በረከት ፀጋዬ
33ተኛው ቶታል ኢነርጂስ አፍሪካ ዋንጫ በካሜሩን አስተናጋጅነት ከጥር 1-29 ይካሄዳል። አስተናጋጇ ሃገር ዋንጫውን በሃገራቸው ለማስቀረት ይፈልጋሉ። ለ33 ጨዋታዎች ያህል ያለመሸነፍ ጉዞ ላይ ያሉትና የወቅቱ የአፍሪካ ሻምፒዮኖች አልጄሪያ ቢያንስ ያለመሸነፍ ጉዞዋቸውን ወደ አምስት ከፍ የማድረግ ፍላጎት አላቸው።
በፊፋ ወርሃዊ ደረጃ የወቅቱ የአህጉሪቱ አንደኛ ሴኔጋል ምንም እንኳን የአፍሪካ ዋንጫውን ለአንድ ጊዜ እንኳ ለመሳም ባይታደሉም ይህን ታሪክ ለመቅረፍ ጊዜው አሁን እንደሆነ ይረዳሉ።
ምድብ አንድ
ቡርኪናፋሶ፣ ኬፕ ቨርድ፣ ካሜሮን፣ ኢትዮጰያ
ቡርኪናፋሶ
● ተሳትፎ፡ 12ኛ ጊዜ
● ምርጥ ውጤት፡ የፍፃሜ ተፋላሚ (2013)
● አሰልጣኝ: ካሙ ማሎ
● ኮከብ ተጫዋች: በርትራንድ ትራኦሬ
● ምን ይጠብቃሉ: ያለፈውን የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ አለመቻላቸው ቁጭትን የፈጠረባቸው ፈረሰኞቹ ይህን ወደ ኃላ ትተው የተሻለ ውድድርን ለማሳለፍ ያቅዳሉ። ወደ ክታሩ አለም ዋንጫ የሚወስዳቸውን ትኬት ለመቁረጥ የመጨረሻው 10 ምርጦች ውስጥ ለመግባት እስከ መጨረሻው አልጄሪያን ቢፈትኑም በጠባብ ውጤት ምድቡን በበላይነት ማጠናቀቅ ሳይችሉ ቢቀሩም እንደ በርትራንድ ትራኦሬ እና አብዱል ታፕሶፓ የመሳሰሉ ከዋክብትን ይዘው ከምድቡ ረጅም ርቀትን መጓዝን ያልማሉ።

ኬፕ ቨርድ
● ተሳትፎ: 3ኛ ጊዜ
● ምርጥ ውጤት: ሩብ ፍፃሜ (2013)
● አሰልጣኝ: ቡቢስታ
● ኮከብ ተጫዋች: ራያን ሜንዴዝ
● ምን ይጠብቃሉ: ያለፉት አስር አመታት ለትንሿ የባህር ዳርቻ ሃገር እግር ኳስ ትልቅ ለውጥን የፈጠረ ነበር። በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በ2013 ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀሉት ሰማያዊ ሻርክስ ፌዴሬሽኑ በተከተለው ትውልደ ኬፕ ቬርድ ተጫዋቾችን ከአውሮፓ በመሰብሰብ ጠንካራ ቡድንን የመስራት ፕሮጀክት በእጅጉ ተጠቅመዋል። ምንም እንኳን ካለፉት 4 ውድድሮች ሁለቱ ላይ መካፈል ባይችሉም ቡድናቸው ጠንካራ መሆኑን በቀረቡባቸው መድረኮች በሚገባ አሳይተውናል።

ካሜሩን
● ተሳትፎ: 20ኛ ጊዜ
● ምርጥ ውጤት፡ ሻምፒዮን (1984፣88፣ 2000፣02፣17)
● አሰልጣኝ፡ አንቶንዮ ኮንሴንሳኦ
● ኮከብ ተጫዋች: ኤሪክ ማክሲም ቺፖ ሞቲንግ
● ምን ይጠብቃሉ: በሜዳቸው ላይ ውድድሩ እንደ መካሄዱ ከምድቡ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ብቻ ሳይሆን እስከ መጨረሻው ተጉዘው ዋንጫውን ሃገራቸው ላይ ማስቀረት በእጅጉ ይፈልጋሉ። ምንም እንኳን እንደ ቀደሙት ጊዜያት የአፍሪካ እግር ኳስ የሃይል ሚዛንነት አብሯቸው ባይሆንም የማይበገሩት አንበሶች በአውሮፓ ሊጎች መድመቅ የቻሉ ከዋክብትን ይዘዋል።
በክረምቱ የሴሪ አውን ክለብ ኢንተር ሚላን ለመቀላቀል ፊርማውን ያኖረው የአያክሱ ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና፣ በውሰት ከፋልሃም ናፖሊን ተቀላቅሎ ጥሩ የውድድር አመት እያሳለፈ የሚገኘው አንድሬ ፍራንክ ዛምቦ አንጉዊሳ እና የባየር ሙኒኩ አጥቂ ኤሪክ ማክሲም ቺፖ ሞቲንግ ከነዚህ ውስጥ ይጠቀሳሉ። ቡድኑን ከ2019 ወዲህ የተረከቡት ፖርቹጋላዊ አሰልጣኝ ኮንሴንሳኦ እርሳቸው ቡድኑን ከያዙት ወዲህ መሻሻሎችን እንዳሳዩ ይነገራል።

ኢትዮጵያ
● ተሳትፎ፡ 11ኛ ጊዜ
● ምርጥ ውጤት፡ ሻምፒዮን (1962)
● አሰልጣኝ፡ ውበቱ አባተ
● ኮከብ ተጫዋች፡ ጌታነህ ከበደ
● ምን ይጠብቃሉ፡ የወደቁት አናብስት (the fallen giants) የካፍ፣ አፍሪካ ዋንጫው መስራቾች እና የቀድሞ ሃያል ሃገር ቢሆኑም ከመሰረቱት ውድድር ከሶስት አስርት አመታት በላይ ማለፍ አለመቻላቸውና በ40 አመት ይህ ሁለተኛ ተሳትፏቸው መሆኑ በርግጥም ይህን ስያሜ ያሰጣቸዋል ሲል የዩሮ ስፖርት ዘጋቢው ኢብራሂም ሙስጠፋ ይናገራል።
በአብዛኛው ሃገር በቀል ተጫዋቾችን ያካተተውን ቡድን በውድድሩ ረጅም ርቀት መጓዝ እንደሚከብደው ጠቅሶ በቅርብ የአለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ያሳዩት ብቃት በተለይም ከጋና ጋር አቻ መለያየታቸው በአንፃራዊነት ከእነርሱ በበላይነት ለተቀመጡት የምድብ ሃገራት መልዕክቱ ጠንካራ እንደሚሆን ኢብራሂም ሙስጠፋ ይጠቅሳል። መሰረታቸውን አፍሪካ ውስጥ ያደረጉ በርካታ የስፖርት ድህረ ገፆች የቡድኑን ወጣት የፊት አጥቂ አቡበከር ናስር በማድነቅ በውድድሩ መድመቅ ከሚችሉና ሊታዩ ከሚገባቸው ተጫዋቾች ተርታ ያስቀምጡታል። ይህ የወቅቱ የኢትዮጽያ እግር ኳስ ኮከብና የአምናው የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ፣ ባለ ሪከርድ ተጫዋች በቅርብ አመታት ከኢት ቡና ወጥቶ በውጪ ሃገራት ክለቦች ሲጫወት ልንመለከተው እንችላለን ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። ዋልያዎቹ ከምድብ ካለፉ ከእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የ9 ሚሊዮን ብር ሽልማት ቃል የተገባላቸው ሲሆን አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ቡድኑ ለረጅም ጊዜ አብሮ የቆየ እንደሆነና የማሸነፍ ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስ የ33ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሳይጠበቅ ብዙ ርቀት የሚጓዝ (surprising team) እንደሚሆን አምናለው ሲል በቡድኑ የሽኝት ፕሮግራም ወቅት አስተያየቱን ሰጥቷል።

የጨዋታ መርሃ ግብሮች
እሁድ ጥር 1/2014
● ካሜሩን vs ቡርኪናፋሶ (ምሽት 2፡00 ሰዓት)
● ኢትዮጵያ vs ኬኘ ቨርድ (ምሽት 4፡00 ሰዓት)
ሐሙስ ጥር 5/2014
● ካሜሩን vs ኢትዮጵያ (ምሽት 1፡00 ሰዓት)
● ቡርኪናፋሶ vs ኬፕ ቨርድ (ምሽት 4፡00 ሰዓት)
ሰኞ ጥር 9/2014
● ቡርኪናፋሶ vs ኢትዮጽያ (ምሽት 1፡00 ሰዓት)
● ኬፕ ቨርድ vs ካሜሩን (ምሽት 1፡00 ሰዓት)
ምንጮች፡
● ጎል አፍሪካ ድህረ ገፅ www.goalafrica.com
● ዩሮስፖርት ድህረ ገፅ www.eurosport.com/AfricanCupOfNations
● BBC ስፖርት www.bbc.com