነኛል ብለው አለማሰባቸው እና በቡድኑ እንደ ዣቢ ኣሎንሶ፣ ከዲራ እና ኢላራሜንዲ አይነት አማካይ ተከላካዮች መኖር የብራዚላዊውን የቋሚነት እድል አመናመነው። ክለቡ ታሪክ በሰራበት የ አስረኛው የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ ላይ እንኳን ተጠባባቂ መሆን አልቻለም ነበር። 

የነጩ ቤት ህይወቱ ወደማብቂያው የተጠጋ የመሰለው ካሳሚሮ ለፖርቶ በውሰት ተሰጠ። በወቅቱ ከ ጁልየን ሎፕቴጊ ጋር የመስራትን እድል ማግኘቱ በብዙ ጠቅሞታል። አማካይ ክፍልን መቆጣጠር ክህሎት፣ ታክቲካል ፋውሎችን እና የቅጣት ምት ቴክኒኩን አሳደገ። በውድድር ዓመቱ የፖርቹጋል ሊግ ምርጡ ተጨዋች ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በበርካታ ክለቦች እይታ ውስጥ መግባት ቢችልም በውሰት ውሉ ውስጥየተካተተውን ‘ከዓንድ የውውድር ዓመት ውሰት በኋላ መልሶ የመጥራት መብት’ ተጠቅመው ሬያሎች አዲስ የ አምስት ዓመት ኮንትራት አስፈረሙት። ብዙም በአሰልጣኝነት ባይቆይም፣ ራፋ ቤኒቴዝ በካሳሚሮ ላይ እምነት አሳድሮ ነበር። የሬያል አማካይ ክፍል አንቀሳቃሽ እና መሪ መሆኑን ተለማመደው። ዓለም ሁሉ ተስማምቶ የቦታው ምርጡ ተጨዋች ብሎ ለመሰየም ግን የበቃው በዚነዲን ዚዳን ስርነበር።

ብዙዎች ስለ ዚዳኑ ሬያል ማድሪድ ሲያስቡ ትኩረታቸው በፊት መስመር ተጨዋቾቹ ቤል፣ሮናልዶ እና ቤንዜማ ላይ ቢሆንም የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ካሳሚሮ እጅግ ወሳኝ ነበር። ሬያል ማድሪድን የገጠመ አሰልጣኝ ሁሉ ስሙን ሳያነሳ እና ሳያደንቅ አያልፍም። የታሪካዊው ቡድን አንድ አካል በመሆንም ሦስት ተከታታይ የቻምፕየንስ ሊግ ዋንጫዎችን አነሳ። የ ክሩዝ፣ ካሰሚሮ እና ሞድሪች ጥምረት ተብሎ ለታሪክ ሲነሳ በሚኖረው ጥምረት ምሶሶው እርሱ ነው። ስለብቃቱ አስተያየት ሰጪዎችን ጥርጣሬ ውስጥ ይከት የነበረው ተጨዋች በአንድ ድምፅ  የሚጫወትበትን ሚና በስሙ አሰየመው። 

ከጨዋታን ማንበብ እና ውሳኔዎችን በተገቢው ሰዓት እና ቦታ ከመወሰን ባለፈ የካሳሚሮ አእምሯዊ ጥንካሬ እጅግ አስገራሚ ነው። ተራ የሊግ ጨዋታም ይሁን የአውሮፓ ቻምፕየንስ ሊግ ፍፃሜ ፊቱ ላይ የሚነበበው የተረጋጋ ስሜት ሁሌም ተመሳሳይ ነው። የእርጋታ። ጨዋታው በጦዘበት ቅፅበት ሜዳው ውስጥ ከእርሱ የበለጠ የተረጋጋ ሰው አይገኝም። ይህ ባህሪውም ከዳኞች ለተመለከታቸው በቁጥር ያነሱ የማስጠንቀቅያ ካርዶች ምክንያት ነው። 

በቀጣይ ማረፍያው ብራዚላዊው መለኛ በብዛ ምክንያቶች የወጣበትን ዋጋ ያህል ላይንቀሳቀስ ወይም የነጩን ቤት ገድሉን ሊደግም ይችላል። ያለጥርጥር ግን መናገር የሚቻለው በአዲሱ ቀጣሪዎቹ ቢሮ ፊት ለፊታቸው ተቀምጦ የሚያስበውን እና ቡድኑን እንዴት ማሻሻል እንደሚቻል ሃሳቡን ለመግለጥ ቃላት እንደማያጥሩት ነው።

  • Minyahel Mamo

    Related Posts

    አቋማቸው የዋዠቀ አምስት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች

    ሁለቱ የማንችስተር ክለቦችን ጨምሮ 5 ቡድኖች ባለፉት ሶስት አመታት የዋዥቀ አቋምን እንዳሳዩ CryptoCasinos  ያወጣው ቁጥራዊ መረጃ ያሳያል:: የ20 ጊዜ የፕሪሚየር ሊግ አሸናፊዎቹ ከትልቁ ዋንጫ ከራቁ 12 አመታት ተቆጥረዋል:: ከ2022/23 አንፃር…

    በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው የአጥቂዎች ዝውውር 

    ከጥቂት አመታት በፊት ይህ ነው የሚባል የዘጠኝ ቁጥር ተጫዋች አልነበረም፡፡ ይህም በርካታ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦችን ያሳስብ ነበር፡፡ በተለይም በ2010ቹ ገነው ከወጡት እንደሉዊስ ስዋሬዝ ፤ ሰርጂዮ አግዌሮ ፤ ካሪም ቤንዚማ ፤…

    Leave a Reply

    You Missed

    St. George wins the City Cup 

    St. George wins the City Cup 

    ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

    ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

    Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

    Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

    ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

    Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

    Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

    የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ

    የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ