(እግር ኳስ ፌዴሬሽን)
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዳኞች ልማትና አስተዳዳር ዳይሬክቶሬት ከዳኞች ልማት ኮሚቴ ጋር በመቀናጀት በ2022 የውድድር ዘመን በኢንተርናሽናል ደረጃ እግር ኳስን መምራት የሚችሉ ዳኞችን ለመለየት ለ12 ኤሊት ወንዶችና ሴቶች የጨዋታ አመራሮች/ ዳኞች/ ትናንት መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት የጽሑፍ፣ የቃልና የኮምፒውተር ክህሎት ፈተና አካሄደ፡፡
ፈተናው መስከረም 5 ቀን 2014 ዓ.ም በተደረገው የኢንተርናሽናል እና የኤሊት የጨዋታ አመራሮች የአካል ብቃት ፈተና ውጤት ማለፋቸውን ለአረጋገጡ 12 ኤሊት ዳኞች የተሰጠ ሲሆን ከነዚህም አንድ ሴት ዋና ዳኛ ፣ ከወንዶች 7 ዋና እና 4 ረዳት ዳኞች ይገኙበታል፡፡
ለኤሊት ዳኞች የተዘጋጀው ፈተና ዓላማ ቀደም ሲል በኢንተርናሽናል ደረጃ የነበሩት ዋና እና ረዳት ዳኞች ቁጥር በተለያዩ ምክንያት በመቀነሱ እነሱን ለመተካት የተዘጋጀ ሲሆን በመመዘኛ ፈተናዎቹ እና በቀረበው መስፈርት መሰረት የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ኤሊት ዳኞችን ወደ ኢንተርናሽናል የጨዋታ አመራር ደረጃ ብቃት በመመዘን ለማሳደግ የተዘጋጀ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2021 በዓለም አቀፋ እግር ኳስ ማህበር /ፊፋ/ ኮታ መሠረት በዋና ዳኝነት 7 ወንድ እና 4 ሴት፣ በረዳት ዳኝነት በተመሳሳይ 7 ወንድ እና 4 ሴት በአጠቃላይ 11 ኢንተርናሽናል ዋና እና 11 ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኞች ተመዝግበው ባጅ ከወሰዱት መካከል 4 ዳኞች በተለያዩ ምክንያቶች በመቀነሳቸው እነዚህን ለመተካት በተዘጋጀው የኤሊቶች ፈተና የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ 4 ዳኞች ( አንድ /1/ ሴት ዋና ዳኛ እንዲሁም 2 ዋና 1 ረዳት ወንዶች) ዳኞች ለ2022 በኢንተርናሽናል ዳኝነት ዝርዝር ውስጥ የሚካተቱ ይሆናል፡፡