ከአራት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብን “የታገዱ ተጫዋቾችን በማሰለፍ” በሚል በኢትዮጵያ ዋንጫ ያገኘው ድል ተሰርዞ በፎርፌ እንዲሽነፍ እና የቀጣዩ የውድድር ዘመን የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊነቱ እንዲነጠቅ መወሰኑ ይታወሳል። በዚህም ክለቡ ለዓለም አቀፉ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት /ካስ/ ይግባኝ እንደጠየቀ መግለፁ ይታወቃል።
ይግባኙ ምን ላይ ደርሷል?
ካስ በገላጋዮች የሚሰሙ ክርክሮችን ዝርዝር በየሳምንቱ ወይም እንደ አስፈላጊነቱ በድረ ገፁ ያወጣል። የሲዳማ ቡና ጉዳይ ግን እስካሁን ድረስ በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተም። ካስ ይግባኙ ደርሶት እንደሆነ እና ክርክሩ መቼ ሊሰማ እንደሚችል ጠይቄያለሁ።
ካስ በምላሹ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላይ ያቀረበውን ይግባኝ ሐምሌ ስምንት ቀን 2017 ዓ.ም መቀበሉን አረጋግጧል።
በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ተከራካሪዎች ጉዳያቸውን በፅሁፍ እያቀረቡ እንደሆነም ካስ ገልፅዋል። ይህ ወቅት ሁለቱ ወገኖች ክርክራቸውን፣ ማስረጃዎቻቸውን እና የህግ ምክንያቶቻቸውን በፅሁፍ ለካስ የሚያቃርቡበት ጊዜ ነው።
ሆኖም ካስ ክርክሩን የመስሚያ ቀን አልቆረጠለትም። ካስ ክርክሩን የመስሚያ ቀን እንደወሰነ በድረ ገፁ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።





