

በፊፋ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮች እየተካሄዱ ሲሆን ከአውሮፓ እግር ኳስ ማሀበር እና ሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን አባላት በስተቀር ሌሎቹ ኮንፌዴሬሽኖች በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ውድድር ተሳታፊዎቻቸውን ለይተዋል።
እነማን አረጋግጠዋል?
እስካሁን 28 ሀገራት ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
አስተናጋጅ ሀገራት፦ አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ
አፍሪካ፦ አልጄሪያ፣ ካቦ ቨርዴ፣ ግብፅ፣ ጋና፣ አይቮሪ ኮስት፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዚያ
እስያ፦ አውስትራሊያ፣ ኢራን፣ ጃፓን፣ ጆርዳን፣ ካታር፣ ሳኡዲ አረቢያ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ኡዝቤኪስታን
ደቡብ አሜሪካ፦ አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ኮሎምቢያ፣ ኢኳዶር፣ ፓራጓይ፣ ኡሩጓይ
ሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ፦ ከሶስቱ አስተናጋጅ ሀገራት በተጨማሪ የሚያልፉ ሀገራት እስካሁን አልተለዩም።
አውሮፓ፦ እንግሊዝ
ኦሼንያ፦ ኒው ዚላንድ
ቀጣይ አላፊዎች?
በአፍሪካ ካሜሩን፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ናይጄሪያ እና ጋቦን በምድብ ማጣሪያ ጥሩ ሁለተኛ ሆነው በመጨረሳቸው ለፊፋው ኢንተርኮንቲነንታል የጥሎ ማለፍ ዙር ለማለፍ ይፋለማሉ። ካፍ ይህ ማጣሪያ መቼ እንደሚካሄድ አላሳወቀም።
በእስያ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ኢራቅ ለፊፋው ኢንተርኮንቲነንታል የጥሎ ማለፍ ዙር ለማለፍ የመጨረሻ ማጣሪያቸውን ያደርጋሉ።
በአውሮፓ ቀድማ ማለፏን ያረጋገጠቸውን እንግሊዝ ለመቀላቀል የህዳር ወር የፊፋ የጨዋታ ቀናት ከባድ ፍልሚያ ይደረግባቸዋል።
በኦሼንያ ደግሞ ኒው ካልዶኒያ ለፊፋው ኢንተርኮንቲነንታል የጥሎ ማለፍ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።
የደቡብ አሜሪካዋ ቦሊቪያ ሌላኛዋ ለፊፋው ኢንተርኮንቲነንታል የጥሎ ማለፍ ዙር ያለፈች ሀገር ናት።
የፊፋ የጥሎ ማለፍ ዙር
ይህ በስድስት ቡድኖች መካከል የሚደረግ የመጨረሻ ማጣሪያ ነው። ከሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ ሁለት፣ ከአውሮፓ በስተቀር ከሌሎቹ አህጉሮች ደግሞ አንድ አንድ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ሲሆን ሁለት ሀገራት የዓለም ዋንጫ ትኬታቸውን ይቆርጡበታል።