ከኬንያ አንጋፋ የረጅም ርቀት ሩጫ አትሌቶች መካከል ሦስቱ – ፖል ቴርጋት፣ ዳንኤል ኮመን እና ሞሰስ ታኑይ – እሁድ ህዳር 14 ቀን 2018 በሚካሄደው የ2018 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር ላይ ለመገኘት ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ተገለፀ።
ሦስቱም አትሌቶች በዓለም አቀፍ የሩጫ ሕይወታቸው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያን በ1994ዓ.ም. ከመሠረተውና የኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ሩጫ ምልክት የሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ ዋና ተፎካካሪ ነበሩ።
ቴርጋት ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. በመስከረም ወር 2003 በበርሊን የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ከሰበረ በኋላ በውድድሩ ላይ በእንግድነት ተገኝቶ ነበር። በ1990ዎቹ ከኢትዮጵያዊው ጓደኛው ኃይሌ ጋር ከፍተኛ ፉክክር የነበረው ሲሆን ፤ በ1996 እና በ2000 ኦሎምፒክ ኃይሌን በመከተል የብር ሜዳሊያውዎችን አግኝቷል። ሁለቱም ወደ ማራቶን ሲያድጉም ፉክክሩ የቀጠለ ሲሆን፣ ኃይሌ በሴፕቴምበር 2007 በመጀመሪያው የማራቶን ክብረ ወሰን የዓለም ሪከርዱን ከቴርጋት በ29 ሰከንድ ልዩነት ወስዷል።

ዳንኤል ኮመንም ከ1996 እስከ 1998 ባሉት ሦስት ዓመታት በትራክ ላይ ከኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር ከባድ ፉክክር ነበረው።
እ.ኤ.አ. 1996 በተካሔደው የአትላንታ ኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ ያልተካተተው ኮመን በሴፕቴምበር 1 ቀን 1996 በጣሊያኗ ሪየቲ የ3000 ሜትርን 7፡20.67 በመሮጥ የዓለም ክብረ ወሰንን ይዞ ነበር ፤ ይህም ጃኮብ ኢንገብሪግስተን በኦገስት 2024 እስኪሰብረው ድረስ ለ28 ዓመታት ያህል ዘልቋል። በ1997 ኮመን የ5000ሜትር የዓለም ክብረ ወሰንን 12፡39.74 በመሮጥ ከኃይሌ ወስዶ የነበረ ቢሆንም ኃይሌ በ12፡39.36 በመሮጥ በአንድ ዓመት ውስጥ መልሶ ወስዶታል።
ሞሰስ ታኑይ በዚህ ወር መጨረሻ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜው ነው። ታኑይ የሁለት የዓለም ሻምፒዮና አሸናፊ (በ1991 በትራክ እና በ1995 በጎዳና ላይ) ሲሆን ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአጋርነት የሚሰራው የኤልዶሬት ማራቶን የውድድር ዳይሬክተር ነው። ታኑይ በ1993 የዓለም ሻምፒዮና የ10,000ሜትር ውድድር ላይ ከኃይሌ ገብረሥላሴ ጋር አይረሴ ፉክክር ቢያደርግም በመጨረሻው ዙር ጫማው በመውለቁ ኃይሌ አሸንፎት እንደነበር ይታወሳል።

ሶስቱም የኬንያ ታላላቅ አትሌቶች ከዚህ ቀደም በተለያየ ጊዜ በእንግድነት ታድመውበት በነበረው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መድረክ ላይ በድጋሚ ከኃይሌ እና ከሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ጋር መገኘት የ25ኛውን ዓመት ክብረ በዓል በሚያደምቁት 55,000 ተሳታፊዎች ላይ ተጨማሪ ደስታን ይፈጥራል።
የ2018 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10 ኪሎ ሜትር መነሻዎቹን መስቀል አደባባይ እና ግዮን ሆቴል በማድረግ ፤ እሁድ ህዳር 14 ቀን 2018ዓ.ም. ይካሔዳል።
(ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ)




