አዲሱ የአሎንሶ አብዮት; የጨዋታ ቁጥጥር እና ከኳስ ውጪ የተጨዋቾች ሚና

ከላይ የተጠቀሱት ሃሳቦች አውሮፓ ውስጥ ላሉ ታላላቅ ክለቦች እና አሰልጣኞቻቸው አዲስ ነገር አይደሉም:: በእግርኳስ ከፍ ባለው ልህቀት ደረጃ ላይ የደረሱ አሰልጣኞች ዋነኛ አላማቸው የጨዋታውን አካሄድ መቆጣጠር ነው:: ይህም ተጋጣሚን አጨዋወቱን ቀድሞ ማጥናት፣ ብልጫ የሚወስድባቸውን አጋጣሚዎች ነቅሶ ማውጣት ከዛም ለእነዚህ ጥንካሬዎች ማክሸፍያ ማበጀት:: ተጋጣሚን እንቅስቃሴ ከማክሸፍ ተነስቶም የራስን ጥቅም መፈለግ:: ይህም ጥቅም የግብ ዕድሎችን መፍጠር..ብሎም ወደ ግብነት መቀየር ነው::

ባለፈው ውድድር ዓመት ሁለተኛው መንፈቅ በአስገራሚ አካላዊ ቁመና እና ታክቲካው የበላይነት የአውሮፓ ክብርን ያሳካው ፓሪ ሳን ዠርመ አንድ ልዩ ስልት ይከተል ነበር:: ቡድኑ የተዋቀረው ኳስን ያለመታከት መንጠቅ በሚችሉ ተጨዋቾች በመሆኑ የጨዋታውን የመጀመር ዕድል ሲያገኙ(kickoff/second half start) ኳሱን ወደተጋጣሚ መአዘን ጠርዝ አቅራቢያ የእጅ ውርወራ እንዲሆን አድርገው ያወጡታል :: ይህም በባላጋራቸው ጥልቅ ግብ ክልል ኳን መልሰው መንጠቅ የሚችሉበትን ዕድል ያሰፋል::

እነዚሁ ጨዋታን አብዝተው መቆጣጠር የሚፈልጉ አሰልጣኞች ትልቅ ራስ ምታት የሆነው ጉዳይ ደግሞ የቆሙ ኳሶችን ከማጥቃት ወይም መከላከል በኅላ የሚመጡ አይገመቴ ሽግግሮች ናቸው:: ቡድናቸው መአዘን ምትን ወይም ለሚያጠቁት ግብ የቀረበ ቅጣት ምትን ሲጠቀም ይህንን እድል ለመጠቀም በቁጥር በዛ ብሎ የተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ መገኘት ግድ ይላል:: ተሻጋሪ ኳሱም የልክነቱ ደረጃ ከተጨዋች ጥራት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ከፍ ዝቅ ቢልም የእንቅስቃሴውን ቀጣይ ምእራፍ አይገመቴነቱን ይጨምረዋል:: እነዝያ ተጋጣሚ ኳስ ሲመሰርት ማን ማንን መቆጣጠር እንዳለበት የተዘጋጁ፣ በእያንዳንዱ የጨዋታ ምዕራፍ መልስ ይዘው የመጡ አሰልጣኞች ከላይ የተነሳውን ሁኔታ አይወዱትም:: ቡድናቸው አብዝቶ ታክቲካዊ ጥፋቶችን ሰርቶ እንቅስቃሴውን እንዲያቋርጥም ያደርጋሉ::

ከዚህ በተለየ መልኩ በመጫወት ብዙውዎች ለይትው የሚያነሱት ክለብ ደግሞ አለ:: ይህ ክለብ ምንም እንኳን ከታላላቆቹ የአውሮፓ ክለቦች አንዱ ቢሆንም በሜዳ ላይ አጨዋወት ከባላንጣዎቹ ፈንጠር ብሎ እራሱን በመለየት ቆይቷል:: የስፔኑ ኅያል ሬያል ማድሪድ ከላይ በተጠቀሱት የጨዋታ ምዕራፎች ቁጥጥር እና በ አጨዋወት ቅንጣት ዝግጅቶች ላይ ብዙም ደንታ የሌለው ክለብ ነበር:: ሬያል ማድሪድ እንዲሁ ያለቅርፅ እና እቅድ ይጫወታል ማለት ግን አይደለም:: በዋና ዋና ይአጨዋታ ምዕራፎች (የማጥቃት እና መከላከል ሽግግር፣ የጅቆመ ኳስ ማጥቃት እና መከላከል አደረጃጀት እንዲሁም ከኅላ ምስረታ) ላይ እቅድ አላቸው ::የሬያል ማድሪድ የአጨዋወቱ ፍልስፍና ከተጨዋቾቹ ጥራት ይመነጫል:: ጨዋታው ላይ ለሚፈጠሩ ፈተናዎች በዋነኝነት ቡድኑ ጥራት ያላቸው ተጨዋቾች መፍትሄ እንዲፈልጉ ያደርጋል:: ሌላ ቡድን አማካይ ክፍል ላይ ቁጥጥር እየተሳነው ሲሄድ የጨዋታውን ፎርሜሽን ይለውጣል፤ ሬያል ማድሪድ መኅል ሜዳ ላይ ቁጥጥር ሲሳነው ሉካ ሞድሪች ለተከላካዮች ተጠግቶ ኳስ እንዲቀበል እና ተጋጣሚን እየቀነሰ ወይም እየተቀባበለ ብልጫ እንዲወስድ ያደርጋል:: ይህ ልዩ የሆነ አጨዋወት ክለቡን ለተለያዩ ክብሮች አብቅቶታል:: ቡድኖች ሬያል ማድሪድን መግጠም ከለመዷቸው ተጋጣሚዎች ፍፁም የተለየ ሲሆንባቸው እንዲሁም ምላሽ ለመስጠት ሲቸገሩ ተመልክተናል:: በአንፃሩም ይህ በግለሰቦች ጥራት ላይ አብዝቶ የተመሰረተው አጨዋወት አልሰራ ሲል እና አስከፊ ሽንፈቶችን ቡድኑ ሲገጥመው አይተናል::

አሁን ጊዜው የ ኦሎንሶ ነው:: ኦሎንሶም ይህ ለዘመናት ከክለቡ ጋር ተዋህዶ የቆየውን ግለሰብ ወለድ የጨዋታ መርህ ወደ ጨዋታ ቅንጣቶች ተቆጣጣሪ የጨዋታ መርህ ለመቀየር እየሰራ ነው::
ይህ መርህ መጀመርያ ለአጨዋወቱ ፍልስፍና ተገዢ መሆንን ይፈልጋል:: እንደከዚህ ቀደሙ 11 ተጨዋቾችን ሰይሞ ከዛ እንዴት እንጫወት ሳይሆን..እንዴት እንጫወት የሚለውን ወስኖ ከዛ እነማንን የትኛው ቦታ ላይ ላሰልፍ ወደሚለው ይሄዳል::

ኦሎንሶ በጣት በሚቆጠሩ ቀናት ዝግጅት በኅላ ክለቡ የተሳተፈባቸው 6 የክለብ ዓለም ዋንጫ ውድድር ጨዋታዎች እንዲሁም ከሊጉ ጅማሪ በፊት 1 የወዳጅነት ጨዋታ አድርጏል:: የክለብ ዓለም ዋንጫ ጨዋታዎቹ በቂ የዝግጅት ጊዜ ማነስ እንዲሁም አስከፊ የዓየር ሁኔታ እንዳሉ ሆኖ ቡድኑ ብዙ ስራ እንደሚፈልግ ጠቋሚ ነበሩ:: በተለይም የምድቡ የመጀመርያ አልሂላል እና የግማሽ ፍፃሜው PSG ጋር ያደረጏቸው ጨዋታዎች ይጠቀሳሉ::

አዲሱ አሰልጣኝ በኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረተ ቡድን ሬያል ማድሪድ እንዲሆን ይፈልጋል:: በቀድሞው ክለቡ ባየርን ሌቨርኩዘን አጨዋወት ማስተዋል እንደተቻለው የተረጋጋ እና ጥራት ባለው ምስረታ ያደገው እንቅስቃሴ ፍጥነት እና ጥራት ባላቸው በቁጥር በዝተው የተጋጣሚን ግብ ክልል በሚወሩ ተጨዋቾች እንቅስቃሴው ይጨርሳል:: ለዚህም ከቦርንመዝ የፈረመው ወጣት የመኅል ተከላካይ ዲን ሃውሰን በመጀመርያው የእንቅስቃሴ ምዕራፍ ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል:: ኦውሬልዮን ቾዋሜኒም (ተጋጣሚ በሁለት 9ኞች ከተጫወተ ከሃውሰን ጎን በመሆን በ አንድ 9 ብቻ ከሆነ ደግሞ ሁለተኛው መስመር ላይ በመገኘት) የ ጨዋታው ምስረታ ቁልፍ አካል ነው:: ሜዳውን በግራ እና ቀኝ የሚለጥጡ ሁለት የመስመር አጥቂዎች ይኖራሉ:: በተለይ የግራ የመስመር ተከላካዩ(ካሬራስ ወይም ፍራን) ከ ቪኒ ጁንዮር ጋር እየተግባባ የግራ ሜዳውን መለጥጥ ይፈራረቃል:: በቀኝ የትሬንት በቋሚነት ወደውስጥ መግባት የቀኝ መስመር አጥቂውን ስራ ያቀለዋል:: ፌዴ ቫልቨርዴ፣ አርዳ ጉሌር እና ትሬንት(በተወሰነ መልኩ) የሚዋልል ነፃ ሚና ይኖራቸዋል:: እምባፔም ሰንጣቂ ኳሶችን ነቅቶ መጠበቅ ወደግራ እየወጣ ቁጥር መጨመር(Overload) ሃላፊነቶች አሉት:: ክለቡ ከታዳጊ ቡድን ያገኘው ጎንዛሎ ጋርሲያም አዲስ ጉልበት እና መንፈስ ለቡድኑ ጨምሯል::

ከኳስ ጋር ባለው እቅስቃሴ የኦሎንሶ አዲስ ቡድን መልካም ነገሮችን አሳይቷል:: ትልቁ ችግር ከኳስ ውጪ ያለውን የጨዋታ ምዕራፍ ላይ መቆጣጠር ነው:: በተለይ ከመስመር የሚነሱት አጥቂዎች ከአሰልጣኙ ቅጥር ጀምሮ ብዙዎች እንደሰጉት ከባድ ኅላፊነት ተጥሎባቸዋል:: ከዚህ ቀደም ያልነበረ ኅላፊነት በመሆኑም በአንድ ጊዜ ለመተግበር እንደተሳናቸው ተስተውሏል:: አሰልጣኙም ከሁለቱ የመስመር አጥቂዎች አንዱ ላይ የጨከነ ይመስላል:: ሮድሪጎ ከዋናው ቡድን ተሰላፊዎች እስካሁን ጥቂት እድል የተሰጠው ተጨዋች ነው:: ውሳኔው ታክቲካው ብቻ ይሁን ወይም የበለጠ ትኩረት የሚሰጠው ቪኒ ጁንዮርን ላለማስቀመጥ ይሁን የተወሰነው የሚያውቀው እራሱ አሰልጣኙ ነው:: አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ሁለቱንም ብራዚላውያን በመስመር ማሰለፍ እንዳልፈለገ ነው::

ተጨዋቾች በተገቢው ስልጠና እና ሰዋዊ ቅርርብ ይማራሉ፣ ይለወጣሉ:: ፊሊፕ ላህም አይነት ተጨዋቾች በእግርኳስ ዘመናቸው መገባደጃ ላይ ከተለየ ሃሳብ ካለው አሰልጣኝ ጋር ሰርተው እራሳቸው ወደተለየ ሚና ለውጠዋል:: ለቪኒ ጁንዮም ሆነ ሮድሪጎ ይህ ምሳሌ ይሰራል::

ሬያል ማድሪድ ፊቱን ወደቁጥጥራዊ አጨዋወት አዙሯል፣ መፍትሄው ከዚህ በኅላ የተጨዋቹ ቴክኒክ ሳይሆን በታክቲኩ ውስጥ ያለው ተጨዋች ነው:: ኦሎንሶም ዛሬ አሃዱ ብሎ ሊጉን ከአዲሱ ቡድኑ ጋር ይቀድሳል::

Minyahel Mamo

Related Posts

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

© Getty Images ኢትዮጵያዊቷ ሐዊ ፈይሳ በባንክ ኦፍ አሜሪካ ቺካጎ ማራቶን ባለድል ሆናለች። መገርቱ አለሙ ደግሞ በሁለተኛነት አጠናቅቃለች። ሐዊ ውድድሩን ያሸነፈችበት ጊዜ 2:14:56 ሲሆን የግሏ ምርጥ ሰዓት ነው።  የዓለም ማራቶን ሜጀር…

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ህዳር 14 ቀን በሚደረገው የ2018 ሶፊ ማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለም አቀፍ 10ኪ.ሜ. ላይ ለሚያሸንፉ አትሌቶች በድምሩ ከ1.8ሚሊዮን ብር በላይ ሊሸልም ነው። ከ2017 ዓ.ም. ጀምሮ የአለም አትሌቲክስ…

You Missed

St. George wins the City Cup 

St. George wins the City Cup 

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

ሐዊ የቺካጎ ማራቶንን አሸነፈች

Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

Great Ethiopian Run Winners to Receive Record Prize Money

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለአትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ሊያበረክት ነው

Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

Ethiopia’s Shure Demise Seeks Third Victory at TCS Toronto Waterfront Marathon

የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ

የ2025 የአፍሪካ ኢምፓክት አዋርድ ተሸላሚዎች ይፋ ሆኑ