በረከት ፀጋዬ

ቶታል ኢነርጂስ አፍሪካ ዋንጫ ካሜሩን 2021 በአፍሪካ ትልቁ የውድድር መድረክ ሲሆን ከአለም አቀፍ የእግር ካስ ውድድሮች አለም ዋንጫና አውሮፓ ዋንጫ ቀጥሎ ሶስተኛው ትልቅ እግር ኳሳዊ ውድድር ነው።
ካፍ ከቶታል ኢነርጂስ ጋር ከገባው የስምንት አመት የአጋርነት ስምምነት አንዱ ይህ ውድድር በዚሁ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስፓንሰር አድራጊነት (title sponsor) ጋር በተገናኘ የውድድሩ ስያሜ ‘ቶታል ኢነርጂ አፍሪካ ዋንጫ ካሜሩን 2021’ ሊባል ችሏል።

በካሜሩን ማን ይነግሳል? ከዚህ ቀደም ውድድሩን ማሸነፍ ከቻሉ አስራ አራት ሃገራት አንዷ ወይስ እንደ ሰኢዶ ማኔ፣ ኤድዋርድ ሜንዲን የመሳሰሉ ከዋክብትን ይዛ ከዚህ ቀደም በሁለት ፍፃሜዎች የተሸነፈችውና ምንም ጊዜ ዋንጫውን ያላሳካችው ሴኔጋል አልያም ከሌሎች ተጣባቂ ሃገራት አንዷ ባለ ድል ይሆናሉ? ከጥር 1 እስከ 29 2014 ዓ.ም ድረስ የሚካሄደው ይኸው ውድድር መልሱን ይነግረናል።
ቀጣዩ አጭር ጥንቅርም የዚህን ውድድር መጀመሪያ መቃረብን አስመልክቶ ቁጥራዊ መረጃዎችንና አንዳንድ ጠቃሚ እውነታዎችን ይዳስሳል። መልካም ንባብ!
▶ ቁጥራዊ መረጃ
2
በቶታል ኢነርጂስ ካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳትፎ የሚያደርጉ ሃገራት ሲሆኑ እነዚህ እንግዳ ሃገራት ጋምቢያ እና ኮሞሮስ ናቸው።
3
ብሄራዊ ቡድኖች በመጀመሪያ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋቸው ባለ ድል መሆን የቻሉ ብቸኛ ሃገራት ሲሆኑ እነርሱም ግብፅ (1957)፣ ጋና (1963) እና ደቡብ አፍሪካ (1996) ናቸው።
በተከታታይ ሶስት ጊዜ (2006፣2008፣ እና 2010) ዋንጫውን ከፍ በማድረግ ብቸኛዋ ሃገር የመድረኩ ባለ ብዙ ጊዜ አሸናፊ ሃያሏ ግብፅ ናት።
ሶስት ቡድኖች ግብፅ (1957፣59)፣ ጋና (1963፣65)፣ እና ካሜሩን (2000፣02) ሁለት ጊዜ በተከታታይ በማሸነፍ ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍሯል።
5
የተለያዩ ከተሞች ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን አጠናቀው እንግዶቻቸውን በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ። እነዚህም የመዲናዋ ያውንዴ ሁለት ስታድየሞች፣ ዱዋላ፣ ሊምቤ፣ ጋሩዋ እና ባፎሳም እያንዳንዳቸው አንድ ስታዲየሞች ከመክፈቻ እስከ ፍፃሜ የሚካሄዱትን ጨዋታዎች ያስተናግዳሉ።
አምስት ጊዜ ውድድሩን በማስተናገድ ግብፅ ልክ እንደ ሻምፒዮናነቷ፣ ተሳትፎዋና የተጫዋቾቿ የግል ሪከርዶች ሁላ አንደኛ ላይ ተቀምጣለች። እ.ኤ.አ 1956፣74፣86፣ 2006፣19 አስተናጋጅ ሃገር ፈርኦኖቹ ነበሩ።
6
ስታዲየሞች ለውድድሩ ብቁ ሆነው ጨዋታዎችን ያስተናግዳሉ። እነዚህም በርዕሰ ከተማዋ ያውንዴ የሚገኙት ኦለምቤ ስታዲየም (60,000 ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው)፣ ስታድ አህማዱ አጆ (42,500) ሲሆኑ ቀሪዎቹ አራት የመጫወቻ ሜዳዎች ጃፖማ ስታዲየም ዱዋላ (50,000)፣ ሊምቤ ስታዲየም, ሊምቤ ከተማ እና ኩዊኮንግ ስታዲየም, ባፎሳም ከተማ ሁለቱም (20,000 የመያዝ አቅም ያላቸው) እና ሮምዴ አጂ ስታዲየም ጋሩዋ (30,000) ናቸው።
8
ብሄራዊ ቡድኖች አስተናጋጅ ሃገር ሆነው ዋንጫውን እዛው ማስቀረት ችለዋል። ግብፅ (1959፣86፣ 2006)፣ ጋና (1963፣78)፣ ኢትዮጵያ (1962)፣ ሱዳን (1970)፣ ናይጄሪያ (1980)፣ አልጄሪያ (1990)፣ ደቡብ አፍሪካ (1996)፣ ቱኒዝያ (2004) የዚህ ታሪክ ባለቤቶች ናቸው።
9
በአንድ አፍሪካ ዋንጫ በርካታ ግብ ማስቆጠር በቻለ ተጫዋች የተያዘ ሪከርድ። ይህ ተጫዋች የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአጥቂ ስፍራ ተጫዋች ንዳዬ ሙላምባ ሲባል ይህን ታሪክ ያስመዘገበውም እ.ኤ.አ በ1978 የግብፅ አፍሪካ ዋንጫ ነበር።
10
ከኮንፌዴሬሽኑ አባል ሃገራት እስካሁን ምንም የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ያላገኙ ሃገራት ቁጥር ሲሆን እነዚህም ጎረቤቶቻችን ኤርትራ፣ ሱማልያ፣ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን፣ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሲሺየልስ፣ ሌሴቶ፣ ሳኦቶሜና ፕሪስንፔ፣ ስዋቲኒ እና ቻድ ናቸው።
14
የተለያዩ ሃገራት ዋንጫውን ወደ ላይ ከፍ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ግብፅ (7 ጊዜ)፣ ካሜሩን (5 ጊዜ) እና ጋና (4 ጊዜ) ሻምፒዮን በመሆን ከ1ኛ-3ኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። ቀሪዎቹ አሸናፊዎች ናይጄሪያ(3) አልጄሪያ፣ አይቮሪኮስት፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ (2) እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኮንጎ፣ ዛምቢያ፣ ደ/አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ እና ቱኒዝያ (1) ናቸው።
15
ጊዜ በተከታታይ በአፍሪካ ዋንጫ በመቅረብ ቱኒዝያ ባለ ሪከርድ ሆና ስሟ ተመዝግቧል (ከ1994 እስከ 2021 ድረስ ብንመለከት ‘የካርቴጅ ንስሮቹ’ የሌሉበትን ድግስ ማግኘት አንችልም።)
18
የውድድሩ የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የአስተናጋጇ ሃገር ታሪካዊ ተጫዋች ሳሙኤል ኤቶ ያስቆጠረው የግብ ብዛት።
24
በውድድሩ ላይ የተካፋይ ሃገራት ብዛት፦ ከዚህ ቀደም የ16 ሃገራት ፎርማት ይከተል የነበረው ካፍ ወደ 24 ሃገራት ተሳትፎ የመጣው ከግብፁ የ2019 አፍሪካ ዋንጫ አንስቶ ነበር።
25
ጊዜ በውድድሩ ላይ በመካፈል ግብፅ የሪከርዱ ባለቤት ናት።
33
ቶታል ኢነርጂስ አፍሪካ ዋንጫ ካሜሩን 2021 የውድድሩ 33ተኛው መድረክ ሆኖ ከጥር 1 ጀምሮ መካሄድ ይጀምራል።
36
በውድድሩ ታሪክ በርካታ ጨዋታዎችን ያደረገው ሌላኛዋ የአስተናጋጇ ሃገር ገናና የቀድም ተከላካይ ሪጎበርት ሶንግ ሲሆን ያደረገው የጨዋታ ብዛትም ከላይ በቁጥሩ የተጠቀሰውን ነው።
40
ካፍ በውድድሩ በተለያየ ረገድ በሽልማት መልክ ለብሄራዊ ቡድኖች ያዘጋጀው ገንዘብ (በሚልዮን ዶላር)
52
በውድድሩ የሚደረገው አጠቃላይ የጨዋታ ብዛት።
102
ጎሎች የተቆጠሩበት የግብፅ አፍሪካ ዋንጫ በውድድሩ ታሪክ ከፍተኛውን የግብ መጠን ያስተናገደ ሆኖ አልፏል። 102 ግቦችን በ52 ጨዋታዎች አስተናግዷል። ( ይህም በአዲስ ፎርማት የተሳታፊ ሃገራትን ቁጥር ወደ 24 አሳድጎ የተካሄደ የመጀመሪያው አፍሪካ ዋንጫ እንደነበር እናስታውሳለን።)
1957
የአህጉሪቱ ትልቁ የእግር ኳስ ድግስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደበት ዓ.ም ሲሆን ተሳታፊ ሃገራት ሶስት ብቻ የነበሩበት በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ አነስተኛ ጨዋታና የግብ መጠን የተመዘገበበት ሆኖ አልፏል (7 ግቦች፣ 2 ጨዋታ። ) የመጀመሪያዋን የውድድሩ ግብ ማስቆጠር የቻለው ግብፃዊው ራፋት አቲያ ከአስተናጋጇ ሃገር ሱዳን ጋር እ.ኤ.አ የካቲት 10 ቀን 1957 በተካሄደ ጨዋታ ላይ ነበር።
ይህን ያውቃሉ?
▶️ በሽልማት መልክ ሚበረከተው የአሁኑ ዋንጫ ለአሸናፊዋ ሃገር የሚበረከት ሶስተኛው ዋንጫ ነው። በመጀመሪያው የካፍ ፕሬዘደንት አብደላዚዝ አብደላ ሳሌም የተሰየመውና ከነሃስ የተሰራውን የመጀመሪያ ዋንጫ ጋና እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም በማሸነፍ ዋንጫውን ማስቀረት ችላለች።
▶️ አይቮሪኮስት በአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ አንድም ግብ ያላስቆጠረች እንዲሁም ምንም ግብ ያላስተናገደች ብቸኛዋ ሃገር ነች። (ይህም በመለያ ምቶች ሻምፒዮን የሆነችባቸውን ሁለት ፍፃሜዎች ማስታወስ የግድ ይሏል)
▶️ አንድ ተጫዋች ብቻ በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ የውድድሩ ኮከብ ሽልማትን ሁለት ጊዜ ማሳካት ችሏል። እርሱም ግብፃዊው አማካይ አህመድ ሃሰን ሲሆን በ2006 እና 2010 ዓ.ም የተካሄዱት ውድድሮች ኮከብ ይሄው ግብፃዊ ነበር።
▶️ ሃገራችን ኢትዮጵያ በውድድሩ ታሪክ ከከፍተኛ ግቦች አንፃር በመጥፎ ሪከርድ ስሟ በታሪክ መዝገብ ላይ ሁለት ጊዜ ሰፍሮ ይገኛል። ይህም በአፍሪካ ዋንጫው ታሪክ የመጀመሪያው ሃትሪክ የተሰራው በግብፃዊው መሃመድ ዲያብ አል-አታር ወይም ‘አድ ዲባ’ የ1957 ዓ.ም የፍፃሜ ፍልሚያ ሲሆን ግብፅ ኢትዮጵያን 4-0 ስትረታ የሁሉም ግቦች ባለቤት ይኸው ተጫዋች ነበር። በሌላኛው መጥፎ የታሪክ ሪከርድ እ.ኤ.አ 1970 አፍሪካ ዋንጫ በአንድ ጨዋታ በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የሪከርድ ባለቤት አይቮሪኮስታዊው ላውሮ ፖኩ ሲሆን ሃገሩ ኢትዮጵያን 6-1 በረታችበት ግጥሚያ ያስቆጠራቸው 5 ጎሎች ባለ ሪከርድ አድርጎታል።
▶️ ግብፃዊው ግብ አዳኝ ሆሳም ሃሰን በከፍተኛ ዕድሜው እንዲሁም ጋቦናዊው ተጫዋች ሺቫ ንዚጉ በአነስተኛ ዕድሜ ግብ በማስቆጠር ስማቸው በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን። በ2006 ግብፅ ዲ.ሪ ኮንጎን 4-1 ስታሸንፍ ግብ ያስቆጠረው ሆሳም በ39 አመት ከ173 ቀን ዕድሜ ሲሆን ጋቦናዊው ንዚጉ በ2000 በደቡብ አፍሪካ 3-1 ሲረቱ ግብ ያስቆጠረበት 16 አመት ከ93ቀን ግብ በማስቆጠር እንዲሁም በተሳትፎ አነስተኛው ዕድሜ ተብሎ ተመዝግቦ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግብፃዊው ግብ ጠባቂ ኢሳም ኤል ሃድሪ በ2017ቱ የፍፃሜ ጨዋታ ካሜሩንን ሲገጥሙ የተሰለፈበት ዕድሜ 44 አመት ከ19ቀን በተሳትፎ ረገድ አንጋፋው ተጫዋች ያደርገዋል።
▶️ ሶስት የተለያዩ ተጫዋቾች ቢያንስ አንድ ጊዜ በስድስት የተለያዩ ውድድሮች ላይ ኳስና መረብን በማገናኘት ባለ ታሪክ ናቸው። እነርሱም ሳሙኤል ኤቶ (ካሜሩን 2000-10)፣ ካሉሺያ ቩዋላ(ዛምቢያ 1986፣ 1992-2000) እና አሳሞሃ ጂያን (ጋና 2008-17) ናቸው።
▶️ ግብፃውያኑ ጥንዶች አህመድ ሃሰንና ኢሳም ኤል ሃድሪ ስማቸውን በወርቅ መዝገብ ላይ ማስፈር የቻሉበትን ደማቅ ታሪክ እያንዳንዳቸው ወድድሩን ለአራት ጊዜ በመሸነፍ ማፃፍ ችለዋል (1998፣2006፣08፣10)
▶️ ጋናዊው አሰልጣኝ ቻርልስ ጂያሚፊ (1963፣65፣82) እና ግብፃዊው አቻቸው ሃሰን ሸሃታ (2006፣08፣10) ዋንጫውን 3 ጊዜ ወደ ላይ በማንሳት ባለ ሪከርድ ሲሆኑ በአንፃሩ ሌላኛው ግብፃዊ መሃመድ ኤል ጎሃሪ 1959 በተጫዋችነት፣ 2008 በአሰልጣኝነት እና ናይጄሪያዊው ስቴፈን ኬሺ 1994 በተጫዋችነት፣ 2013 በአሰልጣኝነት በድል አድራጎት በታሪክ መዝገብ ላይ ስማቸው ሰፍሯል።
▶️ ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ሄርቬ ሬናርድ ከተለያዩ ሃገራት ጋር የዋንጫ ባለቤት በመሆን ባለ ታሪክ ናቸው (ዛምቢያ 2012 እና ኮትዲቯር 2015።) ሌላኛው ፈረንሳዊ ክሎድ ሎርዋ ደግሞ በዘጠኝ የተለያዩ ውድድሮች 6 ብሄራዊ ቡድኖችን መርተው ሪከርድ ጨብጠዋል። (ካሜሩን 1986፣88፣ ሴኔጋል 1990፣92፣ ጋና 2008፣ ዲ.ሪ ኮንጎ 2006፣13፣ ኮንጎ 2015 እና ቶጎ 2017 በአሰልጣኝነት የመሯቸው ብሄራዊ ቡድኖች ናቸው።)
▶️ ስድሰት ተጫዋቾች በተለያዩ ውድድሮች ደጋግመው የወርቅ ጫማውን በመውሰድ ባለ ሪከርድ ናቸው – ላውሮ ፖኩ (ኮትዲቯር 1968፣70)፣ ሴጉን ኦዴግባሚ (ናይጄሪያ 1978፣ 80)፣ ሮጀር ሚላ (ካሜሩን 1986፣88)፣ ረሺድ ያኪኒ (ናይጄሪያ 1992፣94)፣ ፓትሪክ ኢምቦማ (ካሜሮን 2004፣06)፣ ሳሙኤል ኤቶ (ካሜሮን 2006፣08) የኮከብ ግብ አግቢነት ክብርን ተቀዳጅተዋል።
ምንጮች፡
- የካፍ ኦፊሴላዊ ድህረገፅ www.cafonline.com
- ቶታል ኢነርጂስ ዚምባቡዌ zw.totalenergies.com