ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ‘ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ’ በተሰኘው የ2018 ሶፊማልት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አለምአቀፍ 10ኪ.ሜ. የበጎ አድራጎት ዘመቻው አማካኝነት ያሰባሰበውን 4 ሚሊዮን ብር በቼሻየር ኢትዮጵያ መናገሻ ቢሮ በተከናወነ ደማቅ ስነ-ስርዓት ለተመረጡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አስረክቧል።
በዘንድሮው የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ድጋፍ የተደረገላቸው ተቋማት ቼሻየር ኢትዮጵያ፣ ተስፋ ማህበራዊና ልማት ማህበር ፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌደሬሽን እና እዘነት አካል ጉዳተኞች ህፃናት እና ወላጆች መርጃ ድርጅት በኢትዮጵያ ናቸው።
በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ ባስተላለፉት መልዕክት “ዛሬ ማዕከሉን ተገኝቼ በመጎብኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል ፤ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው ባሻገር ህዝብን ከማስተሳሰር ባለፈ፣ ችግረኞችን ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት ለሌሎችም አርአያ የሚሆን ተግባር ነው።በቀጣይም ሌሎች በርካታ ተቋማትን ማገዛችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበኩሉ “ይህን ‘ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ’ ዘመቻን ስንጀምር ዓላማችን ስፖርታዊ ውድድሩ ለወገኖቻችን መድረሻ እንዲሆን ነበር። ዛሬ ላይ በየአመቱ ተጠናክሮ መቀጠሉ አስደሳች ነገር ነው። ከምንሰበስበው ገንዘብ በላይ ለበጎ አድራጎት ድርጅቶቹ በሚሰጠው ትኩረት ትልቅ ኩራት ይሰማኛል” ሲል ገልጿል።
በዕለቱ በግላቸው ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ላሰባሰቡና ለዘመቻው ስኬት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ልዩ ዕውቅና ተሰጥቷል። ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ወደፊትም ስፖርትን ከበጎ አድራጎት ጋር በማስተሳሰር ማህበራዊ ግዴታውን መወጣቱን እንደሚቀጥልም በዚሁ ወቅት ተገልጿል።
ይህ ‘ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለሁ’ የተሰኘው ዘመቻ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ውድድርን ከማዘጋጀት ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከሚወጣባቸው መንገዶች ዋነኛው ሲሆን፤ ከተጀመረም 20 ዓመታትን አስቆጥሯል። ባለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ከተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በማሰባሰብ ለተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል። ዘመቻው ከገንዘብ ድጋፍ ባለፈ ተቋማቱ ተከታታይ የድጋፍ ምንጭና የመገናኛ ብዙኃን ሽፋን እንዲያገኙ በማድረግ ለህጻናት፣ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞችና ለተፈናቃዮች የላቀ ፋይዳ ያለው ስራ ሲያከናውን ቆይቷል።




