
አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ክለቦች በመንግስት ቀጥተኛ በጀት የሚተዳደሩ ናቸው:: ነገር ግን መንግስት ለክለቦች ቀጥተኛ በጀት መስጠት ቀስ በቀስ ማቆም እንዳለበት አምናለሁ። ምክንያቱም በምቹ ሁኔታዎች ውስጥ ክለቦች የራሳቸውን ገቢ ማግኘት ይችላሉ። ይህም ስፖርቱን ለትርፍ መጠቀም የሚፈልጉ ባለሀብቶችን ወደ እግር ኳሱ ያመጣቸዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ የስፖርት ክለቦች የንግድ ተቋም መሆን የሚችሉ አይመስልም።
ህጉ ምን ይላል?
በተለምዶ መመሪያ አንድ የሚባለው በወቅቱ በነበረው ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣው መመሪያ ቁጥር 1/2003 ስለ ስፖርት ክለቦች አመሰራረት አንድ አንቀፅ ይዞ ነበር። የመመሪያው አንቀፅ 14 የስፖርት ክለቦች ስፖርቱን ለንግድ (ለትርፋማነት) በሚጠቀሙ ባለሀብቶች ሊመሰረቱ እንደሚችሉ ይደነግጋል። ከዚያ ቀጥሎ በተሻሻሉት መመሪያ 75/2013 እና 622/2014 ግን ይህ አንቀፅ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀር ተደርጓል።
ታዲያ መመሪያው ፈቅዶ ከነበረ ነጋዴ ክለቦች ለምን አልተቋቋሙም?
ነጋዴ የሆናችሁ እንደምታውቁት የንግድ ፈቃድ ስታወጡ የንግድ ስራ መስክ /field of business/ እና የተሰማራችሀብት የንግድ ስራ /type of activity/ በንግድ ፈቃዳችሁ እና በምዝገባ የምስክር ወረቀታችሁ ላይ ይኖራል። የንግድ ስራ መስኩ እና የንግድ ስራው ደግሞ ራሳቸውን የቻለ “ኮድ” ይኖራቸዋል። የንግድ ፈቃድ እና ምዝገባ የሚሰጠው ደግሞ በንግድ ምዝገባና የፈቃድ አዋጅ ቁጥር 980/2008 መሰረት ሆኖ ድርጅቱ የሚሰማራበት የንግድ ዘርፍ ኮድ የሚሰጠው ደግሞ የኢትዮጵያ የንግድ ስራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያ ቁጥር 556/2013 መሰረት ነው። ይህ መመሪያ የስፖርት ክለብነትን እንደ የንግድ ዘርፍ አያውቀውም። ከዚህ መመሪያ በፊት በ2003 እና በ2005 የወጡት የኢትዮጵያ ንግድ ስራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያዎችም የስፖርት/እግር ኳስ ክለብነትን እንደ የንግድ ዘርፍ አይመለከቱትም ነበር። ስለዚህ የቀድሞው የስፖርት ማህበራት ስለሚቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን የወጣው መመሪያ ነጋዴ ክለቦች እንዲኖሩ ቢፈቅድም የኢትዮጵያ የንግድ ስራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያዎች ግን የስፖርት ክለብ ወይም የእግር ኳስ ክለብ የሚባልን የንግድ ዘርፍ አያውቁም።
አዲሱ የባህልና ስፖርት መመሪያ እና የክለቦች እጣ ፈንታ
ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ለመወሰን ተሻሽሎ የወጣው መመሪያ ቁጥር 907/2014 በመመሪያ ቁጥር አንድ የነበረውን የስፖርት ክለቦች ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ የሚወስነውን አንቀፅ ሙሉ ለሙሉ አስቀርቶታል። በዚህም የክለቦችን ጉዳይ ለፌዴሬሽኖች የሰጠ ይመስላል።
“የስፖርት ክለብንም “በአባላት እና በስፖርተኞች ስብስብ ስፖርትን ለማራመድ ከስፖርት ማህበር ፈቃድ ተሰጥቶት የተቋቋመ ነው” የሚል ብያኔ ይሰጠዋል። ፌዴሬሽኖች በሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ፈቃድ የሚሰጣቸው የስፖርት ማህበራት ናቸው። በእርግጥ በቀድሞው መመሪያም ክለቦች ፈቃድ የሚያገኙት ከፌዴሬሽኖች ነበር። ሆኖም ክለቦቹ ቢያንስ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ሊያሟሏቸው የሚገቧቸው መመዘኛዎች ግን በአዲሱ መመሪያ ቀርተዎል። አሁን ይህን መወሰን በመመሪያ ቁጥር 907/2014 አንቀፅ 8 (3) መሰረት የፌዴሬሽኖች ስልጣን ነው። ይህ ግን በመመሪያው አንቀፅ 59 የተከለከሉ ተግባራትን አይጨምርም።
ይህ ፈቃድ ሙሉ ለሙሉ ወደ ፌዴሬሽኖች መሄዱ የእግር ኳስ ክለቦችን የበለጠ ያግዛል የሚል እምነት አለኝ:: ምክንያቱም ንግድ ፈቃድ ለማውጣት የብቃት ማረጋግጫ ለማግኘት የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑን የክለብ ላይሰንሲንግ መመሪያዎች ማክበር በቂ ሊሆን ይችላል:: ስለዚህ የእግር ኳስ ክለብነት በኢትዮጵያ የንግድ ስራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያ እንደ አንድ የንግድ ዘርፍ እንዲካተት ማድርግ ክለቦች እና ፌዴሬሽኑ በጋራ መስራት ይችላሉ:: ክለቦቻችሁ ወደ ንግድ ተቋምነት እንዲቀየሩ የምትፈልጉ አቅም ያላችሁ ደጋፊዎችም ከክለቦቹ ጋር ከመከራከር መጀመሪያ ከፌዴሬሽኑ ጋር በመሆን የሚመለከተው ሚንስቴር መ/ቤት ላይ ጫና በማሳደር የኢትዮጵያ የንግድ ስራ ፈቃድ መስጫ መደብ መመሪያ እንዲሻሻል ብታደርጉ ይሻላል:: ይህ ለምን የንግድ ተቋም እንደማይሆኑ ሲጠየቁ “ህጉ አይፈቅድም” በሚል መልስ የሚደበቁ ክለቦችንም ሰበባቸውን ያስቀራል:: ያው ከልብ ካዘኑ…