
የቶኪዮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፕዮና የሴቶች የ10000ሜ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቷ ቢያትሪስ ቼቤት ከአራት ሳምንታት በፊት በዳይመንድ ሊግ 1500ሜ ሮጣለች።
ቼቤት በተለምዶ የ1500ሜ ራጭ አይደለችም። በኬንያ ሻምፕዮና፡ የጦር ሰራዊቱ ውድድር ወይም ለዓለም ሻምፕዮና ማጣሪያ ካልሆነ በስተቀር ደጋግማ የምትሮጠው ውድድር አይደለም።
የዓለም አትሌቲክስን በዚህ ርቀት አትሌቷ ያስመዘገበችውን ምርጥ 10 ፈጣን ሰዓት ብትጠይቁት የሚሰጣችሁ ስድስት በይፋ የተመዘገቡ ውድድሮችን ነው።
ከወር በፊት ግን በዳይመንድ ሊግ 1500ሜ ከጉዳፍ ፀጋይ ጎን ተሰለፈች። ከአራት ደቂቃ በታች ሮጠች። ለ10000ሜ ተዘጋጀች። ምክንያቱም ብዙዎቻችን እንደምናስበው ጉዳፍ በተለምዶ የ1500ሜ ሯጭ ስለሆነች አራት ዙር አካባቢ ሲቀር ዙሩን አፍጥና ውድድሩን የ1500ሜ ፍልሚያ ታደርገዋለች የሚል ነበር። ቼቤት ያሰበችውም ይህን ነው።
ጉዳፍ ዙሩን ለማፍጠን የሞከረችው ግን 1000ሜ ሲቀር ነው። ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየትም “ዘጠኝ ኪ.ሜ. ላይ ውድድሩን ተቆጣጥሬው ነበር። ከዚያ ለመፍጠን ሞከርኩ። የታክቲክ ስህተት አይደለም” ያለችውም ለእዚህ ነው።
በአካል ብቃት ለፈጣን አጨራረስ ዝግጁ እንደነበረች ብትናገርም ለማፈትለክ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም። ምቾት የነሳት ነገር እንደነበር ግልፅ ነው። ጉዳፍ ምክንያቱን ስታስረዳ “ለሞቃት አየር ፀባይ ብዘጋጅም ወበቁ ያልጠበኩት ነበር” ብላለች ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ቼቤት ምቾት ላይ ነበረች። ምክንያቱም በ10000ሜ ውስጥ ራሷን ለ1500ሜ ፍልሚያ አዘጋጅታለች።
“ከባድ እና በጣም ታክቲካዊ ውድድር ነበር። የመጨረሻውን 800ሜ የሮጥኩት በኃይል ነው። ጉዳፍ ከባድ ጫና ብታሳርፍብኝም መፋለም ነበረብኝ። (በዳይመንድ ሊግ) 1500ሜ ሮጫለሁ። ስለዚህ በአዕምሮዬ የ1500ሜ ውድድር ላይ ነበርኩ” በማለት ቼቤት የዳይመንድ ሊግ ዝግጅቷ እንዴት እንደጠቀማት ከውድድሩ በኋላ ተናግራለች።
ለአሰልጣኞቻችን ትልቁ ጥያቄ የሚመጣው እዚህ ላይ ነው። ቼቤት የተጋጣሚ ትንተና ሰርታለች። ለዚህም ተዘጋጅታለች። ጉዳፍ ለምትጠይቃት ጥያቄዎች ሁሉ የኬንያዊቷ አሰልጣኝ መልስ አዘጋጅቶላታል።
የጉዳፍ አሰልጣኝስ? ለሁሉም ሁናቴዎች ምላሽ ተዘጋጅቶ ነበር? ወይስ ዝግጅቱ በአትሌቷ ጥረት እና ተሰጥኦ ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው?
(ይህ ፅሁፍ ጉዳፍን ለመውቀስ የተፃፈ አይደለም። አትሌቶቻችን በትንሽ እገዛ፣ በብዙ ልፋት እና ፈተና ከታላላቆች ጋር እንደሚፋለሙ ግልፅ ነው። ሆኖም ባለፉት ዓመታት ብዙ እንደተባለው ስልጠናና የውድድር ዝግጅታችንን መፈተሽ እንደሚገባን የዛሬው ፉክክር እና የሩጫ በኋላ አስተያየት ልዩ ምሳሌ ነው)





