ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዛሬ የ2019 ዓ.ም. ዓለም አቀፍ 10 ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ ምዝገባን በይፋ አስጀምሯል። ውድድሩ እሑድ ህዳር 13 ቀን 2019 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት በታሪኩ ከፍተኛውን 60,000 ተሳታፊዎች ለመቀበል ዝግጅት ተደርጓል።
ይህ ውድድር በተጨማሪም ባንክ ኦፍ አሜሪካ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና አጋር (Presenting Partner) ሆኖ የሚጀምርበት የውድድር ዓመት ይሆናል።
ባለፈው ህዳር ወር የተፈረመውን ስምምነት ተከትሎ፣ በአፍሪካ ትልቁ የጎዳና ላይ ሩጫ በ2030 ዓ.ም. የዓለም ትልቁ 10 ኪ.ሜ. ሩጫ ለመሆን ያለመ ሲሆን፣ ለበርካታ ወጣቶች የመሳተፍ እድልን በማስፋትና በህጻናት ውድድሮች ተሳትፎን በማሳደግ ይህን ግብ ለማሳካት እየሰራ ይገኛል።
የ10 ኪ.ሜ. ውድድሩ ተሳታፊዎች ቁጥር ከፍ እያለ ከመምጣቱ ባሻገር በአንድ ቀን ልዩነት የሚካሔደው የህጻናት ሩጫም በተሳታፊ ቁጥር በማደግ 5,000 ህጻናት እንዲሳተፉበት ይደረጋል።
በተጨማሪም፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ በየዓመቱ በዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዙሪያ በሚካሄደው የ’ቅድሚያ ለሴቶች የ5ኪ.ሜ. ሩጫ’ (Women First 5km) ውድድርም ዋና አጋር ሆኗል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዳግማዊት አማረ ዛሬ በተካሄደው የምዝገባ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት እንደተናገሩት “ዛሬ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጉዞ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የምንከፍትበት ቀን ነው። ዓላማችን የዋና ውድድራችንን ተፅዕኖ በወጣቶች ዕድል ፈጠራ፣ በስፖርት ቱሪዝም እና በአካባቢያዊ ኢኮኖሚ ላይ ይበልጥ ማሳደግ ነው። ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር የጀመርነው አዲስ አጋርነት እንዲሁም ከሌሎች አጋሮቻችን የምናገኘው ቀጣይ ድጋፍ ለወደፊቱ ብዙ አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥር በታላቅ ተስፋ እንጠብቃለን” ሲሉ በተጨማሪም ውድድሩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ የዓለም ትልቁ 10ኪ.ሜ. የጎዳና ላይ ሩጫ ለመሆን ያለውን ራዕይ ገልጸዋል።
ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የባንክ ኦፍ አሜሪካ የበላይ ኃላፊ የሆኑት ይቮን ኢኬ በላኩት መልዕክት “ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማህበረሰቦችን ለማቀራረብ፣ ቀጣዩን ትውልድ ለማነሳሳት እና ኢትዮጵያን ለአለም ለማስተዋወቅ አቅም ያለው መድረክ ሆኗል። ተፅዕኖው ከዕለት ውድድርነት ባለፈ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚፈጥር እና የአካባቢ ንግድ ድርጅቶችን የሚደግፍ ነው ፤ እኛም ከእንደዚህ አይነት ዝግጅት ጋር አጋር በመሆናችን ኩራት ይሰማናል። በአንድነት ሆነን ተሳትፎውን ለማስፋት፣ ተጨማሪ ወጣቶችንና ሴቶች እንዲሳተፉ ለማበረታታት እና ከአፍሪካ በጣም ታዋቂ የስፖርት ዝግጅቶች አንዱ የሆነበትን የስፖርት ግፅታ ለማጠናከር እንሰራለን” ብለዋል።
ውድድሩ ከ2017ዓ.ም. ጀምሮ የወርልድ አትሌቲክስ ሌብል ዕውቅና ያገኘ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖው እያደገ የመጣ ሲሆን፤ አብዛኛው ተሳታፊ ኢትዮጵያዊ ቢሆንም አለም አቀፍ ሯጮችም የውድድሩ አካል ይሆናሉ።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በህዝባዊነቱ እና በተሳታፊዎቹ ውበት እንዲሁም በኢትዮጵያ ሕዝብ ውስጥ በሚፈጥረው የኩራትና የአንድነት ስሜት የሚታወቅ ውድድር ነው። በዚህ መሰረት፣ በተሳታፊዎች የዕድሜ ስብጥር ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት፣ ከጠቅላላው የምዝገባ ቁጥር 5 በመቶ የሚሆነውን (3,000 የመሮጫ ቦታ) በነፃ በዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍልን ለሚያጠናቅቁ ተማሪዎች ተመድቧል።
በተጨማሪም፣ በውድድሩ የ26 ዓመት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ሰዓት በታች እንሮጣለን በሚል በአረንጓዴው መነሻ ላይ ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች የሰአት መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ይውላል። እንዲሁም ሁሉም ተሳታፊዎች ለውድድሩ በተሻለ ሁኔታ እንዲዘጋጁና ሩጫን የዕለት ተዕለት የአኗኗር አካል እንዲያደርጉ፣ በአዲሱ የልምምድ መተግበሪያ (Training App) እንዲመዘገቡና እንዲጠቀሙ ይበረታታል።
በተጨማሪም በዛሬው የምዝገባ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ፣ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ለሚያካሒደው ‘ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለው’ [Run For A Cause] የድጋፍ ማሰባሰቢያ ዘመቻ በኦንላይን GivenGain ድረ-ገፅ አማካኝነት የሚሰበሰበውን ድጋፍ የበለጠ ለማሳደግ ያዘጋጀውን ዕቅድ ይፋ አድርጓል። በዚህ ዓመት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ለማሰባሰብ ግብ የተቀመጠለት ይህ ዘመቻ፣ በኢትዮጵያ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተመረጡ ሶስት ተቋማትን ተጠቃሚ ያደርጋል።
በ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10ኪ.ሜ. ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች ምዝገባቸውን በቴሌብር መተግበሪያ ብቻ ማከናወን ይችላሉ። የምዝገባ ዋጋው ከመስቀል አደባባይ ለሚጀምረው ቀይ መነሻ 790 ብር፣ ከግዮን ሆቴል ፊት ለፊት ለሚጀምረው እና የሰአት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ለሚኖረው አረንጓዴ መነሻ 950 ብር መሆኑ ተገልጿል።
የዘንድሮው የውድድሩ መሪ ቃል (Race theme) “ሩጫዬ ቀለሜ” (My Run, My Color) ሲሆን፣ የውድድሩ ዋና የስያሜ አጋር (Presenting Partner) ባንክ ኦፍ አሜሪካ ነው። በተጨማሪም ዩኒሴፍ (UNICEF)፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ቴሌ ብር፣ ሶፊ ማልት፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ሶሲ ሶያ፣ ፋብ ሳሙና፣ ህያት ሪጀንሲ አዲስ አበባ፣ ቶፕ ውሃ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (EBC)፣ እንዲሁም አፍራን ሆስፒታል ለውድድሩ ስኬት በአጋርነት የሚሰሩ ተቋማት ናቸው።
Source- Great Ethiopian Run




