የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ድህረ ጨዋታ ሀሳቦች

written by Leoul Tadesse

የዘንድሮ ቻምፒየንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ ለእኩል የቀረበ እድል ያላቸውን ቡድኖችን አገናኝቷል። አራቱም ቡድኖች የተለያየ የአጨዋወት ማንነት ያላቸው ቡድኖች መሆናቸውም ጨዋታዎቹን አጓጊ ያደርጋቸዋል። ተፋላሚዎቹን የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ግን አለ – የአሰልጣኖቹ አሻራ በጉልህ የሚታይባቸው የ’አሰልጣኝ ቡድን’ መሆናቸው። አሰልጣኞቹ ቡድኖቹን ያሰለጠኑባቸው ጊዜ ርዝመት ቢለያይም፣ ሁሉም ከቀደምቶቻቸው ፍፁም የተለዩ ቡድኖችን ገንብተዋል። ሚኬል አርቴታ ለዓመታት ችግር ውስጥ የነበረ፣ መነሳት እና መፎካካር ያቃተውን ቡድን አፍርሶ ቀስ በቀስ በጡብ ላይ ጡብ እየጨመረ ራሱን የመሰለ ጠንካራ፣ ኮምጫጫ፣ ተቀያያሪ እና በሁሉም ዘርፎች የላቀ ቡድን ገንብቷል። ሲሞኒ ኢንዛጊ የአንቶኒዮ ኮንቴን 3-5-2 ቢያስቀጥልም፣ በተለይ ኳስ ይዞ በመጫወት፣ በፈጠራ፣ በማጥቃት እና በተለዋዋጭነት ፍፁም የተለየ እና የተሻለ ኢንተርን እያሳየን ይገኛል። ሉዊስ ኤንሪኬ የ’ቀበጦቹን ከዋክብት’ ፒኤዤ፣ ወደሮጠው ያልጠገቡ፣ ታታሪ፣ ለቡድን የሚለፉ ወጣቶች አስደናቂ ቡድንነት ቀይሮታል። ሀንሲ ፍሊክ በበኩላቸው ባለፈው የውድድር ዘመን ደካማ የነበረው ባርሴሎናን በሁሉ ረገድ ድንቅ የሆነ፣ በርካታ ጨዋታ-ቀያሪ ተጨዋቾችን የያዘ እና ‘ትሬብል’ ለማሸነፍ የሚጫወት ቡድን አድርገውታል፤ የቡድኑን ግርማ-ሞገስም መልሰውታል። ግማሽ ፍፃሜውም ከተጨዋቾች ጥራት ይልቅ ታክቲክ እና ስነ-ልቦና የሚወስነው የሚመስለው በአሰልጣኞቹ የእስካሁን ስኬት የተነሳ ነው።

ቻምፒየንስ ሊጉ የዘንድሮ ባሎን ዶ’ር ተፎካካሪ ሊሆኑ የሚችሉ ከዋክብትን እያንጠባጠበ እዚህ ደርሷል። ሳላህ፣ ቫንዳይክ፣ እምባፔ እና ሁሊያን አልቫሬዝ በግላቸው (ሳላህ እና ቫን ዳይክ በሊጉ ከቡድናቸውም ጋር) ድንቅ የውድድር ዘመን እያሳለፉ ቢገኙም፣ የሀገራት ውድድር በሌለበት ዓመት ትኩረት የሚደረገው ቻምፒየንስ ሊግ ላይ በመሆኑ እድሉ ያመለጣቸው ይመስላል። ጥሩ ያልሆኑት ቪኒሲዩስ፣ ቤሊንግሀም እና ሀላንድም እንደዚያው። በእኔ እምነት አሁን አምስት/ስድስት የተሻለ እድል ያላቸው ተጨዋቾች አሉ። ሶስት ከባርሴሎና (ራፊንሀ፣ ያማል እና ፔድሪ)፣ ሁለት ከፒኤዤ (ዴምቤሌ እና ቪቲኒሀ) እና ላውታሮ ማርቲኔዝ። አርሰናል ሻምፒዮን ከሆነ ምናልባት ራይስ ወይም ሳካ የ2006ቱ የፋቢዮ ካናቫሮን ያልተጠበቀ በጥቂት ጨዋታዎች ግዙፍ ተፅዕኖ የተገኘን አሸናፊነት ይደግሙት ይሆናል።

የሩብ ፍፃሜው ምርጥ ተጨዋቾች (ብዙ የተባለላቸውን አይጨምርም):- ፒኤዤ ከዶናሩማ እስከ አጥቂው ዴምቤሌ በሁሉ ረገድ የተሟላ ቡድን ነው። በተለይ ስለአማካይ ክፍሉ ብዙ ተብሏል። አሁን ግን ፉልባኮቹ አችራፍ ሀኪሚ እና ኑኖ ሜንዴሽን ግን በተለየ ማንሳት አለብኝ። ማጥቃት የሚወዱት እና በኤንሪኬ ነፃነታቸውን ያገኙት ጥንድ የተጋጣሚያቸውን አጥቂዎች ከማቆም አልፈው አስቶን ቪላ ላይ ሶስት ወሳኝ ጎሎች አስቆጥረዋል። ሀኪሚ በቀኝ እና ሜንዴሽ በግራ ሲያሻቸው በውጪ በኩል እየደረቡ፣ ሲፈልጉ ወደውስጥ እያጠበቡ የቪላን ተከላካዮች ሲያሸብሩ ነበር።

ለመድፈኞቹ ድል የራይስ እና ሳካ ተፅዕኖ ቢጎላም ልዊስ-ስኬሊ እና ሜሪኖም የሚገባቸውን ክብር ቢያገኙም ሌሎች ሊነሱ የሚገባቸውም አሉ – ቲምበር እና ኪቪዮር። ስለሁለገቡ ሆላንዳዊ ምን ማለት ይቻላል? ተጨዋች ከACL ጉዳት ተመልሶ እንዴት እንዲህ አይነት ድንቅ የውድድር ዘመን ያሳልፋል? ሲከላከል ጠንካራ፣ ሲያጠቃ ደፋር፣ ከስህተት የፀዳ፣ ግርግር የሌለበት የስራ ሰው። ፖሊሹ የመሀል ተከላካይ በበኩሉ የብዙዎችን ስጋት እና ጥርጣሬ ያስረሱ 180 ደቂቃዎች አሳልፏል። ከመጀመሪያው ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በኋላ ኪቪዮር ድንቅ ነበር። ለሶስት ወራት አንዴም ሳይጫወት ወንበር ሲያሞቅ ቆይቶ በድንገት ይህ ኃላፊነት ወድቆበት በስኬት መወጣት የሚያስደምም ነው።

የምርጥ ዓመታቱ ብቃቱን እና አስፈሪነቱን ያሳየን ራሽፈርድ፣ በመጀመሪያው ጨዋታ እድሎቹን ባይጠቀምም በመልሱ ጨዋታ ሀት-ትሪክ ሰርቶ ካታላኖቹን ያስደነገጠው ጊራሲ፣ አምስት ጎሎች ቢቆጠሩበትም ፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ በርካታ ሙከራዎችን ያዳነው ኩርቷ ከተሸናፊ ወገን ቢሆኑም በግላቸው የሚኮሩበትን ብቃት አሳይተዋል።

  • Leoul Tadesse

    Related Posts

    የአለም አትሌቲክስ ከ2030 ጀምሮ ራሱን የቻለ የአለም ማራቶን ሻምፒዮና ሊያስተዋውቅ ነው

    የአለም አትሌቲክስ ከ2030 ጀምሮ “የአለም አትሌቲክስ ማራቶን ሻምፒዮና” በማዘጋጀት ለወደፊቱ የረጅም ርቀት ሩጫ ትልቅ ነገርን አሰናድቷል። ማራቶን በ2027 እና 2029 የአለም አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ እንደ አንዱ የውድድር አይነት ሆኖ የሚቀጥል…

    የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አዲስ አሰልጣኝ አግኝቷል

    የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌን ቀጣዩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ በመምረጥ ውሳኔ አሳልፏል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ በአሁኑ ወቅት የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ሆነው…

    Leave a Reply

    You Missed

    ትዕግስት አሰፋ የራሷን የማራቶን ክብረ ወሰን አሻሽላለች 

    ትዕግስት አሰፋ የራሷን የማራቶን ክብረ ወሰን አሻሽላለች 

    Olympic Champion Gabby Thomas Touches Down in Addis Ababa for Historic Grand Prix

    Olympic Champion Gabby Thomas Touches Down in Addis Ababa for Historic Grand Prix

    Doha Diamond League Postponed to June; Venue Switched to Khalifa International Stadium

    Doha Diamond League Postponed to June; Venue Switched to Khalifa International Stadium

    የአለም አትሌቲክስ ከ2030 ጀምሮ ራሱን የቻለ የአለም ማራቶን ሻምፒዮና ሊያስተዋውቅ ነው

    የአለም አትሌቲክስ ከ2030 ጀምሮ ራሱን የቻለ የአለም ማራቶን ሻምፒዮና ሊያስተዋውቅ ነው

    World Athletics to introduce standalone World Marathon Championships from 2030 

    World Athletics to introduce standalone World Marathon Championships from 2030 

    Saint George respond on the pitch 

    Saint George respond on the pitch