(በዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ)
የ25ኛ ዓመቱን ያከበረው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፈው ዕሁድ በደመቀ እና በተሳካ ሁኔታ ተከናውኗል። የዚህ ተቋም የ25 ዓመት ጉዞው ብሄራዊ አንድምታ ጥልቅ እና ዘርፈ ብዙ ነው። ታሪካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ፣ ስፖርታዊ፣ ትምህርታዊ፣ ከጤና ጉዳዮች ጋር የተገናኙ ፋይዳዎቹ የበረከቱ ናቸው። በተለይም ትምህርታዊ ፋይዳውን በዋናነትም ብሄራዊ አንድምታውን ይህ ጹሁፍ ተመልክቷል። ለዚሁም እንደመነሻ ባለፈው ሳምንት ሀሙስ የአሜሪካው ግዙፍ የፋይናንስ ተቋም ባንክ ኦፍ አሜሪካ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ታሪካዊ የአጋርነት ስምምነትን ማንሳት ይቻላል። ስምምነቱ የስፖርታችንን ስብራት ወደ ብስራት መለወጥ እንደምንችል ያሳየ አጋጣሚነው። 25 አመታትን ቆጥሮ በመዘከር የመጣ ስኬት ብቻ ሳይሆን በራዕይ፣ በእቅድ፣ በዘመናዊ አካሄድና በተቀናጀ ስርአትየተገኘ የልፋት ውጤት ነው። ለአገራችን የስፖርት ዘርፍም ትልቅ መልዕክት የያዘ የአጋርነት ውል ጭምር ነው።
ለ25 ዓመታት የተገነባ ራዕይ
ለታላቁ ሩጫ ጅማሮ መሰረት መጠናከር ድርሻውን እንዳበረከት ሰው፣ ዝግጅቱ የታላቅነት ተስፋን ሰንቆ ተፀንሶየአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ውድድር እስከመሆን መብቃቱን ተመልክቻለሁ። ዋናው መሰረት የተጣለውም ገና ከጅማሬውነበር። ግልፅ አላማና ግብ ይዞ፣ የአንድ ቀን መድረክ ብቻ ሳይሆን አመታትን አሻግሮ የሚመለከት ራዕይ ሰንቆ፣ ባህል ወግናቅርስን ለአለም የማስተዋውቅ አጀንዳ አንግቦ እንዲሁም ሚሊዮኖች ሩጫን እንደ አንድ የህይወት ክፍላቸውእንዲቆጥሩት አስቦ የተቋቋመ፣ ይህንንም ያሳካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም ሆኗል።
ለዚህ ሁሉ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደውና ቀዳሚው ሰው የታላቁ ሩጫ መሰረት ጣይ ታላቁ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ነው። ሀይሌ በአለም አደባባይ ኢትዮጵያን ከማስጠራቱ ባለፈ ሩጫ መለያችን መሆኑን በታላቁ ሩጫ ያሳየተምሳሌታችን ነው። ሌላው ደግሞ ሪቻርድ ኔርውርካር ሙያን ከባለሙያ ስራን ከስነምግባር አገናኝቶ ታላቁ ሩጫን ቅርፅአስይዞ ተቋሙን በሁለት እግሩ እንዲቆም ካስቻሉት ጥቂቶች መካከል ሪቻርድ ኔርውርካር ቀዳሚው ነው። ሪቻርድለስራው የነበረው ትጉህነት እንዲሁም ለእቅድና ለግቡ የሚጠቀመው ስልት በወቅቱ አብረነው ለነበርነው በሙሉየሚጋባና በአርአያነት የሚጠቀስ ነበር። ዳግማዊት አማረ ደግሞ ተቋሙን በበሰለ አደረጃጀት አንፃ በስኬታማ አመራርጠብቃ ቅብብሎሹን ያሳደገች ተጠቃሽ መሪ ነች። እናም እነዚህ መሪዎችና ባልደረባዎቻቸው አንድ የውድድር መድረክብቻ አልፈጠሩም። ህብረትን ያስተዋወቀ በየአመቱ የሚናፈቅ ሁሉን አሰባሳቢ ሀገራዊ ብሄራዊ ተቋም አበረከቱልንእንጂ!
የትርጉም ጽንሰት እና ስፖንሰርሺፕ
አንድ ማህበረሰብ ለነገሮች የሚሰጠውን ትርጉሜና ትርጓሜውም ተቀባይነትን አግኝቶ የሚስተናገድበትን ፍቺ በተለያየ መንገድ ያገኛል።አንዳንዴ በልማድ ሌላ ጊዜ በተሞክሮ ሲልም የአንድን ነገር መረዳት በተረዳበት ፍቺ ልክ ቀድሞለማህበረሰቡ ያካፈለውን ሰው ትርጓሜ በስፋት በመቀበል፣ ወዘተርፈ ሊሆን ይችላል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ስፖንሰርሺፕ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ወይም አስተሳሰብ ነው። ስለ ስፖንሰርሺፕ በሀገራችን ያለው አስተሳሰብና ትርጓሜ እጅጉን የተዛባ፣የተዛነፈና የተሳሳተ ነው። አብዛኛውን ጊዜ ስፖንሰርሺፕ የሚወሰደው እንደ ስጦታ፣ ልግስና አልያም እርዳታ ነው።
እውነተኛ ስፖንሰርሺፕ ንዋየ መዋልን በማፍሰስ አዎንታዊ የጥቅም ምላሽ እንደሚገኝበት በመጠበቅየሚፈፀም የሰጥቶ መቀበል የንግድ ልውውጥ ነው። ስምምነቱ በገንዘብ አልያም በአይነት ሊሆን ይችላል።የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በተለያየ መንገድና አካል ሊፈፀምም ይችላል። ጥቂት ማሳያዎችን እንመልከት። በተለያዩመድረኮች ወይም ዝግጅቶች ለምሳሌ እንደ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባሉት ላይ ወይም በግለሰብ ለምሳሌ ሀይሌ ከአዲዳስጋር አልያም ከተቋም ጋር ለምሳሌ ከሊግ፣ ከብሄራዊ ቡድን፣ ከአለም አቀፍ ዝግጅት አልያም ከስታዲየም ስያሜ ሊሆንይችላል። የገበያ ምላሽን ደግሞ ይጠብቃል። ለምሳሌ አንድ ድርጅት ራሱ ተቋሙን ወይም ምርቱንና አገልግሎቱንለህዝብ ማስተዋወቅ፣ ስለምርቱና አገልግሎቱ አስተማሪ መረጃዎችን ማቅረብ፣ ለገጽታ ግንባታ ጠቀሜታ ማዋል፣በመጨረሻም የሽያጭና ሌሎች ግብረ መልሶችን ያካትታል።
ስፖንሰር አድራጊው ተቋም ገንዘቡን፣ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን ስፖንሰር ለሚደረገው አካል የሚያቀርበውለተመልካቹ፣ ለተሳታፊው፣ ለደንበኛው ወይም ለደጋፊው በመድረስ ትስስሩ የሚፈጥርለትን መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞየቢዝነስ አላማዎቹን ለማሳካት ነው። ለዚህ ደግሞ ስፖንሰርሺፕ አራት መሰረታዊ የንግድና የተግባቦት ደረጃዎችንይከተላል። የመጀመሪያው ግንዛቤን መፍጠር ወይም እይታን መጨመር ነው። ህብረተሰቡ ስፖንሰር አድራጊውንእንዲያውቀው ማድረግ ቀዳሚ ስራ ይሆናል። የስፖንሰሩን ምርት፣ ምልክት ወይም አገልግሎት ማሳወቅ ይጠበቃል።ሁለተኛው ስለ ስፖንሰሩ ማስረዳት ወይም ማስተማር ነው። የመጀመሪያውን የስፖንሰርሺፕ ደረጃ አስታኮ አገልግሎቶችን እና ምርቶችን ከሌሎች ተመሳሳይ በገቢያው ውስጥ ካሉ ተወዳዳሪዎች የሚለዩባቸውን ባህርያትንና ተመራጭነትን ማስረዳትና አጉልቶ ማውጣት ማስቻል ነው። ሶስተኛው ደረጃ የስፖንሰሩን ገጽታ መገንባት ነው። ያለውን ግንዛቤማሳደግና መልካም ምስልን በሰዎች አእምሮ ውስጥ ማስረጽ ነው። አራተኛውና የመጨረሻው ሽያጭ ነው። የደንበኛንፍላጎት ያማከለ፣ በታማኝነት ሽያጭ ማከናወን ነው። የማንኛውም ስፖንሰር ዋነኛ ግብ ደግሞ ሽያጭ ነው። የሶስቱደረጃዎች የሂደት መጨረሻም አራተኛው ላይ ማለትም ሽያጩ ላይ ማረፍ ይሆናል።
ብዙ ጊዜ ከላይ የጠቀስኳቸውንና ሌሎች ዝርዝር የስፖንሰርሺፕ ባህሪና ትግበራ ለመማርና ለማጥናት ወደትምህርት ቤት የሚሄዱ አልያም መፅሀፍትን የሚያገላብጡ ብዙ ናቸው። በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርት ተቋማት ግንእንደ እኔ እይታ ይህንን ማድረግ ይበረታታሉ ነገር ግን የግድ ላይላቸውም ይችላል። ምክኒያቱም አገር በቀል ተሞክሮውንም ማኑዋሉንም ከፊታቸው ያገኙታል። ለዚህም ታላቁ ሩጫ ለባለፉት 25 አመታት በዘርፉ የፈፀመውንስኬት ማጥናት ሁነኛ አማራጭ ነው።
የባንክ ኦፍ አሜሪካ አጋርነት ብሄራዊ አንድምታ
በስፖንሰርሺፕ ውስጥ “Reverse Image Effect” የሚባል መርህ አለ። አንድ በአለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና ታላቅብራንድ በአንድ አገር ከሚገኝ ስፖርታዊ ተቋም ጋር በስፖንሰርሺፕ አጋርነት ለመስራት ሲስማማ፣ የአለም አቀፍ ተቋሙታላቅነት፣ ተቀባይነት፣ ክብር፣ ተአማኒነት፣ ወዘተርፈ ያሉ አዎንታዊ ገጽታዎች ወደስፖርታዊ ተቋሙ ትርጉም ባለውመልኩ የመሻገር አቅማቸው የተሳለጠና ያየለ መሆኑን በርካታ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶች አረጋግጠዋል። ባንክ ኦፍአሜሪካ መምጣቱም ታላቁ ሩጫ የነበረውን ተቀባይነት፣ ክብር፣ ተአማኒነት፣ታዋቂነት ወዘተርፈ በአገርና አለም አቀፍደረጃ የበለጠ ያሳድጋል። ለሌላ የንግድና የስፖንሰርሺፕ አቅምም ተጨማሪ ጉልበት ይፈጥራል፣ በር ይከፍታል።
የሁለቱ ተቋማት የአጋርነት ስምምነት ለታላቁ ሩጫ ከሚኖረው “Reverse Image Effect” ባሻገርም ለመላውየኢትዮጵያ ስፖርት ዘርፍ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው። በባለሙያ የሚመራ፣ ለገበያ የሚያበቃ አወቃቀር ለፈጠረአገራዊ ተቋም አለም አቀፍ ድርጅቶች አብረው ለመስራት እንደሚመጡ ማሳያ ጭምር ነው። በሀገራችን ያሉየእግርኳስ፣ ብስክሌት፣ ቦክስ፣ ቅርጫትኳስ፣ ቮሊቦልና ሁሉም ስፖርቶች በምን መንገድ ራሳቸውን ለገበያ ማቅረብእንዳለባቸው የሚያሳይ የማንቂያ ደውል ጭምር ነው።

እግርኳስና የሚያስፈልገው አስቸኳይ ለውጥ
ከሁለት አመት በፊት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጋር በመቀናጀት ሁለት አመት የፈጀና በሀገራችን እግርኳስ ልማት ዙሪያ ያጠነጠነ ጥልቅ እና ሰፊ ጥናት ተካሂዶ በመጸሃፍ መልክ ለሊጉ አዘጋጅቼ አቅርቢያለሁ። ጥናታዊ ፅሁፉ 370 ገፅያሉት ከ140 ሀገራት በላይ ተሞክሮን ያካተተ ከ15 የኢትዮጵያ እግርኳስ ባለድርሻ አካላት ማለትም ከፌዴሬሽኑ፣ ከክለቦች፣ከተጫዋቾች፣ ከወኪሎች፣ ከጋዜጠኞች፣ ከምሁራንና ከሌሎች የተውጣጡ ከ90 በላይ ሰዎችን ቃለመጠይቅ በማድረግየተዘጋጀ ነበር። በተጨማሪ ሀገር አቀፍ፣ አህጉራዊ፣ አለም አቀፋዊና የፊፋ ፖሊሲ ተሞክሮዎች የተመለከተ፤ የህግ ማእቀፎችን ያጣቀሰ፣ ከ200 በላይ የምርምር ጥናት ፅሁፎችን ያማከረ ጥልቅ፣ ሰፊና ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና አገር በቀል የልማት ፍኖተ ካርታ ያቀረበ የምርመራ ውጤት ነው። እንደ አንድ ዜጋም ያለኝን የሰጠሁበት እስካሁንም በትምህርት ሞያዬ ካካፈልኳቸው የሳይንሳዊ ጥናታዊ ጽሁፎች ልዩ እና ቀዳሚ ቦታ የምሰጠው የስራ ውጤት ነው።
የጥናቱ ውጤት ደግሞ ግልፅና አጭር ነው። በኢትዮጵያ እግርኳስ አሁን ያለው አሰራር በተለይ በፋይናንስ በኩልፍሬ አልባ ብክነት መሆኑን ያሳያል። በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ከመንግስት በጀት ድጋፍነው። አብዛኞቹ በአማካይ በአመት 75 ሚሊየን ብር አካባቢ ያወጣሉ። ከዚህ ውስጥ 75% ያህሉ የሚውለው ለደሞዝክፍያ ነው። ቀሪው ለትራንስፖርትና ለሌሎች አቅርቦቶች ይከፈላል። ለመሰረተ ልማት፣ ለማርኬቲንግና ለረጅም ጊዜልማታዊ እቅድ የሚውለው ግን ኢምንት ነው። ይህ ደግሞ ዘለቄታዊነት ያለው የስፖርት እድገት ግንባታ አይደለም።አሸዋ ላይ ውሃ ሲያፈሱ እንደመኖር እንጂ።
ክለቦችን በማህበረሰብ ባለቤትነት የማስተዳደር ሃገራዊ መፍትሄ
በጥናቱ ነጥረው ለወጡት ውስብስብ እና ሥር ሰደድ ችግሮች መሰረታዊ መፍትሄው ማህበረሰቡን የክለቦች ባለቤት አድርጎ በሀገር ሰው ሀገራዊ እድገት የማምጣት ሞዴልን መከተል ነው። የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲየሚፈቅደውም የሚያዘውም ይሄንኑ ነው። ፖሊሲው በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ እንዳስቀመጠው ማህበረሰቡየክለብ ባለቤት ይሆናል፤ መንግስት የስፖርት ልማትን ያመቻቻል፤ ያግዛል፤ ይላል። ከዚህ በተቃራኒ እና ፖሊሲውን በተጻረረመልኩ በተግባር የሚታየው የክለቦች ባለቤትነት ግን በአብዛኛው (ከጊዮርጊስ እና ቡና በስተቀር) የተያዘው በአካባቢያዊመንግስታት ነው። እዚህ ጋር ‘በመንግስት ባለቤትነት መያዝ’ እና ‘በአካባቢያዊ የመንግስት አካላት ባለቤትነት መያዝ’ ለየቅል መሆናቸውን ልብ ሊሉ ይገባል።
ጥናቱ የክለቦች ባላቤትነትን ከአካባቢያዊ የመንግስት አካላት ሙሉ በሙሉ ቁጥጥር ስር ማውጣት የእግርኳሱዘርፈ ብዙ እና ውስብስብ ችግሮች የመጀመሪያው መፍትሄ መሆኑን አጉልቶ አሳይቷል። በጥናቱ ምክረ ሀሳብ መሰረትም(በተጓዳኝም ህጋዊውን የፖሊሲ አቅጣጫ ለመከተል) የአንድ ክለብ የባላቤትነት ድርሻ መጠን ድልድልን እንደሚከተለውአስቀምጧል (በዚህ ዙሪያ የበለጠ እና ጥልቅ ትንታኔ ለማግኘት መጸሃፉን ይመልከቱ)፦ የተመዘገበ ደጋፊ 30%፣ ህዝብ40%፣ እንዲሁም መንግስት 30% ድርሻ መያዝ ነው። ህዝብ የሚለው ቃል ደግሞ ሰፊ እና አቃፊ ነው። ይሀም በአካባቢው የሚኖሩ ግን በደጋፊነት ያልተመዘገቡ ነዋሪዎች፣ ክለቡ በሚገኝበት ያሉ የንግድ ተቋማት ባለቤቶች፣ የሆቴልና ሞቴል ባለቤቶች፣ ባንኮች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቢራ ፋብሪካዎች፣ ዲያስፖራዎችና ሌሎችን ያካትታል። በረጅምጊዜ እቅድ ደግሞ የውጭ ሀገር ባለሀብቶችን መጨመር ይቻላል።
ይህ ሞዴል የክለብ አመራሮች ላይ ተጠያቂነትን ይፈጥራል እና ብቁ የስፖርት ንግድ አስተዳዳሪዎች ክለቦቹንእንዲመሩ ይጋብዛል። በተለይ ከፖለቲካ አመራሮች ጣልቃ ገብነት በራቀ መልኩ ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ፣ በሞያ ብቃትእና አቅም ላይ የተመረኮዘ የስፖርት አመራርን ከነተጠያቂነቱ ለመመደብ ያስችላል፤ የስፖርት ንግድ ባህልን ለማስረጽየተመቸ ይሆናል፣ ፈጠራ የታከለበት የገቢ ምንጭ ለመተግበር የሚያበረታታ አውድን ይፈጥራል። ከሁሉ በላይምከኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ስፖርታዊ እና ባህላዊ እውነታዎች ጋር የታረቀ እና ዘለቄታነት ያለው የእግር ኳስልማት ማስፈን ያስችላል። በጥቅሉም አገር በቀል የክለቦች ባለቤትነት ሞዴሉ ክለቦች በራሳቸው ፈጠራ እንደ ታላቁ ሩጫ ገቢ አመንጭተው ራሳቸውን ማስተዳደር እንዲችሉ፣ የአካባቢያዊ መንግስት አካላትም አሸዋ ላይ ከሚያፈሱት ውሃ ይለቅ በጀቱን ለደሃው ህዝባችን ትምህርት ቤት፣ ጤና ኬላ፣ የኮብል-ስቶን መንገድና የቤት ግንባታ ላይ እንዲያውሉት ያስችላል፤ በዋናነትም ለረጅም ጊዜ ርቆን የቆየውን የእግር ኳስ ብሄራዊ ድል ለማግኘት ጭላጭል የሚሰጠን፣ በጊዜ ሂደትም የሚያጎናጽፈን ዘላቂነት ያላው አካሄድ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
ተምሳሌቱ ደግሞ አጠገባችን ይገኛል
በኢትዮጵያ የሚገኙ የስፖርት ተቋማት ስኬታማ የስፖርት ተቋም እንዴት እንደሚገነባ ለማወቅ ከሀገር ውጪማየት አይጠበቅባቸውም። ትልቁ ተምሳሌት እዚሁ ሀገር ቤት ይገኛል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተግባር ተፈትኖበባለሙያና በጠንካራ አመራር ተመርቶ በማህበረሰቡ ታቅፎ ራሱን በማስታዋወቅና በመሸጥ ስኬታማ መሆኑንንበተግባር አሳይቷል። ብዙ ክለቦችና ፌዴሬሽኖች ያቃታቸውንና እስካሁን የሚታገሉበትን ራስን ችሎ መውጣትን ራስንመሸጥን አሳክቷል። ከትንሽ ሃሳብ ተነስቶ ብሄራዊ ተቋም ሆኖ የአለም አቀፍ አጋሮችን ቀልብ ስቧል።
ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙት እንደ ሌሎቹ የስፖርት ፌዴሬሽኖችና ተቋማት ተመሳሳይ የማርኬቲንግ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ቢገኝም ሰንሰለቱን በጥሶ ወጥቷል። ልዩነት ማምጣትን ፈልጎ ብቻ ሳይቀመጥተለይቶ ወጥቷል። ስፖርትን እንደ ቢዝነስ ወስዶ ማህበረሰቡን አሳታፊና አጋር እንጂ የሩቅ ተመልካች ሳያደርግ ተንቀሳቅሶግቡን አሳክቷል።
ታላቁ ሩጫ ቤት ውስጥ ስለ ስፖንሰርሺፕ ጥልቅ መረዳትና ግንዛቤ ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነቱ መልፋት ጭምርአለ። ከተለምዷዊው የስፖንሰር ግንዛቤ ወጣ ብሎ ሰጥቶ በመቀበል መርህ ራስን ማስተዋወቅ፤ ምርትና አገልግሎትንማስረዳት፣ ገጽታን መገንባት፣ ብሎም ምርትና አገልግሎትን የመሸጥ አስተሳሰብ የሰረፀበት ተቋም ነው። ከባንክ ኦፍአሜሪካ ጋር የተደረገው የስፖንሰርሺፕ ስምምነትም ድንገት የመጣ ሲሳይ አይደለም። ከሁለት አስርት አመታት ከግማሽበታታሪነት በፕሮፌሽናል አመራርና የገጽታ ግንባታ ጥረት የመጣ የልፋት ውጤት ነው።
በመንግስት ትከሻና በጀት ላይ ላሉ ክለቦች፣ ሊጎችና ፌዴሬሽኖች ታላቁ ሩጫ ቀላል ግን ጠንካራ መልዕክትአስተላልፏል። ተቋም እንዴት እንደሚመራ ከአጋሮች ጋር እንዴት ስምምነት እንደሚፈፀም በተግባር አሳይቷል። ለዚህምነው ወደ ውጪ ተመልክቶ ጥናት ፍለጋ ከመባዘን አጠገባችን ያለውን ታላቁ ሩጫ በተምሳሌትነት መውሰድየሚያስፈለገው። አርአያ ፍለጋ የውጭ ሀገር ተሞክሮን ከመፈለግ ይልቅ በየአመቱ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሺዎች አንድቤተሰብ ሆነው የሚውሉበትን መድረክና ተቋም እንድንመለከት የግድ የሚለን።
አርአያነትና የብር እዮቤል በአል አከባበር
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 25ኛ አመቱን ከማክበሩ ጎን ለጎን ሀገራዊ አርአያነቱን አሳይቷል። አንድ የስፖርት ተቋምበስነ ምግባር በንግድ ሃሳብና እቅድ ተመርቶ ስኬታማ ሲሆን ሌላው አለም ሌላው ተመልካች ማስታወሻ ይይዛል። አብሮለመስራት የስምምነት ሰነድ ይዞ ይመጣል። ለዚህ ደግሞ የባንክ ኦፍ አሜሪካ አጋርነት አንዱ ማሳያ ነው። ይህከስፖንሰርሺፕ ስምምነት በላይ ነው። ለ25 አመታት በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ የተገነባ ፍኖተ ካርታና የስራ ድምር ውጤትነው
ይህ ምን ያሳያል? እ.ኤ.አ. በ2006 በታላቁ ሩጫ አማካይነት በእንግሊዝ አገር የስፖርት ማኔጅመንት ስማር አንድመጣጥፍ ለጋዜጣ ፅፌ ነበር፤ ርዕሱ “በታላቁ ሩጫ ሁሉም አሸናፊ ነው” ይላል። ለኔ ታላቁ ሩጫ የጎዳና ላይ ውድድር ብቻአይደለም።
ከስፖርትነቱ ባለፈ የጤናማ አኗኗር ማሳያ የማህበራዊ ህይወት ምሳሌ የታሪክና የባህል ማስተዋወቂያ ማዕከልጭምር ሆኗል። በተጨማሪ ህዝብን ወደ አንድ ያመጣ ትውልድን ያነሳሳ ኢኮኖሚው ላይ የራሱን ጠብታ የጨመረበአለም የኢትዮጵያን ምስል በበጎ ያሳወቀ እንዲሁም ሩጫ ባህላችን መሆኑን ያሳየ ብሄራዊ ተቋም ለመሆን የበቃ ነው።በእነዚህ ምክንያቶች የበለጠ ድጋፍና ጥበቃ ክብርና ምስጋና ለተቋሙና ለመሪዎቹ ያስፈልጋል። በስፖርቱ ዘርፍ ሀገርንየመገንባት ስራ ላይ ናቸውና ይበልጥ እገዛ ያስፈልጋቸዋል።
የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት
የማጠቃለያ ሃሳቤ ምስጋናና የደስታ መልዕክት ይሆናል። በቅድሚያ ለባለራዕዩ ታላቁ አትሌት ሀይሌ ገ/ስላሴ ያለኝንአክብሮትና አድናቆት መግለፅ እፈልጋለሁ። በአለም አደባባይ በእግሮቹ ተአምር ሰርቶ ሰንደቃችንን ከፍ አድርጎ ብሄራዊመዝሙራችንን አዘምሮ ሀገራችንን አስጠርቷል። ካስለመደን ድልና ሜዳሊያ በኋላም ሀገር ማስጠራቱን ቀጥሎበታል። እንደግለሰብ እኔንም በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት የምርምር እና የማስተማር ዘርፍ እንድሰማራ መነሻ ሆኗል። በአገሪቷ ሩጫ የህይወታችን አንዱ ክፍል እንዲሆንአንድነትን የሚፈጥር መሰባሰቢያ መድረክ ፈጥሮልናል። ሀይሌ ታላቁ ሩጫን ወልዶልናል። ታላቅ ምስጋና ይገባዋል።
በታላቁ ሩጫ ጅማሬ ቢሮ ውስጥ ከነበሩ ሁለት/ ሶስት ባለሙያዎች አንዱ በመሆኔ እድለኛ ነኝ። መሰረትን መጣልከባዱ ስራ ነው። ለ 25 አመት በወጥነት በጠንካራ መሰረት በራዕይ በአላማና ግብ ማስቀጠል ብሎም ስኬታማ ማድረግናለዛሬ ማብቃት ደግሞ ዋነኛው እና ትልቅ ስኬት ነው። ይህ ሁሉ በእድል አልመጣም። በከፍተኛ ደረጃ አመራርናያለመሰልቸት በመስራት የመጣ ውጤት ነው። ለዚህም ሌላኛው ተመስጋኝ ሪቻርድ ኔርውርካር ይሆናል። የእሱ የላቀ የስራ ባህል፣ በሳል አመራርና እቅድ ታላቁ ሩጫን ወደ ላቀ ደረጃ አሻግሮታል። የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ትልቁዝግጅት ሆኗል። ታላቅ ምስጋና ይገባዋል።
ዳግማዊት አማረ ሌላኛዋ ምስጋናና አድናቆት የሚገባት የታላቁ ሩጫ የጀርባ አጥንት ነች። ተቋሙን በላቀአመራር በማስቀጠልና በማሳደግ እዚህ ደረጃ አድርሳዋለች። ታላቅ ምስጋና ይገባታል።
በመጨረሻ ታላቁ ሩጫን አምናችሁበት ይህንን የአጋርነት ስምምነት ለፈፀማችሁት ባንክ ኦፍ አሜሪካ እንኳንደህና መጣችሁ እላለሁ። ታላቁ ሩጫ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ሌሎች የስፖርት ተቋማት ደግሞ ከዚህ ተማሩ ማለትእፈልጋለሁ። አገር በቀል ተሞክሮውም ማኑዋሉም ከፊታችሁ ነው።
ስለ ፀሀፊው፦
ዶ/ር ጋሻው ዘርጋው አብዛ በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩኒቨርስቲ የስፖርት ቢዝነስ ማኔጅመንት ፕሮፌሰርና ተመራማሪ ናቸው።ለታላቁ ሩጫ ጅማሮ መሰረት ከጣሉት አንዱ የሆኑት ዶ/ር ጋሻው ይህንን ተሞክሮ ወደ አሜሪካ በመውሰድ ግራንድ አፍሪካ ረንንመስርተዋል፤ ዘንድሮ ሰባተኛ አመት ውድድሩን በደማቁ በዋሽንግተን ዲሲ አከናውኗል። በስፖርት ስፖንሰርሺፕ፣ በስፖርት ቢዝነስናማርኬቲንግ ዙሪያ በርካታ መፅሀፍትን የፃፉ አለም አቀፍ ተቋማትን የሚያማክሩና የሚያስተምሩ ምሁር ናቸው። በጀርመን ሙኒክ ቢዝነስ ስኩል ደግሞ የዶክትሬት ተማሪዎችን በስፖርት ቢዝነስ ዙሪያ ያማክራሉ። ዶ/ር ጋሻው እስካሁን 10 መፅሀፍትንአሳትመዋል። በስፖርት ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ከ100 በላይ የሳይንሳዊ ምርምር የህትመት ውጤቶችን ለአንባቢ አቅርበዋል።





