ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እ.አ.አ. ከ2026 ጀምሮ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር አብረው ለመስራት የበርካታ ዓመታት የአጋርነት ስምምነት ማድጋቸውን ዛሬ አሳውቋል፡፡ አጋርነቱ ባንኩ በረዥም ርቀት ሩጫ ላይ የነበረውን ግዙፍ እንቅስቃሴ ከአፍሪካ እጅግ ተለዋዋጭ እና በፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ የሩጫ ማህበረሰቦች ወደ አንዱ እንዲያሰፋ ያግዘዋል፡፡
ባንክ ኦፍ አሜሪካ እና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሶስት ትልልቅ የሩጫ ሁነቶች (events) ላይ በጋራ ይሰራሉ – የ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10ኪ.ሜ ፣ የልጆች ሩጫዎች እና ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ.። ባንክ ኦፍ አሜሪካ እነዚህን ውድድሮች ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ደማቅ የሩጫ ባህል እይታ ለማሳደግ እና በስፖርት፣ ቱሪዝም እና ንግድ አማካይነት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ለማድረግ ተዘጋጅቷል፡፡
ባንክ ኦፍ አሜሪካ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አጋር የመሆኑ ምክንያት ተቋሙ ቀጣዩን ትውልድ ለማነሳሳት እና በኢትዮጵያ እና በመላው ዓለም የፅናት ስፖርቶችን ለማስፋፋት ካለው ማህበረሰብ-ተኮር መርሆ የተነሳ ነው፡፡ ይህ ባንክ ኦፍ አሜሪካ በስፖርት አማካይነት እድገትን የማነሳሳት እና ማህበረሰቦችን የማገዝ የረዥም ጊዜ ቁርጠኝነቱን ሲያጠናክር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሩጫን የሁሉም የህይወት ዘይቤ የማድረግ ዋነኛ ራዕይ ጋርም የተስማማ ሆኗል።
‹‹ባንክ ኦፍ አሜሪካ በስራዎቻችን ሁሉ አጋር ሆኖን ወደምንንቀሳቀስበት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጉዞ ቀጣዩ ደረጃ ልንገባ በመሆናችን እጅግ ደስተኞች ነኝ›› የሚሉት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ስራ አስኪያጅ ዳግማዊት አማረ ‹‹ለማህበረሰባችን እና ለልጆቻችን ባለን ጠንካራ መሰጠት፣ ትልቁ ውድድራችንን ተጠቅመን መዳረሻችንን ለማስፋት እና ለልጆች እና ወጣቶች የሩጫ እድሎችን ለመጨመር በጋራ እንሰራለን›› ሲሉ ያክላሉ፡፡
በጋራ የመስራቱ ዋነኛ ዓላማ በየዓመቱ 50.000 ገደማ ተሳታፊዎችን የሚቀበለውን የዝነኛው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ 10ኪ.ሜ ተሳትፎ ይበልጥ ማሳደግ እንዲሁም በታዳጊዎች እና ሴቶች ሁነቶች ላይ ተሳትፎን ማስፋት ነው፡፡ እነዚህ እንቅስቃሴዎች በየአካባቢው ያለ ተሰጥኦን የማሳደግ፣ ጤነኛ የህይወት ዘይቤን የማስተዋወቅ እና የኢትዮጵያን የተለየ የሩጫ ባህል እና የመሰባሰብ መንፈስ የሚያከብሩ መድረኮችን የመፍጠር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን የሚያጎሉ ናቸው፡፡
‹‹ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የስፖርቶችን አዎንታዊ ተፅዕኖ በኢትዮጵያ፣ አፍሪካ እና በዓለም ዙሪያ እያሳደገ የሚገኝ እጅግ የላቀ ድርጅት ነው፡፡ እኛም በዓለም ዙሪያ ማህበረሰቦች እንዲያድጉ ለመርዳት፣ ተፅዕኗቸው የገዘፈ እድሎችን ለመፍጠር እና አትሌቶችን ለማገዝ ካለን ህልም መነሻ፣ የልጆች እና ሴቶች ውድድሮች ተሳትፎ እንዲያድግ ብሎም በስፖርት አማካይነት ቀጣዩን ትውልድ ለማብቃት ከታላቁ ሩጫ ጋር በመተባበሩ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ኩራት ይሰማዋል›› የሚሉት የባንክ ኦፍ አሜሪካ የዓለም አቀፍ ማርኬቲንግ ትብብሮች ኃላፊው ብራድ ሮስ ናቸው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን በመሳብ ለአዲስ አበባ ቱሪዝም እና መሰረተ ልማት ግዙፍ አስተዋፅኦ ያበረክታል፤ በከተማዋ ያሉ የንግድ እንቅስቃሴዎችንም ያነቃቃል። ይህ አጋርነትም እነዚህን ጥቅሞች – ስራዎችን መፍጠር፣ የከተማዋ ንግዶችን ማነቃቃት እና በአዲስ አበባ ውስጥ እና ዙሪያ ለሚኖሩ ማህበረሰቦች የተለዩ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ማቅረብ – የበለጠ ያጎላሉ።
ባንክ ኦፍ አሜሪካ ሁነቶቹ በጋራ የ1.1 ቢሊየን ዶላር የኢኮኖሚ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ እና ለበጎ አድራጎት ስራዎች ከ90ሚሊየን ዶላር የበለጠ የሚያሰባስቡ ሁለት የአቦት ወርልድ ማራቶን ሜጀሮች (Abbott World Marathon Majors) – ቦስተን እና ሺካጎ ማራቶኖች – ስፖንሰር መሆኑ ሲታወስ፣ ይህ አጋርነት ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ ሀብቶችን እና አሰራሮችን ወደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ እና ወደሚያዘጋጃቸው ሁነቶች እንደሚያመጣ መጠበቅ ይቻላል።
ባንክ ኦፍ አሜሪካ ዓለም አቀፋዊውን የሩጫ መድረኩን ከአፍሪካ ቀጣይ የሯጮች ትውልድ ጋር በማስተሳሰር ስፖርት እንዴት እድሎችን ሊፈጥር እንደሚችል ማሳየቱን ቀጥሎበታል፡፡ ይህም ሰዎችን፣ ገበያዎችን እና ማህበረሰቦችን በማሰባሰብ እና በአውሮፓ፣ መካከለኛው ምስራቅ እና አፍሪካ ዙሪያ ካለው ሰፊ የንግድ ስትራቴጂ ጋር በሚስማማ መልኩ በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ እድገት ላይ እንደአጋር የራሱን ሚና በማጠናከር ነው፡፡
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋነኛ ራዕዩ የሆነው ‹‹ሩጫን የሁሉም የህይወት ዘይቤ ማድረግ››ን ይዞ ሲጓዝ፣ በላቀ ቴክኖሎጂ የውድድር ዝግጅቱን ይበልጥ የዘ’መነ እንዲያደርግ ለማገዝ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ሀብቶችን እና የሩጫ እውቀትን ያቀርባል፡፡ ይህ ስትራቴጂያዊ ትኩረት የሯጮችን ተሞክሮ ማሻሻልን፣ የሁነት ዝግጅትን ይበልጥ ማዘ’መንን እና የሁነቱን እየሰፋ የሚገኝ ዱካ በብቃት ማስተዳደርን ያለመ ነው፡፡ ይህ አጋርነት የበለጡ ተሳታፊዎችን ይስባል፤ የመሪ ዓለም አቀፍ የሩጫ ሁነት ደረጃውን ያጠናክራል፤ የሁነቱን የረዥም-ጊዜ ዘላቂነት ያረጋግጣል፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ደማቅ የባህል ክብረ-በዓል ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡
ባንክ ኦፍ አሜሪካ አዲስ እና ጠለቅ ያለ የደንበኛ ግንኙነትን የመፍጠር፣ የቡድን አጋሮችን የማሳተፍ እና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ የኢኮኖሚ ተፅዕኖን የማገዝ እንቅስቃሴው አካል አድርጎ በስፖርት ውስጥ ካሉ እጅግ ታዋቂ ብራንዶች ጋር በአጋርነት ይሰራል፡፡ ባንክ ኦፍ አሜሪካ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ካለው አጋርነት ባሻገር በሩጫ፣ እግር ኳስ እና ጎልፍ ከዓለም አቀፍ ብራንዶች እና ሁነቶች ጋር በአጋርነት ይሰራል፡፡ እነዚህም Boston Marathon presented by Bank of America፣ Bank of America Chicago Marathon እና Chicago Distance Series፣ የ2026 የፊፋ ዓለም ዋንጫ፣ የአሜሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ሁሉም 27 የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድኖች እንዲሁም በጎልፍ የማስተርስ ውድድር እና Augusta National Women’s Amateur ናቸው፡፡ ባንክ ኦፍ አሜሪካ የስራ እንቅስቃሴውን ለማሳደግ፣ ብራንዱን ለማጎልበት እና በሚንቀሳቀስባቸው 35 ሀገራት እና 100 የሚጠጉ የአሜሪካ ገበያዎች በጎ ተፅዕኖ ለማሳደር በእነዚህ አጋርነቶች ዙሪያ በትኩረት ይሰራል፡፡
(ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ)





