

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ህዳር 14 ቀን በሚደረገው የ2018 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ 10ኪ.ሜ. ላይ ለሚያሸንፉ አትሌቶች በድምሩ ከ1.8ሚሊዮን ብር በላይ ሊሸልም ነው።
ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ የአለም አትሌቲክስ (Label Road Race) ደረጃ የተሰጠው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ 10ኪ.ሜ. ሃያ አምስተኛ ዓመት ውድድሩን በማስመልከት በአንደኛነት ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች የሚያበረክተውን የገንዘብ ሽልማት ወደ አራት መቶ ሺህ (400,000) ብር ከፍ አድርጓል።
በዚህም መሰረት ሽልማቱ በውድድሩ ላይ ባለፈው አመት ለአሸናፊዎች በሽልማትነት ተበርክቶ ከነበረው 250ሺህ ብር በስልሳ በመቶ (60%) አድጓል። በተመሳሳይ ሁለተኛ ለሚሆኑ የ200ሺህ አንዲሁም ሶስተኛ ሆነው ለሚያጠናቅቁ አትሌቶች የ100ሺህ ብር ሽልማት አንደሚበረከት ይፋ ተደርጓል።
የውድድሩን ጥራት አና የአትሌቶችን ፉክክር ከፍ ማድረግ አንዲቻልም በክለብ አና የስፖርት ማኔጅመንት ውስጥ ከሚገኙ አትሌቶች በተጨማሪ በግል ለሚወዳደሩ አትሌቶች ዕድል ለመፍጠር ቅዳሜ ጥቅምት 01 ቀን 2018 ዓ.ም. በእንጦጦ ፓርክ የማጣሪያ ውድድር ይካሔዳል። ይህም ማጣሪያ በግል ለሚወዳደሩ አትሌቶች በውድድሩ ላይ የመሳተፍ ዕድልን ይፈጥርላቸዋል።
ቅዳሜ ከአትሌቶች የማጣሪያ ውድድር በተጨማሪም 9ኛው ዙር የወርሃዊው እንጦጦ ፓርክ ሲቢኢ ሩጫ ላይ ባለፉት ውድድሮች ላይ ሰባት እና ከዛ በላይ ለሆነ ጊዜ የሮጡ ተሳታፊዎች ልዩ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።
(ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ)